1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የንብረት ታክስ ማን ስንት ይከፍላል?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥር 7 2017

ኢትዮጵያውያን በቤት እና በመሬት ግብር የሚከፍሉበት የንብረት ታክስ በተቃዋሚዎች ትችት ቢገጥመውም ጸድቋል። ተቃዋሚዎች አዲሱ ታክስ በሸማቾች ላይ ጫና እንደሚፈጥር አስጠንቅቀዋል። መንግሥት “ፍትኃዊ የሀብት ክፍፍል የሚያሰፍን” ያለው የንብረት ታክስ በክልሎች ይሰበሰባል። ለመሆኑ በንብረት ታክስ ማን ስንት ይከፍላል? የማይከፍሉትስ እነ ማን ናቸው?

https://p.dw.com/p/4pB5z
አዲስ አበባ የመኖሪያ ቤቶች
ኢትዮጵያውያን በቤት እና በመሬት ግብር የሚከፍሉበት የንብረት ታክስ በተቃዋሚዎች ኃይለኛ ትችት ቢገጥመውም በአራት ተቃውሞ እና በአስር ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።ምስል Eshete Bekele Tekle/DW

በኢትዮጵያ የንብረት ታክስ ማን ስንት ይከፍላል?

የኢትዮጵያ መንግሥት “በከተማ ነዋሪዎች መካከል ፍትኃዊ የሀብት ክፍፍል የሚያሰፍን” ያለው የንብረት ታክስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመጽደቁ በፊት በአባላቱ መካከል ሞቅ ያለ ክርክር አስነስቷል።  ከምክር ቤቱ ሕግ አውጪዎች 255 ብቻ በተገኙበት መደበኛ ጉባኤ በአዋጁ ላይ ጠጠር ያለ ተቃውሞ ያቀረቡት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ናቸው።

በአራት ተቃውሞ እና በአስር ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው አዋጅ የክልል መንግሥታት በአካባቢ መስተዳድሮች አማካኝነት በንብረት ላይ የሚጣል ግብር እንዲሰበስቡ ሥልጣን የሰጠ ነው።

አዋጁን መርምሮ የተሰጡ ማሻሻያዎችን በማከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ “በፍጥነት እየጨመረ ያለውን የከተማ ነዋሪ ሕዝብ የመገልገያ ፍላጎት በአግባቡ ለማሟላት የሚያስችል ገቢ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለማመንጨት የሚረዳ” እንደሆነ ገልጿል።

አዲሱ አዋጅ በመንግሥት ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር መሠረት የሚከናወነው የታክስ ማሻሻያ አካል እንደሆነ የተናገሩት የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የልማት ዕቅዶችን ለማስፈጸም “የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ” አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዘላቂ የልማት ፋይናንስ ለመፍጠር ሥራ ላይ በሚገኙ ሕጎች ገቢ መሰብሰብ ብቻውን እንደማይበቃ ያስረዱት አቶ ደሳለኝ “አዳዲስ የታክስ አይነቶች መጣል” ሌላው አማራጭ እንደሆነ አስረድተዋል።

“የከተሞች መስፋፋት እና አጠቃላይ ዕድገት ተከትሎ ሰፋፊ የልማት ፍላጎቶች እየመጡ ነው። እነዚያን የልማት ፍላጎቶች በመንግሥት ወጪ ብቻ መሸፈን አይቻልም” ያሉት ሰብሳቢው “ብዙዎቹ ከተሞቻችን ከጠቅላላ የልማት ፍላጎታችን 70 በመቶ የሚሆነውን በፌድራል እና በክልል [መንግሥታት] ነው የሚደጎሙት” ሲሉ ተደምጠዋል።

 ከተሞች “የመንግሥትን ወጪ መጋራት አለባቸው” በማለት የተናገሩት አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የንብረት ታክስ “በፌድራል [መንግሥት] ላይ ያለውን የበጀት ጫና መቀነስ” እና ከተሞች በራሳቸው እየጠነከሩ እንዲሔዱ” የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

የንብረት ታክስ ማን ስንት ይከፈላል?

ዜጎች የሚከፍሉት የግብር መጠን የሚወሰነው ባለፈው ታኅሳስ በጸደቀው የሪል እስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይት እና ግመታ አዋጅ መሠረት ነው። ይኸ የግብር አይነት አንድ ንብረት ከዓመት ዓመት በሚያሳየው የዋጋ ለውጥ ላይ የሚጣል ነው።

በአዋጁ መሠረት የንብረት ታክስ የሚከፈልበት ከአንድ ንብረት የገበያ ዋጋ 25 በመቶው ብቻ ነው። ይሁንና የገንዘብ ሚኒስቴር በጥናት ላይ በመመሥረት ታክስ የሚከፈልበትን ዋጋ ከፍ ወይም ዝቅ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር
የገንዘብ ሚኒስቴር በጥናት ላይ በመመሥረት ታክስ የሚከፈልበትን ዋጋ ከፍ ወይም ዝቅ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታልምስል Eshete Bekele/DW

አቶ ደሳለኝ ወዳጄ “ለቤት ከ0.1 በመቶ እስከ 1 በመቶ፤ ለመሬት ደግሞ ከ0.2 በመቶ እስከ 1 በመቶ” የንብረት ታክስ እንደሚከፈል አስረድተዋል። “የትኛውም ክልል ወይም የከተማ አስተዳደር ሲጀምር ከ0.1 በመቶ ነው” ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ “በአራተኛው ዓመት ላይ የመጨረሻው ላይ መድረስ አለበት” ሲሉ ሒደቱን አስረድተዋል።

ጭማሪውን “የሕዝቡን ፍላጎት፣ ስሜት እና አጠቃላይ አቅም” በማጥናት እና በመመካከር የመወሰን ሥልጣን ክልሎች ተሰጥቷቸዋል። አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የንብረት ባለቤቶች የሚከፍሉት የግብር መጠን ምን ያክል እንደሚሆን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ማብራሪያን እየጠቀሱ ሲያስረዱ “20 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቤት ያለው ሰው በዓመት አንድ ጊዜ ክፍያው 5,000 ብር ነው ሊሆን የሚችለው” ብለዋል።

10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቤት 2,500 ብር፤ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቤት 1,250 ብር፤አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ቤት ያለው 250 ብር ሊከፍል እንደሚችል ተናግረዋል። የንብረት ባለቤቶች ክፍያውን በአንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ማከናወን ይችላሉ።

የፌድራል እና የክልል መንግሥታት ተቋማት የንብረት ታክስ አይከፍሉም። “ለሕብረተሰቡ ነጻ የማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ለዚሁ አገልግሎት የሚጠቀሙበት ቦታ እና ሕንጻ” ከንብረት ታክስ ነጻ ሆኗል። የኃይማኖት ተቋማት ለአምልኮ እና ለመካነ-መቃብር አገልግሎቶች የሚጠቀሙባቸው ቦታዎች እና ሕንጻዎችም ተመሳሳይ ዕድል አግኝተዋል።

አዋጁ “ዝቅተኛ ገቢ ላለው አንድ ቤተሰብ በመኖሪያነት አገልግሎት እየሰጠ ያለ የመኖሪያ ሕንጻ” የንብረት ታክስ እንደማይከፈልበት ይደነግጋል። ይሁንና “ዝቅተኛ ገቢ” የሚለው መመዘኛ በምክር ቤቱ አከራካሪ ነበር።  

“አዲስ አበባ ላይ ያለ ዝቅተኛ ገቢ ከኑሮ ውድነት እና ከቤት ኪራይ ጋር ተያይዞ ወደ ክፍለ ሀገር ሲሔድ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል” ያሉት የብልጽግና ፓርቲ አባል የሆኑት አለሙ ጎንፋ “ዝቅተኛ ገቢ ምንድነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። “ጡረተኛ፣ ከ60 ዓመት በላይ ያለ ሰው፤ ገቢ የሌለው አይክፈል ከተባለ” በግልጽ ማስቀመጥ እንደሚሻል የመከሩት አቶ አለሙ “የማይከፍሉ” የንብረት ባለቤቶች በአዋጁ በግልጽ ካልሰፈረ “ዝቅተኛ” የሚለው መመዘኛ “መለኪያ የለውም” ሲሉ ሞግተዋል።

የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባል የሆኑት አበባው ደሳለው አንድ እና ሁለት ክፍሎች የሚያከራዩ የመንግሥት ሠራተኞች “ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ” ከንብረት ታክስ ነጻ “ማድረግ አይቻልም ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። ለዚህም “ካለው የኑሮ ውድነት የተነሳ የኢትዮጵያ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ሳይቀር የኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኞች ታክስ ይቀነስ እያለ በተደጋጋሚ በሚጠይቅበት” የንብረት ታክስ ሥራ ላይ የሚውል መሆኑን አንስተዋል።

Äthiopien | Geldscheine Währung
ምስል MICHELE SPATARI/AFP

አቶ ደሳለኝ ወዳጄ “ዝቅተኛ ገቢ ያለው ገቢው ምን ያህል ነው? የመኖሪያ ቤቱ ስፋት ስንት ካሬ ነው?” የሚለውን ጉዳይ የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ “መለየት” እንደተቸገረ አምነዋል። ቋሚ ኮሚቴው ጉዳዩን “ሁለት ሦስት ጊዜ ካየ በኋላ ክልሎች ከየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አይተው ዝቅተኛ የሆነውን ሊያስቀምጡ ቢችሉ” የሚል አቋም መያዙን አስረድተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከንብረት ታክስ ለመሰብሰብ የተነሳው የኑሮ ውድነት በኃይል በበረታበት ወቅት ነው። መንግሥት ከታክስ የሚሰበስበውን ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ ያለውን ምጣኔ 4% የመጨመር ዕቅድ አለው። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች ግን የንብረት ታክስ በሸማቾች አቅም ላይ የሚያስከትለው ጫና አስግቷቸዋል።

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል የሆኑት መብራቱ ዓለሙ “የዋጋ ንረቱ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የማክሮ ኤኮኖሚ አለመረጋጋት እንዲሁም የድህነት መጠኑ እጅግ በጣም እየጨመረ ስለመጣ በተለይ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የንብረት ባለቤቶች ይኸንን የንብረት ታክስ የመክፈል አቅማቸው እጅግ በጣም ሊፈትን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የንብረት ታክስ መሰብሰብ ሲጀመር “ተከራዮች በሚሸጧቸው [ምርቶች] እና አገልግሎቶች ላይ ዋጋዎች ስለሚጨምሩ …ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ንረት ሊያጋጥመው ስለሚችል ከዚህ ለመዳን ምን ታሳቢ ተደርጓል?” የሚል ጥያቄም ነበራቸው።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተወካይ የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ ገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት 451.4 ቢሊዮን ብር ከታክስ እና ከጉምሩክ ቀረጥ መሰብሰቡን ይፋ እንዳደረገ ለምክር ቤቱ አስታውሰው አሁን ሥራ ላይ በሚገኙ የግብር አይነቶች “መንግሥት ወጪዎችን ወደ ሚሸፍንበት ደረጃ እየደረሰ ነው” ማለት እንደሚቻል ተናግረዋል። ገቢው የተሰበሰበው “በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዋጋ እየከፈሉ ነው” ያሉት አቶ ደሳለኝ ጫኔ የአዲሱን የንብረት ታክስ ፍትኃዊነት መቀበል እንደሚቸገሩ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። 

“አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በደመወዙ ቤተሰብ መርቶበት፤ 35% ታክስ ከፍሎበት ተበድሮ የመኖሪያ ጎጆ ቀልሶ ለዚያም ብድር እየከፈለ” የንብረት ታክስ መጣል “እኔ ከመቀማት ነጥዬ አላየውም” ሲሉ መንግሥት የተከተለውን አቋም በጽኑ ኮንነዋል።

“የመንግሥት ሠራተኛ እና ዝቅተኛ ነጋዴዎች” የንብረት ታክስ ሊከፍሉ አይገባም የሚል አቋማቸውን በግልጽ አቶ ደሳለኝ ጫኔ ተናግረዋል። “በተደራራቢ በማኅበረሰቡ ላይ በሚጣሉ ግብር እና ታክሶች በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ መማረር ተፈጥሯል” ያሉት ተቃዋሚው ፖለቲከኛ  “ፍትኃዊነቱን በደንብ ብንነጋገርበት” በማለት ጠይቀው ነበር።

“መንግሥት ወጪዎቹን በገቢ ወደ መሸፈን ደረጃ ከተጠጋ ይኸን አዲስ ታክስ ማስተዋወቅ ፍትኃዊ ነወይ?” ሲሉ የጠየቁት የአብን አባል “እኔ አይደለም ብዬ እከራከራለሁ” ሲሉ ለራሳቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

ካዛንቺስ ሲፈርስ
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌላው የአብን አባል  አበባው ደሳለው ከንብረት ታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ከአንገብጋቢ ሥራዎች ይልቅ ለአወዛጋቢው የኮሪደር ልማት ሊውል እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።ምስል Solomon Muche/DW

ከንብረት ታክስ የሚሰበሰብ ገቢ ለየትኞቹ ዓላማዎች ይውላል?

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌላው የአብን አባል  አበባው ደሳለው ከንብረት ታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ከአንገብጋቢ ሥራዎች ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና መንግሥታቸው ለሚያቀነቅኑት አወዛጋቢው የኮሪደር ልማት ሊውል እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

“በቀጥታ የኅብረተሰቡን ኑሮ ያሻሽላሉ ተብለው የሚገመቱ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች ተቋርጠዋል” ያሉት አበባው “የኮሪደር ልማት በፍጥነት የኅብረተሰቡን ኑሮ ያሻሽላል ተብሎ አይገመትም” ሲሉ ተችተዋል።

በአዋጁ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ የመስጠት ኃላፊነት የተጣለባቸው የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ከንብረት ታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ለኮሪደር ልማት አይውልም ብለው ማረጋገጫ ባይሰጡም “ታክሱ የሚውለው ለአካባቢው መሠረተ-ልማት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ኅብረተሰቡ ታክሱን ገና ወደ ሥራ ከማስገባቱ በፊት ለ60 ቀናት ይወያያል። ከተወያየ በኋላ እዚህ አካባቢ ምን ይሠራ? የሚለውን ይለያል። ከዚያ በኋላ ለመሠረተ-ልማት፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች ከተማው ለሚፈልገው ልማት እንዲውል ነው የሚደረገው” ሲሉ አብራርተዋል።

ይሁንና አቶ ደሳለኝ ወዳጄ አዋጁ በግብር ከፋዮች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና አልተቀበሉም። “ይኸ የኑሮ ውድነትን በተለየ ሁኔታ የሚያባብስ አይደለም” ያሉት ሰብሳቢው የንብረት ታክስ የሚጣለው “በተፈጠረ ሀብት ላይ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። “ታክስ የሚከፍለው ቤት ያለው ነው። ቤት የሌለውን አይመለከትም። ሀብት ያለው ላይ ነው። ሀብት የሌለውን አይመለከትም” ሲሉ ተደምጠዋል።

አረጋውያንን ጨምሮ “የመክፈል አቅም የሌላቸው” ኢትዮጵያውያን “ቤታችሁን ሸጣችሁ ክፈሉ” እንደማይባሉ አቶ ደሳለኝ በምክር ቤቱ ተናግረዋል። “መክፈል የማይችሉ መሆናቸውን” የከተማ አስተዳደሮች የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው። ቤታቸውን ሲሸጡ ወይም ሲያወርሱ ግን የሁለት ዓመታት የንብረት ታክስ መክፈል ይጠብቅባቸዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ