1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምዕራብ ወለጋ አንዳንድ ወረዳዎች ኤሌክትሪክ እንደተቋረጠ ነው

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2016

በአሶሳ፣ ቤጊና ጊዳሚ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠ 2 ሳምንት ሆኖታል ።በአሶሳና አካባቢው እንዲሁም በምዕራብ ወለጋ ዞን ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠ ሁለት ሳምንት አስቆጥሯል ።

https://p.dw.com/p/4i3d6
 power transmission tower in West Wolega zone Manasibu district
ምስል Negassa Desalegn/DW

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠ ነው

በአሶሳ፣ ቤጊና ጊዳሚ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠ 2 ሳምንት ሆኖታል ። በአሶሳና አካባቢው እንዲሁም በምዕራብ ወለጋ ዞን ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠ ሁለት ሳምንት አስቆጥሯል ። በዚህ አካባቢ በከፍተኛ ኃይል አስተላላፊ መስመር ላይ በደረሰው ጉዳት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ ተገልጿል ። በተለይም በአሶሳ እና አሶሳ ዞን ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሪክ ተቋርጦ የሚገኝ ሲሆን በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩን ያነጋርናቸው ነዋሪዎች አመልክተዋል ። መስመሩን የሚያስተዳድረው  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እስካሁን ስለ ጉዳዩ ያለው ነገር የለም ። 

ከፍተኛ መስመር ተሸካሚ ማማዎች ላይ ጉዳት ደርሷል

ከሰኔ 17 ቀን፣ 2016 ዓ.ም አንስቶ የኤሌክትሪክ ኃይል በአሶሳ እና አካባቢው፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊና ቆንዳላ ወረዳዎች እንዲሁም  በቄሌም ወለጋ ዞን  ጊዳሚ ወረዳ ተቋርጧል ። በዚህ አካባቢ ተቋርጧል የተባለው የአሌክትሪክ ኃይል በምዕራብ ወለጋ ዞን ማናስቡ በተባለ ወረዳ ውስጥ በከፍተኛ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመር ላይ ጉዳት መድረሱንና መስመር ተሸካሚ ማማ በመውደቁ እንደሆነ ያነጋርናቸው አንድ ነዋሪ ገልጸዋል ። የማናስቡ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ነዋሪ በአንድ አካባቢ የወደቁ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ማየታቸውን በመግለጽ በአሁኑ ወቅት አጎራባች በሆኑ ቤጊ፣ ቆንዳላና ጊዳሚ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ገልጸዋል ።

በአካባቢው ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠ ነው

በአሶሳና አካባቢው ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ የሚገኝ ሲሆን፤ ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትና ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል ። አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪዎች እንደሚሉት የመብራት ኃይል መቋረጥን ተከትሎ የእህል ወፍጮ ዋጋ እና በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪዎች መታየታቸውን አመልክተዋል ።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠ ነው
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠ ነውምስል Negassa Desalegn/DW

በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እየደረሰ እንደሚገኝ ያነጋርናቸው ነዋሪዎች ሀሳባቸውን አጋርተውናል ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠቀሱት አካባቢዎች የተቋረጠውን ሐይል አስመልክቶ እስካሁን ያለው ነገር የለም ። ስለ ጉዳዩ ማብራርያ የጠየቅናቸው መስመሩን የሚስተዳድረው በነቀምቴ ከተማ ውስጥ የሚገኙው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል  ምዕራብ ሪጅንም መስመር ወድቃል ከማለት ውጪ ስጉዳዩ ዝርዝር መረጃ መስጠት አለፈለጉም ። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከሁለት ቀን በፊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት በኃይል ተሸካሚ መስመር ላይ በሚደርስ ጉዳት ምክንያት መብራት ኃይል መቋረጡን ዐሳውቋል ። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችሉ አማራጮች ላይ ከፌደራል መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ እንደሚገን የክልሉ መንግስት ገልጸዋል ።

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ