ሰሞነኛው ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ በኢትዮጵያ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2015አዲስ አበባን ጨምሮ ሰሞኑን በመላ አገሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለው ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ ሰዎች ታመዋል፡፡ ተዋሲው ከሰው ሰው ልዩነት ያለው የህመም ምልክቶችን እንደሚያሳይ ነው የሚነገረው፡፡ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳመለከተው ወረርሽኙ የዝናብ ወራት ማለፍን ተከትሎ የተከሰተና የተሰራጨ ነው፡፡ በሽታው ላይ እስካሁን በተወሰዱ ናሙናዎች መደበኛ ኢንፍሉዌንዛ አንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከወትሮ ቁጥሩ ከፍ ብሎ መታየቱንም የምርመመራ ውጤቶች ያሳያሉ ብሏል፡፡
“ሲጀምረኝ በጉሮሮ ህመም ነው የጀመረኝ፡፡ እህል እንኳ ለመዋጥ ለአንድ ሁለት ቀናት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ከዚያን ትኩስ ትኩስ ስወስድበት ጉሮሮዬን ተሻለኝ፡፡ ከዚያን በመቀጠል ድምጽ እንደማፈን፣ በአፍንጫ ፈሳሽ ነገር መውረድ እና ሳል ነገር አብሮት መጣ፡፡”
ሰሞኑን አገር ባዳረሰው ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ የተጠቁት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ስለ በሽታው ጠባይ እና በሳቸው ላይ የተከሰተውን የህመሙ ምልክት ሲያብራሩ የገለጹት ነው፡፡ አስተያየት ሰጪያችን አቶ በፍቃዱ ጌታነህ፤ መላ ቤተሰባቸውን እንዳዳረው የገለጹት ወረርሽኙ በሁሉም ሰው ላይ ያውና ተመሳሳይ የሆነ ምልክትም እንደማያሳይ ነው የገለጹት፡፡
“ለምሳሌ እኔ አሁን የጉንፋን ስሜት ብቻ ነው ያለኝ፡፡ ከባድ እራስ ምታትም እንዲሁ ተከስቶብኛል፡፡ ሌሎች ላይ ደግሞ እንደ ቁርጥማት አይነት ምልክትም ተስተውሏል፡፡ ብርድ ብርድ የሚለውም አለ፡፡ ምልክቱ እንደተረዳሁት ያውና ተመሳሳይ አይደለም፡፡”
የወረርሽኙ ተጠቂ መሆኗን የምትገልጸው ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኤዴንም የህመሙን ክብደት ስታስረዳ፡ “እስካሁን ሁለት ሳምንት ቆይቶብኛል፡፡ አሁንም ሙሉ በሙሉ ለቆኛል ማለት አልችልም፡፡ እራሴን ያመኛል፡፡ ከባድ ቁርጥማትም አለው፡፡ የማዳከም ባህሪ አለው በጣም ከባድ ነው” ትላለች፡፡
ወረርሽኙ እንደተከሰተ ብሄራዊ የኢንፍሉዌንዛ ላቦራቶሪ ናሙናዎችን በመውሰድ ምርመራዎችን በማካሄድ የቅኝት ስራዎችን ሲያካህድ መቆየቱን የሚያነሳው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፤ ወረርሽኙ የዝናብ ወራት ማለፉን ተከትሎ በመከሰት የተስፋፋ ነው ይላል፡፡ ወረርሽኙ ከኮቪድ-19 ጋር የሚያያዝ ስለመሆን አለመሆኑም የተጠየቁት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በርግጥ የኮቪድ ወረርሽኝም አሁን ላይ የመጨመር አዝማሚያ ቢያሳይም በቫይረሱ የተያዙ ሁሉ በኮቪድ የተያዙ ናቸው የሚል መደምደሚያ ግን አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡ ወረርሽኙ እስካሁን አስጊ ሊያስብልና የተለየ ስጋት በሚያጭር ደረጃ ላይ አለመሆኑን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ ጥንቃቄዎች ግን እንዲደረጉም አሳስበዋል፡፡ “የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥርና ምላሽ ማዕከላችን በተደራጀ አኳሃን እየሰራበት ነው፡፡ ይህ ግን የሚያሰጋ የህብረተሰብ የጤና ችግር አይለም፡፡ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በተለይም ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የጤና ባለሙያዎችን ቀረብ ብለው እንዲያማከክሩ ስናሳስብ ቆይተናል፡፡ በቫይረሱም የተጠቁ ስርጭቱ እንዳይስፋፋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በቂ እረፍትም በመውሰድ እንደሁልጌዜው ፈሳሽና ትኩስ ነገሮች እንዲወስዱ፤ በሽታውም ከባሰባቸው ተገቢውን ህክምና እንዲወስዱ ነው የምንመክረው” ብለዋልም፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ