1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሞዛምቢክ፦ የራፕ አቀንቃኙ ሞት የቀሰቀሰው ነውጥ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 23 2015

ሞዛምቢክ ውስጥ ታዋቂ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ የቀብር ሥርዓት ላይ ፖሊስ ለቀስተኞችን ያስተናገደበት ሁኔታ በርካቶችን አስቆጥቷል ። የሀገሪቱ ወጣቶች አደባባይ ወጥተው ከፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል ። ሁኔታው ወደ ጸረ መንግሥት ተቃውሞ እየተቀየረ ነው ። ወጣቶቹ ፖሊስ ፈቀደም አልፈቀደ ሰልፎችን ማድረጋቸውን እንደሚገፉበት ዝተዋል ።

https://p.dw.com/p/4PZWj
Mosambik | Beerdigung Rapper Azagaia
ምስል Madalena Sampaio/DW

የፖሊስ ርምጃ ወጣቶቹን አስቆጥቷል

ሞዛምቢኪያዊው የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ አዛጋያ በሀገሩ ሞዛምቢክ በርካታ አፍቃሪዎች አሉት ። ዝናው ግን በሌሎች የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ የአፍሪቃ ሃገራትም የናኘ ነው ። በተለይ በፖርቹጋልኛ "Povo no Poder" ሲል ያቀነቀነው «በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች» የተሰኘው ዜማው እጅግ ይወደድለታል ።

«ወጪው ጣራ ነካ፤ ገቢ እንዳሽቆለቆለ ። ይሄም መንግሥት መታደጉን አልቻለ ። አስለቃሽ ጢስ ጭናችሁ ብትመጡ፤ ይቀጥላል ተቃውሟችን በብርቱ ። እንዲያው እነሱም ሊያቆሙን አይችሉ፤ ሰዎች በሥልጣን ላይ ያሉ ። ሰዎች በሥልጣን ላይ ያሉ ።»

ይህ ዜማ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2008 ለአድማጭ በደረሰበት ወቅት ወጣቶች ጣራ በነካው የቤንዚን እና የነዳጅ ዋጋ የተነሳ ተቃውሞዋቸን መንግሥት ላይ ለማስተጋባት አደባባይ ሲወጡ እንደመፈክር ያስተጋቡት የነበረም ነው ። በዚህ ዜማ ብቻም አይደለም አቀንቃኙ አዛጋያ የሚታወቀው ። የቀድሞ በማርክስ እና ሌኒን ርእዮተ ዓለም ይመራ የነበረው የፍሬሊሞ (FRELIMO)መንግሥት ፖለቲከኞች አብዮቱን ከሕዝቡ መንትፈው ለተንደላቀቀ ሕይወት መምሪያ ተጠቀሙበት እያለ በተደጋጋሚ ይተችም ነበር ።

ይህ ዝነኛ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ባለፈው ወር መጨረሻ የካቲት 30 ቀን፤ በ38 ዓመቱ ከሚጥል በሽታ ጋር በተያያዘ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል ። የአዛጋያስ ድንገተኛ ሞት በመላው ሞዛምቢክ ብርቱ ሐዘን ነው ያጫረው ። በሁሉም የሞዛምቢክ ትልልቅ ከተሞች ማለት በሚቻል መልኩ ለዚሁ ዝነኛ አቀንቃኝ ዝክር እና የሻማ ማብራት እንዲሁም ለክብሩ ሰልፍ ተደርጓል ። በእርግጥ ቆንጣጭ ዘፈኖቹ በመንግሥት ዘንድ ወትሮም አይወደድለትም ነበር ። እንደውም የአዛጋያ ዘፈኖች በመንግሥት የመገናኛ አውታሮች እንዳይደሙጡ እገዳ የተጣለባቸው ናቸው ። «ፖቩ ኖ ፑዴር» የተሰኘውን ዘፈኑን ለአድማጭ ካደረሰ በኋላ የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዝነኛውን አቀንቃኝ ነውጥ ቀስቃሽ በሚል ከሶት ነበር ።

የአዛጋያን ሞት ተከትሎ ወጣቶች በሞዛምቢክ የተለያዩ ትልልቅ ከተሞች ማለትም፦ በማፑቶ፣ ቤይራ፣ ቄሊማኔ እና ናምፑላ የሐዘን ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ አስተላልፈው ነበር ። ሰልፉ በአራቱም ከተሞች በፀጥታ ኃላፊዎች ፈቃድ አግኝቶም ነበር። ሆኖም ግን ከሁለት ሳምንት በፊት፤ ቅዳሜ መጋቢት 9 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ለአዛጋያ ክብር በተደረገው ሰልፍ ወጣቶችን የሚያበሳጭ ክስተት ተፈጥሯል ። ማፑቶ ከተማ ውስጥ የሀገሪቱ ልዩ ኮማንዶዎች ቅዳሜ ማለዳ ላይ የሐዘን ሰልፉ የሚጀምርበትን ስፍራ ይዘጋሉ ። የተቆጡ ወጣቶችም፦ «አትነሳም ወይ» ማለት ይጀምራሉ ። የሞዛምቢክ መንግሥት የሚጠላውን የአዛጋያ «በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች» ማለትም «ፖቩ ኖ ፑዴር» የተሰኘውን ዜማ እንደመፈክር ያስተጋባሉ ። ጸረ መንግሥት እና የፀጥታ ኃይላት መፈክሮችንም ያሰማሉ ። ፖሊስ ወጣቶቹን ለመበተን የአስለቃሽ ጢስ ይተኩሳል፤ ኃይል ይጠቀማል ።

ወጣት ሞዛምቢኪያውያን በኑሮ ውድነት የተነሳ ለተቃውሞ አደባባይ በወጡበት ወቅት
ወጣት ሞዛምቢኪያውያን በኑሮ ውድነት የተነሳ ለተቃውሞ አደባባይ በወጡበት ወቅትምስል Da Silva Romeu/DW

ከዚያ አንድ ቀን ቀደም ብሎም በአዛጋይ የቀብር ስነስርዓት ላይ ወጣቶች የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ አስክሬን ሳጥንን የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ወደሚኖሩበት ፖንታ ቬርሜላህ ለመውሰድ ሲሞክሩም ሁኔታው እጅግ ተባብሶ በርካቶች በፖሊስ ድብደባ ቆስለው ነበር ። የፖሊስ ቃል አቀባይ ፌርናንዶ ቱስካና ።

«የሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ፖሊስ የሰልፉ አዘጋጆች የቀብር ታዳሚው አቅጣጫ ቀይሮ ሌላ መንገድ እንዲይዝ በማድረግ ሆን ብለው ነገሮችን ሲያባብሱ አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድ እና ወደ ቦታው መሄድ ነበረበት ። ወጣቶቹ ሰልፈኞች ሰልፋቸውን እንዲያቆሙ ጠይቀናቸዋል ።»

በዚህ ትርምስ እና የፖሊስ ድብደባ ማፑቶ ከተማ ውስጥ ብቻ ቢያንስ 19 ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ። ሁለቱ ብርቱ ድብደባ ነው የገጠማቸው ። የሰልፉ አዘጋጆች ፖሊስ ያልታጠቀ መሬት ላይ የተኛ ወጣትን በብርቱ ደብድቦ ወደ ፖሊስ ተሽከርካሪ ለመጫን መሬት ለመሬት ጎትቶታል ብለዋል ። ከሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴዎች አንዷ የሆነችው ሲንዲያ ክሪስቱንጎ በእለቱ ፖሊስ ያልተገባ ኅይል መጠቀሙን ገልጣለች።

የሰልፉ አዘጋጆች ፖሊስ ኃይል የተቀላቀለበር ርምጃ መውሰዱን ይናገራሉ
የሰልፉ አዘጋጆች ፖሊስ ኃይል የተቀላቀለበር ርምጃ መውሰዱን ይናገራሉምስል Sebastião Arcénio/DW

«የትኛውም ወጣት ማንኛው ዜጋ ኃይልን አልተጠቀመም ። ይህን ክስ የሚያረጋግጥ የሆነ ቪዲዮ ካለ ቢያሳዩን ደስ ይለናል ። ዓርማችን አመጽ አልባ ነበር እንደዚያም ሆኖ ይቆያል።»

እንደ ፖሊስ መረጃ ከዚሁ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በመላ ሞዛምቢክ 36 ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ 20ዎቹ ከማፑቶ ከተማ ናቸው ።  ወጣቶቹ ፖሊስ ፈቀደም አልፈቀደ እጅግ እየወደዱት ላጡት የጥበብ ሰው አዛጋያ ክብር የዝክር ሰልፎችን ማድረጋቸውን እንደሚገፉበት ዝተዋል ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ/አንቶኒዮ ካሽካሽ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር