1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

በባሏ «የተገደለችው» ሴት አስከሬን ከ28 ቀናት በኋላ ተገኘ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 24 2017

ጥርጣሬው የተጀመረው ዳላቻ አለጌ ከተባለ ባለቤቷ ንግግር ነው ይላሉ፡፡ «የገደላት ሌሊት ላይ ነው፡፡ ከገደላት በኋላ በዚያው በቄያቸው ደጃፍ የሆነ ቦይ ውስጥ ቀበሯት፡ ይሄን የሚለው መቼም ሰው መግደል ለአንድ ሰው የሚሳነው ባይሆንም ያለ ሰው እገዛ ግን አንድን አስከሬን ብቻውን አውጥቶ መቅበር ስለሚከብድ ነው።»

https://p.dw.com/p/4olSt
በገዳይነት የተጠረጠረዉ ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በአባሪነት የሚጠረጠሩ ሰዎችም እንዳሉ የሟች ቤተሰቦች አስታዉቀዋል
ቡልቡሊ ቀበሌ ደካ አርባ በምትባል ልዩ ስፍራ የሚኖረዉ ግለሰብ ባለቤቱን ገድሎ ባካባቢዉ በሚገኝ ቦይ ዉስጥ እስከሬንን መጣሉን የሟች ዘመዶች አስታዉቀዋል።ምስል Seyoum Hailu/DW

በባሏ “የተገደለችው” ሴት አስከሬን ከ28 ቀናት በኋላ ተገኘ

 

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ጉሚየልደሎ ወረዳ «በባሏ ተገደለች» የተባለች ሴት አስከሬን ከተጣለበት ጉርጓድ ከ28 ቀናት በኋላ ወጥቶ ተቀብሯል፡፡የሟች ቤተሰቦች የተፋጠነ ፍትህን ጠይቀዋል። የአከባቢው ባለስልጣናትም ፍርድ እናሰጣለን ብለዋል፡፡

ዱባ ሊባን ሀላኬ በምስራቅ ቦረና ዞን ጉሚየልደሎ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ደኮሌ ሊባን የተባለች የ30ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ እህቱ የሁለት ልጆች እናት፤ በዚሁ ወረዳ ቡልቡሊ ቀበሌ ደካ አርባ በምትባል ልዩ ስፍራ እንዴት ተገድላ ተገኘች የሚለውን ለዶቼ ቬለ ሲያስረዱ ጥርጣሬው የተጀመረው ዳላቻ አለጌ ከተባለ ባለቤቷ ንግግር ነው ይላሉ፡፡ “የገደላት ሌሊት ላይ ነው፡፡ ከገደላት በኋላ በዚያው በቄያቸው ደጃፍ የሆነ ቦይ ውስጥ አውጥተው ቀበሯት፡ይሄን የምለው መቼም ሰው መግደል ለአንድ ሰው የሚሳነው ባይሆንም ያለ ሰው እገዛ ግን አንድን አስከሬን ብቻውን አውጥቶ መቅበር ስለምከብድ ነው፡፡ ለዚያ ነው እኛ እንደ ቤተሰብ ከዋናው ተጠርጣሪው በተጨማሪ ከቤተሰቦቹ ቅሬታ የምኖረን” ሲሉ ስለ እህታቸው በባለቤቷ መገደል በቁጭት የምናገሩት፡፡

«ከቤት ከወጣች 28 ቀናት ሆኗታል»

አስተያየት ሰጪው የሟች ወንድም ቀጠሉ፤ የጥርጥሬያቸው መነሻ የሆነውንም ስያስረዱ ህዳር 07 ቀን 2017 ዓ.ም. ባል ወደ ሟች ሴት ቤተሰብ በመገስገስ አንድ ማስተባበያ ለማቅረብ ጣረ፤ “እኔ ደኮሌን ከጣኋት ቆየሁ ቤተሰቦቼ ጋ እሄዳለሁ ብላ ከወጣች ዛሬ 28 ቀን ደፍኗል ሲል እሷን በገደላት 28ኛ ቀን መጥቶ ነገረን፡፡ እስኪ ተቀመጥ ስባልም አልቀመጥም አለ፡፡ ይህ ንግግሩ በአባታችን ዘንድ ከፍተኛ ጥያቄ ፈጠረ፡፡ እንዴት ባል የጠፋች ሚስቱን 28 ቀናት ሁሉ ቆይቶ ይፈልጋል በሚል፡፡ በዚህ መሃል ወዴት ናት ብለው ከቤተሰቦቹ እንኳ አንዳቸውም እሷን ፍለጋ ወደእኛ አልመጡም፡፡ እናም አባታችን ለህግ አካላት ጥቆማ በመስተቱ ከሁለት ቀናት በኋላ እሱ ለመጥፋት በምዘጋጅበት ወቅት በጥቆማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ እኛ ልጃችንን መፈለግ ተያያዝን፡፡ የቦረና ህዝብ ከኛ ጋር ወጣ፡፡ ከህዳር 09 የጀመርነው ፍለጋ በህዳር 13 አንድ ጥቆማ ከአከባቢው ደረሰን፡፡ በዚህ አከባቢ ገና ሳይመሽ እቆፈረ ነበር የሚል፡፡ እናም ቦታው ላይ ሄደን ስንፈትሽ የተቀበረ አስከሬኗን አገኘን፡፡ ህዳር 14 ቀን የጸጥታ አካላት፣ ህዝብ እና ቤተሰቦቿ በተገኘንበት ህርማችን አውጥተን በወጉ ስራተቀብር ፈጸምን” ብለዋል፡፡

ተጠርጣሪው የእህታቸው ባልህዳር 09 በህግ ጥላ ስር ከዋለ በኋላ ከሱም በተጨማሪ እሷ የድረሱልኝ ጩኸት ስታሰማ ያልደረሱላትም በአጠገባቸው የሚኖሩትን በወንጅል ተባባሪነት ተጠርጥረው እንዲያዙ ባቀረብነው ጥሪ መሰረት ለጊዜው ብያዙም መረጃ አልተገኘባቸውም በሚል መለቀቃቸውን የሟች ወንድም ገልጸውልናል፡፡ እህታቸው ለተጠርጣሪው ሁለተኛ ሚስት መሆኗን የሚገልጹት ወንድም የ7 ኣመት ወንድ ልጅ እና የ5 ዓመት ሴት ልጅ እናትም እንደነበረች አስረድተዋል፡፡ በሟች እና ተጠርጣሪው መሃል የንብረት ክርክር እና መካሰስ እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

የሕግ ክትትሉ ያለበት ደረጃ

የወንጀሉን መፈጸም አረጋግጠውልን ዋና ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር እንደሚገኝ የገለጹልን የምስራቅ ቦረና ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሹኬ ጎዳና ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን በማስረዳት ሌሎች ስድስት ተጠርጣሪዎች በዋስ የተለቀቁበትን ምክንያት ነግረውናል፡፡ “በተርጣሪነት ጉዳዩ ስፈጸም የትነበራችሁ በሚል የተያዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ እስካሁን ተጠርጣሪው እናቴን አዝሏት ነው የወጣው በሚል በሰባት ኣመት ህጻን ከተነገረ ውጪ በትልቅ ሰው በይፋ የተሰጠ ነገገር ስለሌሌ ባለሙያዎች ምርመራቸውን አጠናቀው አላሳወቁንም፡፡ የተለቀቁት ላይ መረጃ ከተገኘ ግን ተመልሰው የማይታሰሩበት ምክንያት የለም” ብለዋል፡፡

ድርጊቱ በአከባቢው ባህል እንዴት ይወገዛል?

በአከባቢው ባህል ሴት ላይ እንዲህ ያለ ጭካኔየተሞላበት በደል አስነዋሪ ነው የሚሉት የምስራቅ ቦረና ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ድርጊቱ የአከባቢውን ማህበረሰብ እንደማይገልጽ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በፊትም በዚሁ ዞን ሚስቱን በአደባባይ እንጨት ላይ አስሮ የገረፋትን ጨምሮ ተባባሪዎቹን ፍርደኞች በማስታወስ እንዲህ ያለ ነገር ለምን በአከባቢው ተደጋገመ የምለውን ጥያቄ ለቦረና አባገዳ ኩራ ጃርሶ አቅርበናል፡፡ እሳቸውም “ቦረና ለሴት ልጅ ትልቅ ስፍራ ነው የሚሰጠው፡፡ ጥፋት እንኳ ብኖር በጎሳ ታይቶ መግባባት ላይ ካልተደረሰ ወደ ፊቺ ይኬዳል እንጂ አሁን ተደጋግሞ እየታዬ ያለው ነገር በቦረናም ሆነ በገዳ ስርዓታችን የሚወገዝ ነው፡፡ ከባህል ውጪም ነው እንደዛ ነው የምናየው” ሲሉ መልሰዋል፡፡

ዘላቂ መፍትሄውስ ምንድነው?

እየተደጋገመ የመጣው አሰቃቂ የሴት ልጅ ጥቃት አሳሳቢ ነው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡን የስነጾታ ባለሙያ ሕቢቴ ተስፋዬ፤ “ስሜታችን እንዴት እንቆጣጠር የሚለው ጉዳይ ላይ ብዙ መስራት ያለብን ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ለግጭት መንስኤ ይኖረዋል፡፡ ግን ያንን በንግግር ብቻ እንዲፈታ ህብረተሰባችንን ብዙ ማስተማር ያለብን ይመስለኛል” በማለት መፍትሄ ላሉት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ