የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ግምገማ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 4 2016ለሁለት ዓመታት ይካሄድ የነበረውን ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶርያውን ውል በአደራዳሪነት ያፈራረመው የአፍሪካ ሕብረት፥ ሁለተኛ ዙር የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ሂደት ስትራቴጂክ ግምገማ የስምምነቱ ፈራሚዎች በተገኙበት ማክሰኞ በሕብረቱ ፅሕፈት ቤት ማካሄዱን አስታውቋል። የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ፣ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ሐላፊ አምባሳደር ባንኮሌ የጦርነቱን ተፈናቃዮች መልሶ ለማቋቋም እና የታቀደውን የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ስራ ለመተግበር የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀምና ትችቱ
በአፍሪካ ሕብረት አዘጋጅነት በህወሓት እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ታዛቢዎች መካከል ስለተደረገው የውሉ አፈፃፀም ግምገማ ዙርያ የፃፉት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በውይይቱ ተፈናቃዮች በመመለስ ዙርያ ሐሳቦች መነሳታቸውን፣ የተጀመረው ተፈናቃዮችን የመመለስ ተግባር እውቅና የሚሰጠው መሆኑን የገለፁ ሲሆን ሂደቱ እንዲጠናከርና ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉትንም እንዲያጠቃልል መግባባት መደረሱ አመልክተዋል። የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባራት እንዲሁም የህወሓትን ሕጋዊነት የማረጋጋት አጀንዳዎችም የሁለተኛው የፕሪቶርያ ውል አፈፃፀም ርእሶች እንደነበሩ አቶ ጌታቸው ገልፀዋል። በዚህ የግምገማ መድረክ ዙርያ ከህወሓት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ግምገማ
ከትግራይ ሊሂቃን በኩል ግን በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ዙርያ ጥያቄ እና ወቀሳዎች ይነሳሉ። ሐሳባቸውን ያጋሩን የሕግ ሙሁር አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ፥ የሰላም ውሉን አፈፃፀም ለመገምገም በረዥም ግዜ ከሚደረግ ስብሰባ ምንም እንደማይጠበቅ፣ ይልቁንስ የውሉን አፈፃፀም ለመቆጣጠር የተቋቋመው አካል ስራውን እየሰራ እንዳልሆነ ማሳያ መሆንኑ ያነሳሉ።
የሕግ ምሁሩ አቶ ሙስጠፋ ጨምረውም ለሰላም ስምምነቱ ዘላቂነት የውሉን ሁሉንም ነጥቦች በትክክል መፈፀም እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ።ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት የፖለቲከኞች አስተያየት
ከተፈረመ 20 ወራት ያለፈው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት፥ በአፈፃፀሙ ላይ የተለያዩ አካላት ትችት ያቀርባሉ። በትግራይ የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚው ፓርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በተለይም ተፈፃሚ እየሆነ ነው ተብሎ በሁለቱ የውሉ ፈራሚዎች የተገለፀው ተፈናቃዮች የመመለስ ተግባር፥ ለፕሮፖጋንዳ አልያም ለፖለቲካ ትርፍ ካልሆነ የሚጠበቀው ደረጃ እየተፈፀመ አይደለም ብለዋል።
የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ከፍተኛ አመራር አቶ ኪሮስ ኃይለስላሴ " ተፈናቃዮች እንመልሳለን የሚል ለዲፕሎማሲያዊ፣ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል የሚደረግ ነገር አለ። መሬት ላይ ግን ማስተጓጎል እና ተፈናቃዮች የመመለስ ስራ እውን እንዳይሆን ማድረግ ነው" ብለዋል።በማክሰኞው የፕሪቶርያ ውል አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ዙርያ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የተባለ ነገር የለም።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ