1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኪም እና ሙን አንድ ሁለት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2010

የኪም ጆንግ ኡንን ስልት በቅርብ እናዉቃለን የሚሉት ተንታኞች ኪም ነብስ ካወቁ በኋላ ሲሆን ካዩት፤ በሳዳም ወይም በቃዛፊ ላይ ከደረሰዉ መማራቸዉን አይጠራጠሩም።የኪም አስተሳሰብ፤ ዝንባሌ እና ስልት ግን ከቅርቦቹ አረቦች፤ ከሩቁ ጎርባቾቭም ይልቅ ለዴንግ ዢዮፒንግ የሚቀርብ ወይም የዴንግ ዢዮፒንግ ቅጂ ነዉ ባይ ናቸዉ

https://p.dw.com/p/2wwYb
Korea-Gipfel
ምስል Reuters/Korea Summit Press Pool

የኮርያዎች የሰላም ተስፋ

ሶል-ቶኪዮዎችን በዋሽግተን፤ለንደን ብራስልሶች ክርን አተብቶ፤ ፒዮንግዮንጎችን ከቤጂንግ-ሞስኮዎች እቅፍ ዶሎ ሚሊዮኖችን ያረገፈዉ፤ አንዲቱን ሐገር እሁለት የገመሰዉ፤ ኒኩሌር ያማዘዘዉ ጠብ፤ የነሱ እና በነሱ ብቻ ባለመጀመሩ መወገድ-አለመወገዱም የሚበየነዉ በሶል-ፒዮንግዮንጎች ፍላጎት እና ብቻ አለ መሆኑ እርግጥ ነዉ።የ65 ዘመኑን ደም አፋሳሽ ግጭት-ቁርቁስ፤ በሰላም፤የአንዲቱን ሐገር ክፍፍል በዳግም ዉሕደት ለመተካት ፈቃጅ-ከልካዮቹ መስማማት-አለመስማማታቸዉ የሚፀናዉም፤ በጊዜ ሒደት፤ከሁሉም በላይ ከሰላም እኩል ለመጠቀም በሚኖራቸዉ ቁርጠኝነት መሆኑ ሐቅ ነዉ።የሶል-ፒዮንግያንግ መሪዎችን ይሆናል ተብሎ ያልታሰበዉን አደረጉ።የሰላም-ዉሕደትን የተስፋ ጭላንጭል በረቁ።ታሪክ ሰሩ።አርብ።ታሪካዊዉ ክስተት መነሻ፤ ዳራ-ሒደቱ ማጣቃሻ፤ ጭላንጭሉ ተስፋ የመድመቅ-መደንገዙ ምክንያት መድረሻችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

 ፓንሙንጆም፤ አርብ።የሁለቱ መሪዎች የመጀመሪያ ወግ።

የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ሊቀመንበር ኪም ጆንግ ኡን፤-«ከርስዎ ጋር በመገናኘቴ ደስ ብሎኛል።በጣም ደስብሎኛል።

የደብቡ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት ሙን ጄ-ኢን፤-«ደሕና መጡ? ወደዚሕ ሲመጡ ችግር ነበር?»

ኪም፤-«በጭራሽ»

ሙን፤ «ከእርስዎ ጋር በመገናኘቴ ደስ ብሎኛል።»

ኪም «በዚሕ ታሪካዊ ሥፍራ በመገናኘታችን ልቤ በደስታ ተሞልቷል።-----እኔን ለመቀበል ይሕን ሁሉ መንገድ አቋርጠዉ እዚሕ ወታደራዊ ድንበር ድረስ በመምጣትዎ ደግሞ ልቤ ተነክቷል።»

ሙን፤-«እዚሕ ድረስ እንድንመጣ ያደረገዉ የርስዎ ቆራጥ እና ደፋር ዉሳኔ ነዉ።»

Kim Jong Un und Moon Jae-in pflanzen Baum
ምስል picture-alliance/AP Photo/Korea Summit Press Pool

እያሉ ሲመሰጋገኑ፤ ሲጨባበጡ፤ ሲተቃቀፉ ቆዩ።ላፍታ።ሁሉቱም ግን፤ ሁለቱን ኮሪያዎች ከሚገምሰዉ ወታደራዊ መስመር  ሰሜን እና ደቡብ እንደቆሙ ነበር።«እባክዎ ከመስመሩ በዚሕኛዉ በኩል ይቁሙ።» ጠየቁ።ሙን። ኪም መስመሩን ተሻገሩ።ከ1950 ወዲሕ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ለመጀሪያ ጊዜ የሰሜን ኮሪያ መሪ የደቡብ ኮሪያን ግዛት ረገጠ።ኪም በፋንታቸዉ የሙንን እጅ ይዘዉ ወደ ሰሜኑ ግዛት እንዲሻገሩ ተጠየቋቸዉ።ሙን ተሻገሩ።

የቀድሞዉ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ሮሕ ሙ ሕዩን በ2007 ሰሜን ኮሪያን ከጎበኙ ወዲሕ የደቡብ ኮሪያ መሪ የሰሜንን ግዛት ሲረግጥ ሙን የመጀመሪያዉ ሆኑ።የሙን ወደ ሰሜን መሻገር እስቀድሞ ስላልታቀደ እዚያ የነበሩትን አስደነቀ።አሳቀ፤አስጨበጨበም።

                         

እኚሕ አጭር፤ ድንቡሽቡሽ፤ ወፍራም፤ ጠጉረ ቄንጠኛ ጎረምሳ ብዙዎችን ብዙ ጊዜ እንዳስደነቁ፤ የብዙዎችን ግምት እንደተቃረኑ ነዉ።ዘንድሮ 34 ዓመታቸዉ።ለሚጠላቸዉ፤ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም እንደ ታላቅ ሐገር መሪ ሳይሆን  እንደ «ጋጠ-ወጥ» እንደተሳደቡት «አጭር ነዉጠኛ ናቸዉ»

                        

«በነገራችን ላይ ባለ ሮኬቱ ሰዉዬ ከብዙ ጊዜ በፊት (ዋጋዉን ማግኘት) ነበረበት።አጭር የሮኬት ሰዉ።ማድረግ አለብን።ምክንያቱም ምርጫ የለንም።»

የእድሜያቸዉን ለጋነት፤ የአስተናደጋቸዉን ቅምጥልነት፤የፖለቲካ ልምዳቸዉን ዉስንነት ምክንያት የሚጠቅሱ ተንታኞች በበኩላቸዉ ሰዉዬ እንድ ብዙ የዕድሜ አቻዎቻቸዉ በመቅበጥ መፈንጠዝ፤ መጫወት እንጂ ሌላ አያዉቁም ይላሉ።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለሰላም ከመደራደር ይልቅ የሚሳዬል እና የኑክሌር ቦምብ ሙከራ፤ ፉከራ ዛቻቸዉን መደጋጋማቸዉ፤ ቻይን ከመሰለች የሐገራቸዉ ታሪካዊ ደጋፊ ጋር ያላቸዉን ወዳጅነት በጥንቃቄ መያዛቸዉን የታዘቡ ደግሞ ሳዳም ሁሴይንን ወይም ሙዓመር ጋዛፊን ላለመሆን መዘየዳቸዉን  ይጠቁማሉ።

እንነዚሕ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ሳዳም ጢማቸዉ ተጎትቶ ከተወሸቁበት ጉርጓድ የወጡት፤ ባደባባይ የታነቁት፤ሙዓመር ቃዛፊ ቁጥቋጦ ለቁጥቋጦ ሲሽሎኮሎኩ  ግንባራቸዉ በጥይት ተበርቅሶ የተደፉት የምዕራባዉያንን ልብ አራርተዉ በየሥልጣናቸዉ የሚቆዩ መስሏቸዉ የኑክሌር መርሐ-ግብራቸዉን ሳይቀር መነቃቅረዉ ኃይል-አቅማቸዉን በገዛ እጃቸዉ በመግደላቸዉ-አንድ፤ የገዛ ወገኖቻቸዉ አረቦች አጋልጠዉ ስለሰጧቸዉ-ሁለት ምክንያት ይሰጣሉ።

የኪም ጆንግ ኡንን ስልት በቅርብ እናዉቃለን የሚሉት ተንታኞች ኪም ነብስ ካወቁ በኋላ ሲሆን ካዩት፤ በሳዳም ወይም በቃዛፊ ላይ ከደረሰዉ መማራቸዉን አይጠራጠሩም።የኪም አስተሳሰብ፤ ዝንባሌ እና ስልት ግን ከቅርቦቹ አረቦች፤ ከሩቁ ጎርባቾቭም ይልቅ ለዴንግ ዢዮፒንግ የሚቀርብ ወይም የዴንግ ዢዮፒንግ ቅጂ ነዉ ባይ ናቸዉ።የደቡብ ምሥራቅ እስያ የፖለቲካ ሳይቲስት ጆን ዴላይ እንዲሕ ዓይነት እምነት ካላቸዉ አንዱ ናቸዉ።

                               

«ያሁኑ የኪም ጆንግ ኡን ስልት ቻይና በዴንግ ዢዮፒንግ በምትመራበት በ1970ዎቹ የነበረችበት ሁኔታ ያስታዉሰኛል።ቻይና ትኩረትዋን በሙሉ በምጣኔ ሐብቱ ላይ ያደረገችበት ወቅት ነበር።ማለቴ ኪም ጆንግ ኡን ምን ላይ እንዳሉ፤ወዴት መጓዝ እንደሚሹ፤ ጉዟቸዉ የሚሰምረዉ ወይም ኤኮኖሚዉ የሚያድገዉ ማዕቀቡ ሲነሳላቸዉ መሆኑን እንደሚያዉቁ፤ ለዚሕ ስኬት በኑክሌሩ ጉዳይ እንደሚደራደሩ መገመት ይቻላል።»

በ1978 የማኦ ዜዱግን ቅሪቶች ገፈታትረዉ የቻይናን የመሪነት ስልጣን የያዙት  ዴንግ ዢዮፒንግ፤ከ1960ዎቹ ጀምሮ «ድመቷ ጥቁር ሆነች ነጭ ትርጉም የለዉም፤ አይጥ እስከያዘች ድረስ ጥሩ ድመት ናት» በማለት የሚገልፁት ፍልስፍና ነበራቸዉ።«የትም ፍጪዉ ዱቄቱን አምጪዉ» እንዲል ሐበሻ።

Korea-Gipfel 2018 Umarmung Kim und Moon
ምስል Reuters

በዚያ ዘመን በጦር፤ ፖለቲካ የትልቂቱን ግን የደሐይቱን ሐገር ሥልጣን የተቆጣጠሩት ዴንግ ዡዮፒንግ ምጣኔ ሐብቷ እንዲዳብር የነፃ-ገበያን መርሕ ከኮሚንስቱ አስተምሮ ጋር ቀይጠዉ የቢሊዮኖቹን ሐገር ያሮጥዋት ገቡ።

የዴንግዋ ቻይና የግራዉን ፅንፍ ፖለቲካ ረገብ አድርጋ ምጣኔ ሐብቷን ለማሳደግ ደፋ-ቀና በምትልበት መሐል በ1985 የሶቬት ሕብረትን ኮሚንስት ፓርቲ የዋና ፀሐፊነት ሥልጣን የያዙት ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ለዉጥና ግልፅነት ማለታቸዉ አልቀረም ነበር።ይሁንና የግልፅነቱን ድካ ሳያዉቁ እነ ሮናልድ ሬገንን ኑክሌረን ተረከቡኝ እያሉ ሲወተዉቱ ኃያል ሐገራቸዉ ተበታትና ዳፋዉ ለሌሎችም ተረፈ።

የኪም ጆንግ ኡን አያት-አባቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ጦር ሠራዊት አደራጅተዋል።ጦሩን ከ2006 ጀምሮ የኑክሌር ቦምብ አስታጥቀዉታል።አጥፊዉን ቦምብ ተሸክሞ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ድረስ የሚምዘገዘግ ሚሳዬል ተክሏል።ይሕን ጦር እንደ ሳዳም በማዕቀብ ማላሸቅ፤ እንደ ቃዛፊ የኑክሌር መርሐ ግብራቸዉን መነቃቅረዉ  ማሽመድመድ፤ እንደ ጎርቫቾቭ መበታተን አልፈለጉም።እንደ ዴንግ ፈርጣማዉን ጦር እንደያዙ ምጣኔ ሐብቱን ላሳድግ አሉ እንጂ።

የዓለም ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች ሰዉዬዉን እንደ ጭራቅ ለሚስሏቸዉ ጠላቶቻቸዉን የሚሰጡትን ያክል ትኩረት አልሰጡትም እንጂ ወጣቱ መሪ፤ ሥለ ሰላም እና ምጣኔ ሐብት ዕድገት ማዉራት የጀመሩት የአባታቸዉን አልጋ በወረሱ ማግስት  ነበር።በተለይ ጥር 2013፤ የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ኢኮኖሚያችንን ለመገንባት መሠረታዊ ለዉጥ እናድርግ ብለዉ ነበር።ለደቡብ ኮሪያ ባስተላለፉት ጥሪ ደግሞ «በኮሪያዎች መካከል እስካሁን ያለዉ ጠብ እና ፍጥጫ የአንድ ሐገር ልጆችን ከሚፈጅ ጦርነት በስተቀር የፈየደዉ ነገር የለም።»ብለዉ ነበር።

የሰማ እንጂ ያደመጠ-የተቀበላቸዉም መንግሥት የለም።ፕሮፌሰር ዴላይ «ሥለ ኪም ብዙ የማናወራዉ ጉዳይ» ይሉታል።

                                         

«ደሕና ሥለ ኪም ጆንግ ኡን ለየት የሚለዉ ትልቅ ነገር እኛ ብዙ የማናወራላቸዉ ጉዳይ ነዉ።የሰሜን ኮሪያ ምጣኔ ሐብት። ኪም ጆንግ ኡንን ለስድት ዓመት ያጠና ሰዉ የሳቸዉን ዲስኩር፤ለሐገራቸዉ ህዝብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ሁሉ ምጣኔ ሐብት ግንባታ ላይ ያተኮረ ነዉ።ይሕ ጉባኤ ከመደረጉ ካንድ ሳምንት በፊት ባስተላለፉት መልዕክት እንኳን የኑክሌር መከላከያዉን እና የምጣኔ ሐብቱን ግንባታ ጎን ጎን እንደሚያስኬዱት አስታዉቀዉ ነበር።»

አስታወቁ ፓንሙንጆም ሔዱ።ከደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት ጋር የ65 ዓመቱን ጦርነት፤ ግጭት እና ፍጥጫ ለማስቆም ተስማሙ።ኪም በክብር እንግዳዉ መዝገብ ላይ «አዲስ ታሪክ አሁን ተጀመረ» የሚል ዓረፍተ ነገር ፃፉ።

አሮጌዉ ታሪክ በኮሪያዎች እንዳልተጀመረ ሁሉ አዲሱም ታሪክ መቀጠል አለመቀጠሉ በርግጥ የዋሽግተን-ቶኪዮ፤ የለንደን ብራስል ወዳጆችን፤ የቤጂንግ-ሞስኮ ተፎካካሪዎችን ይሁንታ ማግኘት ግድ ነዉ።ኪም ግን «እስካሁን ለምን አልጀመርነዉም?» ጠየቁ ባለፈዉ አርብ።

              

«ወደዚሕ ሥራመድ ያሰብኩት።ይሕን ያሕል ጊዜ ለምን ቆየ።እዚሕ ለመድረስ ምን አዳገተን? እያልኩ ነዉ።»

ቀጥታ መልስ ማግኘት በርግጥ ከባድ ነዉ።ያለዉ መልስ  ከ19440ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ የነበረዉ ታሪክ ነዉ።

እስከ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ድረስ ኮሪያን ይገዛ የነበረዉን የጃፓን ጦር በጋራ መትተዉ ያስወጡት ሶቭየት ሕብረት እና ዩናይትድ ስቴትስ አዉሮጳን «ምሥራቅ እና ምዕራብ» ብለዉ እንደከፈሉት ሁሉ ኮሪያንም ሰሜን እና ደቡብ ከፍለዉ ያዙ።በ1949 በሁለቱ ኃያላን እና በተከታዮቻቸዉ የሚደገፉት የፒዮንግዮግ እና የሶል ገዢዎች ዉጊያ ገጠሙ።

ጦርነቱ ለዩናትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ለሐሪ ኤስ ትሩማን የማኦ ዜዱንግ እና የስታሊን የመስፋፋት ደባ ዉጤት ዓይነት ነበር።

                              

Atomtests in Nordkorea
ምስል picture-alliance/dpa

ዩናይትድ ስቴትስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስም ከታላቅዋ ብሪታንያ እስከ ትንሿ ላክሰምበርግ፤ ከሐብታምዋ ካናዳ እስከ ደኃይቱ ኢትዮጵያ 15 ሐገሮችን አስከትላ ሰሜኖችን ለመዉጋት፤ ቻይና እና ሶቬት ሕብረት ከሰሜኖች ወግነዉ ደቡቦችን የሚወጋ ጦር አዘመቱ።አዲስ አበባ ላይ «እልም አለ ባቡሩ ሲዘፈን» የጦርነት ትቢያዉን  ያላራገፈዉ ዓለም ኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ይጨፋጨፍ ገባ።

ስድት መቶ ሺሕ ወታደር አለቀ።ከ2,5 ሚሊዮን በላይ ሰላማዊ ሕዝብ ረገፈ።የኮሪያ ልሳነ ምድር ለሁለት እንደተገመሰ ቀረ።ግጭት ቁርቁሱ ቀጠለ።እስካሁን ሠላም የለም።

የመጀመሪያዉ የሰላም ሙከራ የተደረገዉ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን በ1972 ቻይናን ሲጎበኙ ነበር።ኒክሰን እና ማኦ ዜዱንግ ሰላም ማስፈን እንደሚፈልጉ ተነጋግረዉ ነበር።ተናገሩ ቀረ።በ1975 ሌላዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር የ«ሰላም ሐሳብ አለኝ» ብለዉ ነበር።አሉ።በቃ።

የተሻለ ሙከራ የተደረገዉ በ2000 መጀመሪያ ነበር።1998 የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ሆነዉ የተመረጡት ኪም ዴ-ጁንግ «የፀሐይ ነፀብራቅ» ያሉት መርሕ ከያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ከቢል ክሊንተን ጠንካራ ድጋፍ በማግኘቱ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

ኪም ዴ ጁንግ በ2000 ፒዮንግዮንግ ድረስ ሔደዉ ከከኪም ጆንግ ኡን አባት ከኪም ጆንግ ኢል ጋር ያደረጉት ስምምነት ሁለቱን ኮሪያዎች በምጣኔ ሐብት ማስተሳሰር፤ በቀጥታ የስልክ መስመር ማገናኘት ከሁሉም በላይ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር መርሐ-ግብር ማስቆም አስችሎ ነበር።

ጆርጆ ቡሽ የሚባሉ የቴክሳስ ሰዉ  ዋይትሐዉስ ገቡና ሰሜን ኮሪያን ከኢራቅ እና ኢራን ጋር ደብለዉ «የሰይጣን ዛቢያ» እያሉ ሲፎክሩ የነበረዉ ሁሉe እንዳልነበር ሆነ።ቡሽ «የስድስትዮሽ» ይባል የነበረዉን ድርድር ፍርክስክሱን ባወጡት በሰወስተኛ ዓመቱ ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያዉን የኑክሌር ቦምብ በይፋ ሞከረች።2006።

Südkorea Militärmanöver 14.02.2013
ምስል Reuters

ሰሜን ኮሪያ የመጨረሻዉን እና ትልቁን የሐይድሮጂን ቦምብ የሞከረችዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቡሽዋ የሰይጣን ዛቢ ላይ «ዓለም አይቶት የማያዉቀዉን እቶን እና መዓት» ለማዉረድ በዛቱ በወሩ ነበር።መስከረም 2017።ለጦርነት የሚዛት፤የሚፎከር፤ ኑክሌር ቦምብ የተደገነበት የኮሪያ ልሳነ-ምድር በዘጠኛ ወሩ አርብ ሰላም ይነገር፤ይደሰኮር፤ ይዘመርበት ይዟል።የዓለም ኃያላንም ዲስኩር መዝሙሩን እያስተጋቡ ነዉ።ቃል ገቢር ይሆን-ይሆን? መቼ? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ