1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ወሎ ዞን ኦፓል ሲፈልጉ ናዳ የቀበራቸው ሰዎች የሕይወት አድን ጥረት ተቋረጠ

ዓርብ፣ የካቲት 8 2016

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ወገልጤና ከተማ አቅራቢያ በማዕድን ቁፋሮ ላይ የነበሩና በናዳ የተዳፈኑ ወጣቶች ከናዳው ሳይወጡ ከአንድ ሳምንት በላይ ሆናቸዉ። በሰው ኃይል ቁፋሮ ወጣቶችን ለማዳን የሚደረገው ስራም ከተቋረጠ 2 ቀናት እንዳለፈዉ ቤተሰቦችና የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል። ቤተሰብ ግን በከፍተኛ ጭንቀት ላይ ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/4cURS
 ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ማዕድን ማዉጫ አካባቢ
ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ማዕድን ማዉጫ አካባቢ ምስል South Wollo Zone Communication

በአማራ ክልል በመዓድን ማዉጫ ናዳ የተዳፈኑ ወጣቶች ጉዳይ

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ወገልጤና ከተማ አቅራቢያ ጥር 30/2016 በኦፓል ቁፋሮ ላይ የነበሩና በናዳ የተዳፈኑ ወጣቶች ከናዳው ሳይወጡ ከአንድ ሳምንት በላይ አስቆጥረዋል፣ በሰው ኃይል ቁፋሮ ወጣቶችን ለማዳን የሚደረገው ስራም ከተቋረጠ 2 ቀናት ማሳለፉን ቤተሰቦችና የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል፣ ቤተሰብ ግን በከፍተኛ ጭንቀት ላይ ናቸው፡፡

አብዛኛዎቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የነበሩና ኑሯቸውን በተለያየ መንገድ ሲደግፉ ቆይተዋል፣ ከነኚህ ወጣቶች መካከል በማዕድን ማውጣት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ይገኙበታል፣ እንደወትሮው አገር አማን ብለው በባህላዊ መንድ ወደ ኦፓል ማውጫ ዋሻ አመሩ፣ ጥር 30/2016 ዓ ም ግን እንደበፊቱ በለስ አልቀናቸውም፣ የዞኑ አስተዳደር እንደገመተው 20 የሚሆኑ ወጣቶች ይቆፍሩበት የነበረ ውሻ ተደርምሶ በእለቱ እኩለ ሌሊት አካባቢ በአፈርና በዓለት ናዳ ተዳፈኑ፡፡

ወጣቶቹን በቁፋሮ ለማውጣት ለ5 ቀናት ያክል በሰው ኃይል የቁፋሮ ስራ ተካሄደ፣ ሆኖም የዋሻው የላይኛው ክፍል የመናድና የመደርመስ ስጋት በመፍጠሩና በነብስ አድን ስራ ላይ ለነበሩ ሰዎች ስጋት በመሆኑ ቁፋሮው 70 ሜትር ያክል እንደደረሰ ተቋረጠ፡፡

ታላቅ ወንድማቸው በናዳው ከተዳፈነባቸው መካከል አቶ አዳነ በሪሁን አንዱ ናቸው፣ አንድ እህትና አንድ ወንድም እስካሁን አደጋውን አልሰሙም፣ ይሁን እንጂ እድሜያቸው የገፋው አባት በእርጅና ዘመናቸው ከባድ ሀዘን ላይ ወደቁ ይላሉ፣ “አባቴ ወገቡን በገመድ አስሮ አደጋው በደረሰበት ቆላማ ቦታ በየቀኑ ተራራና አቀበት ሲወርድና ሲወጣ ይውላል” ብለዋል፣ ሆኖም የተጨበጠ ተስፋ የለም ነው ያሉት፡፡ አቶ አዳነ በምትችሉት ሁሉ እባካችሁ ርዱን ሲሉ ተማፅነዋል፡፡

ኦፓል
የደቡብ ወሎ ዞን የኦፓል ማዕድን ከሚገኝባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ ነው። ምስል Rob Lavinsky/ARKENSTONE

የአክስታቸው ልጅ በናዳው የተዳፈነባቸው አቶ ክንድያ ተስፋዬ አደጋው በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ሀዘንና ትካዜን መፍጠሩን ይገልጻሉ፣ በየቤቱ የሚሰማው ለቅሶ ብቻ ነው ብለውናል፡፡ እስካሁን ናዳ ከተጫናቸው ወገኖች በኩል የተገኘ ፍንጭ ይኖር እንደሆን? አቶ ክንድያን ጠይቄያቸው ነበር፡፡ ሆኖም ምንም በህይወት መኖርና አለሞኖራቸውን የሚያመለክት ፍጭ የለም ሲሉ ነው ተስፈ  በቆረጠ ስሜት ነገሩን፡፡

የደላንታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤሌው በሪሁን በሰው ኃይል የሚደረገው ነብስ የማዳን ስራ ሌላ ችግር ይፈጥራል ተብሎ በመሰጋቱ ቁፋሮው መቆሙን ተናግረዋል፣ ሆኖም የወጣቶቹን እጣፋንታለመወቅ ከህብረተሰቡ ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት የጅኦሎጂ ባለሙያዎች ቦታውን ከተመለከቱ በኋላ ሌላ አማራጭ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

ወጣቶቹ በናዳ ከተያዙ 8ኛ ቀናቸው በመሆኑ በህይወት የመገኘት እድላቸው ምን ያህል ይሆናል? ብለን ጠይቀናል፣ አቶ አያሌው፣ “ያን ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋ፡፡

የደላንታ ወረዳ ማዕድን ጽ/ቤት ቡድን መሪ አቶ በሪሁን አበረ በበኩላቸው በዋሻው ውስጥ የተለያዩ ጉድጓዶች መኖራቸውን አመልክተው፣ ባለፉት 13 ዓመታት በተለያዩ ጊዜዎች በሚፈጠሩ ናዳዎች የሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውሰዋል፡፡

 

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ