1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአለፈው ጦርነት ሕይወታቸው ያለፉት ለቤተሰቦችቻቸው መርዶ እየተነገረ ነው

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 2016

"እኛ፣ እኔን ጨምሮ እንደመሪዎች ምን ስላደረግን ወይም ምን ስላላደረግን፣ ስለምን ይህ ሁሉ ገጠመን ብለን ልንጠይቅ፣ ንስሃ ልንገባ፣ ይህ የገጠመን መከራ እና መስዋእትነት እንዳይደገም ብለን ውስጣችን ልንፈትሽ ለህዝባችን ቃል ልንገባ ግድ ነው" አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንት

https://p.dw.com/p/4XXPo
Äthiopien Tigray Mekelle | Nationaler Trauertag für die Toten des Krieges
ምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ የ3 ቀናት ክልላዊ ሃዘን ታወጀ

በጦርነቱ ወቅት ያለፉ  የትግራይ ሐይሎች አባላት መርዶ ለቤተሰቦች በይፋ ተነገረ። ከዛሬ ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚቆይ ክልላዊ የሃዘን ቀናትም ታውጃል።ይህን ተከትሎ በመላው ትግራይ ከፍተኛ የሐዘን ስሜት ነግሷል። በመቐለ ሁሉም አብያተ ክርስቲያን ለተሰዉት  ታጋዮች የፍትሓት ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ከንጋት ጀምሮ የተካሄደ ሲሆን፥ የተረዱ ቤተሰቦችም ተሰባስበው ሐዘናቸው ሲገልፁ ተስተውሏል። ከዚህ በተጨማሪ ዛሬ ጠዋት በመቐለ የሰማእታት ሐወልት ቅጥር ግቢ በነበረ ስነስርዓት የክልሉ አስተዳደር መሪዎች፣ የሰማእታቱ ቤተሰቦች እና ሌሎች በተገኙበት የህሊና ፀሎት፣ የአበባ ጉንጉን ማኖርና ሌሎች ይፋዊ የሐዘን መግለጫ መርሐግብሮች ተከናውኗል።

በጦርነቱ ያለፉ  የትግራይ ሐይሎች አባላት፥ ቤተሰቦች መርዶ ከደረሳቸው በኋላ ከትላንት ለሊት ጀምሮ በመቐለ ከፍተኛ የሐዘን ድባብ ይስተዋላል። ለቅሶ፣ ጩኸት፣ ዋይታ፣  በበርካታ የመቐለ አካባቢዎች ሲሰማ አርፍዷል። ከመርዶው በኋላ በመቐለ ሁሉም አብያተ ክርስቲያን ለተሰዉት  ታጋዮች ፀሎተ ፍትሐት ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ከንጋት ጀምሮ የተካሄደ ሲሆን፥ የተረዱ ቤተሰቦችም ተሰባስበው ሐዘናቸው ሲገልፁ ተስተውሏል።

የ3 ቀናት ሃዘን በመቐለ ከተማ ሲካሄድ
በትግራይ ከዛሬ ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚቆይ ክልላዊ ሃዘን ታውጇልምስል Million Haileselassie/DW

በመቐለ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በነበረው የሐዘን ስነስርዓት፥ በጦርነቱ ያለፉ  የትግራይ ሐይሎች አባላት ፎቶ የያዘ ወጣቶች፣ እናት እና አባቶች መራር ሐዘናቸው ሲገልፁ ተመልክተናል። ከነዚህ መካከል አጭር አስተያየት የሰጡን መርዶ የተነገራቸው አቶ ሀፍቶም አሰፋ፥ ታናሽ ወንድማቸው ማጣታቸው ነግረውናል።

ሌላዋ ያነጋገርናቸው እናት "ቀን እና ሌት እያለቀስን፣ ቀንና ለሊት እነሱን እያሰብን ነው የምንኖረው። የወደቁት የትግራይ ልጆች ናቸው። ልጆቻችን ሲሰርቁ አልጠፉም፣ ሲዋሹ አልወደቁም፣ በሌብነት አልነበሩ። በጅግንነት ነው ያለፉት፣ ለሀገራቸው። ጀግኖች ናቸው። አልቅሰናል፣ አንብተናል ይበቃናል" ብለዋል።

ክልላዊ የሃዘን ቀን በትግራይ
የልጆቻቸው ህልፈት የተረዱ ቤተሰቦች የሟች ቤተሰቦቻቸው ፎቶ በመያዝ እርማቸውን ሲያወጡ ከሚያሳዩ ፎቶዎች በከፊልምስል Million Haileselassie/DW

በጦርነቱ ወቅት ያለፉ  የትግራይ ሐይሎች አባላት መርዶ ለቤተሰቦቻቸው መነገሩ ተከትሎ፥ ከዛሬ ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚፀና ክልላዊ የሐዘን ቀን በትግራይ ተተግብሯል። ዛሬ ጠዋት በመቐለ የሰማእታት ሐወልት ቅጥር ግቢ በነበረ ስነስርዓት የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር መሪዎች፣ የሰማእታቱ ቤተሰቦች እና ሌሎች በተገኙበት የህሊና ፀሎት፣ የአበባ ጉንጉን ማኖርና ሌሎች ይፋዊ የሐዘን መግለጫ መርሐግብሮች ተከናውኗል። በዚሁ ስነስርዓት ንግግር ያሰሙት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ የወጣቶቹ ሕልፈት ከፍተኛ ሐዘን የሚፈጥር መሆኑ ገልፀዋል። አቶ ጌታቸው "በተለይም ለተከበሩ አባቶቼ እና እናቶቼ በቁማችሁ እያላችሁ የልጆቻችሁ ህልፈት መንገር ከድንጋይም ይከብዳል። ታሪካዊ አጋጣሚ በዚህ ቦታ ካቆየኝ ግን እየመረረኝም ለህዝቤ ፅናቱ ይስጥህ ማለት ግድ ሆንዋል። እንደጠላቶቻችን ፍላጎትማ ሙሉበሙሉ ከምድረ ገፅ፣ ከታሪክ እና ከሰው ህሊና ልንጠፋ እንጂ ተርፈን ፅናቱ ይስጥ የምንባባልበት ሊሆን አይፈልጉም ነበር። በትግላችን፣ በልጆቻችን እና ወንድሞቻችን ክቡር መስዋእትነት፥ ተጋሩ አሁንና ለቀጣይ በዓለም አንድ ቦታ ይዘን እንኖራለን" ብለዋል።

የገጠመን ችግር ከባድ ነው፣ ይህ ለምን ሆነ ብለን ራሳችን እንጠይቃለንሲሉም አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምረው ገልፀዋል። "እኛ፣ እኔን ጨምሮ እንደመሪዎች ምን ስላደረግን ወይም ምን ስላላደረግን፣ ስለምን ይህ ሁሉ ገጠመን ብለን ልንጠይቅ፣ ንስሃ ልንገባ፣ ይህ የገጠመን መከራ እና መስዋእትነት እንዳይደገም ብለን ውስጣችን ልንፈትሽ ለህዝባችን ቃል ልንገባ ግድ ነው" ሲሉ የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ጨምረው ገልፀዋል።

ዛሬ በመቐለ፥ ከሐዘን ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴ ካልሆኑ ውጭ የመንግስት መስርያቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ መዝናኛ ማእከላት ተዘግተዋል፣ የትራፊክ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል፣ በአጠቃላይ ከፍተኛ የሐዘን ድባብ ሰፍኖ ውሏል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር