1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሞዛምቢክን ያሸበረው ጥቃት

ቅዳሜ፣ መስከረም 7 2015

ሞዛምቢክ ከባለፈው ሳምንት ሽብር በቅጡ ያገገመች አትመስልም። በሰሜናዊ ሞዛምቢክ፤ ደረቷን ወደ ሰፊው የሕንድ ውቅያኖስ ገልብጣ ለተቆረቆረችው የናምፑላ አውራጃ አነስተኛዋ የወደብ ከተማ ናካላ ያለፈው ሳምንት ሽብር ጥላውን እንዳሳረፈባት ነው። በከተማዪቱ በሚገኘው የመነኮሳት ማደሪያ መናኒያቱ ያልጠበቁት አስደንጋጭ የሽብር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

https://p.dw.com/p/4Gztx
Mosambik | zerstörte Häuser in Mecula
ምስል Privat

አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል

ሞዛምቢክ ከባለፈው ሳምንት ሽብር በቅጡ ያገገመች አትመስልም። በሰሜናዊ ሞዛምቢክ፤ ደረቷን ወደ ሰፊው የሕንድ ውቅያኖስ ገልብጣ ለተቆረቆረችው የናምፑላ አውራጃ አነስተኛዋ የወደብ ከተማ ናካላ ያለፈው ሳምንት ሽብር ጥላውን እንዳሳረፈባት ነው። በከተማዪቱ በሚገኘው የመነኮሳት ማደሪያ መናኒያቱ ያልጠበቁት አስደንጋጭ የሽብር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። የናካላ ከተማ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አቡን አባ ዶም አልቤርቶ ቬራ ከምሽቱ ሦስት ሰአት ላይ ስለተፈጸመው ግፍ ለዶይቸ ቬለ እንዲህ ያብራራሉ።

«ከምሽቱ 3 ሰአት አካባቢ አምስት አለያም ስድስት አሸባሪዎች ወደ መናንያቱ ማደሪያ ድንገት በኃይል ጥሰው ገቡ። እዚያም በእድሜ የገፉት ሁለቱ መነኮሳት ነበሩ። ጣሊያናዊቷ እማሆይ ማሪያ ጭንቅላታቸው ላይ ተተኩሶባቸው ነው የሞቱት። ሌላኛዋ ስፔናዊት መነኩሲት በእርግጥ ማምለጥ ችለዋል። እጓለ ምውታን ልጃገረዶቹንም ያስጠነቀቋቸው እሳቸው ናቸው። እግዚአብሔር ይመስገን እሳቸው ወደ ጫካው ሮጠው አምልጠዋል።»

BG Mosambik | Alltag und Militarismus in Cabo Delgado
ምስል Roberto Paquete/DW

የሽብር ጥቃቱ በከተማዪቱ የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ነበር። ጥቃት አድራሾቹ ደግሞ አህሉ-ሱናህ ዋል ጃማኣ (ASWJ)የተሰኘው እና ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ በሚጠራው ቡድን ሞዛምቢክ ውስጥ ድጋፍ የሚደረግለት ታጣቂ ነው ተብሏል። 

የእድሜያቸውን ሲሶ ሞዛምቢክ ካሳለፉት ከ83 ዓመቷ ጣልያናዊት መነኩሲት ባሻገር በዚያኑ ቀን እዛው ገዳም ውስጥ ሌሎች ሁለት ሰዎችም በአሸባሪ ቡድኑ ተገድለዋል። ጥቃት የደረሰበት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ገዳም ከሃይማኖታዊ ትምህርቶች ባሻገር የተለያዩ በርካታ የርዳታ ፕሮጄክተች የሚከወኑበት እንደሆነም ይነገራል። 

በርካታ የሞዛምቢክ ቋንቋዎችን የሚያውቁት እማሆይ ማሪያ ገዳዮቻቸውን ለማናገር ሞክረው ነበር ይላሉ አቡነ ዶም አልቤርቶ ቬራ። «ያ ግን ምንም አልጠቀማቸውም» ሲሉም ሐዘናቸውን ገልጠዋል።  ሌላኛዋ በእድሜ የገፉ መነኩሲት ግን ወደ ጫካው ሸሽተው ከማምለጣቸው በፊት ገዳሙ ውስጥ የነበሩ 12 እጓለ ምውታን ልጃገረዶችንም ማስጠንቀቅ ችለዋል። ማስጠንቀቅ ብቻም አይደለም ልጆቹን ይዘው ወደ ጫካው መሸሽ ተሳክቶላቸዋል ብለዋል አቡኑ።  

መሸሽ ያልቻሉ ሌሎች ሰዎች ግን የአሸባሪዎቹ ጭዳ ሆነዋል። የሞዛምቢክ ርእሰ ብሔር ፊሊፔ ንዩሲ በአሰቃቂ መልኩ የተገደሉ እና ተጠልፈው የደተወሰዱ እንዳሉ አረጋግጠዋል። 

Filipe Nyusi, Präsident von Mosambik
ምስል DW

«ስድስት ሰዎች አንገታቸው ተቀልቷል፤ ሦስት ደግሞ ተጠልፈው ተወስደዋል። በዐሥራዎቹ የሚቆጠሩ ቤቶች ላይም እሳት ተለቆባቸዋል።» 

ሞዛምቢክ ውስጥ ለቀጠለው ግጭት፤ ሽብር እና ግድያ ሰበቡ ከእምነት እና ርእዮተ ዓለም ባሻገርም የማኅበራዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮችም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ባለሞያዎች ይናገራሉ። የሞዛምቢክ እምቅ የተፈጥሮ ሐብት ፍትኃዊ በሆነ መልኩ ለኅብረተሰቡ አልተከፋፈለም የሚሉ ድምፆችም በእየ ጊዜው ሲያስተጋቡ ይደመጣል። 
የናካላ ከተማ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አቡን አባ ዶም አልቤርቶ ቬራ፦ በግጭት ጥቃቱ ለተፈናቀሉ እና ቤተሰቦቻቸውን ላጡ የሚያደርጉትን ርዳታ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያናቸውም ተግባሯን በአዲስ መልክ ማደራጀት እንደሚያስፈልጋትም አስገንዝበዋል። ከምንም በላይ ግን የእለት ጉርስ የሚሹ በርካታ ተፈናቃዮች ስላሉ ለእነሱ ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል።  በገዳማቸው የተከሰተው ሽብር ሰላም ያጣችው የጎረቤት አውራጃ ካቦ ዴልጋዶ ነጸብራቅ መሆኑን በመግለጥ ጥቃቱ ሊደጋገም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። 

«እዚህ የሆነው ከረዥም ጊዜ አንስቶ ካቦ ዴልጋዶ ውስጥ ሲያሸብር የሰነበተው ጦርነት ቀጣይ ነው። ከአንድ ሳምንት በፊት ካቦ ዴልጋዶ ውስጥ የተቆጡት እነዚያኑ አሸባሪዎች ናቸው ወደ ናምፑላ አውራጃ ናካላ የመጡት። በየኼዱበትም ነዋሪው ላይ ሽብር መንዛት ማስፋፋት ነው ሥራቸው።» 

Mosambik Cabo Delgado | Terroranschlag | Kirche
ምስል privat

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህም ካቦ ዴልጋዶ የተሰኘችው አውራጃ የአሸባሪዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ዒላማ መሆኗ ቀጥሏል። እንደ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR)ከኾነ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ካቦ ዴልጋዶ ውስጥ ይኖራል። የፀጥታ እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ደግሞ ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎች እዛው አካባቢ በተፈጠረ ተደጋጋሚ ጥቃት መገደላቸውን መዝግቧል።  

አንቶኒo ካሽካሽ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ