በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሁለት ወረዳዎች በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች መቸገራቸውን ገለጹ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 1 2016በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ ውስጥ በአከባቢው ከመንግስት እውቅና ውጪ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የተባሉ ታጣቂዎች ላይ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ መክፈታቸውን ተከትሎ ተቀስቅሷል በተባለው አለመረጋጋት በርካታ የአከባቢው ነዋሪዎች ከቀዬያቸውና ንብረታቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ ዶይቼ ቬለ ከሰሞኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በዚሁ በሁለቱ ወረዳዎች በተለይም በአቤዶንጎሮ ወረዳ ቀጥሏል በተባለው የጸጥታው ይዞታ መደፍረስ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ጭምር ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ በተለያዩ ስፍራዎች ወድቀው እንደሚገኙ የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡን የአቤ ዶንጎሮ ወረዳ ነዋሪ አሁን ላይ እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ጫካ መሸሸጋቸውን ገልጸው፤ ሰላማዊ ዜጎችን ስጋት ውስጥ ያስገባው ያሉት ወታደራዊ እርምጃው አሁንም በመቀጠሉ መረጋጋት ወዳአከባቢው እዳልተመለሰ አብራርተዋል፡፡
“የተሻለ ነገር የለም አሁንም ነገሮች እንደቀጠሉ ነው፡፡ የፋኖ አባል ነህ በሚል ነው የሚገደሉት፡፡ ይህ ደግሞ ማህበረሰቡን አፈናቅሎ በርሃብም የተዳከመ ብዙ ሰው አለ፡፡ እርምጃውን የምወስዱቱ አካላት ሴቶችና ሰላማዊ ሰዎች አንነካም ብሉም በሚተኮሰው ከባድ መሳሪያ በመረበሽ ህይወታቸው ያለፈ ነፍሰጡር እንኳ አሉ” ሲሉም ሃሳባቸውን አክለዋል።
በሰሞኑ የሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉና በርካቶች መፈናቀላቸው ተሰማ
አስተያየት ሰጪው አክለውም የማህበረሰቡ በስጋት ቀዬያቸውን መልቀቅ ተከትሎ ንብረቶች እየተሰረቁና እየወደሙ ነው ይላሉም፡፡ “ከኋላ ደግሞ ማንነታቸውን የማናውቅ ሰዎች የንብረት ስርቆት ላይ የተሰማሩ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የቤት እቀም ሆነ ማንኛውንም ንበረት ይወስዳሉ” ሲሉም ግጭቱ በሰላማዊ ዜጎችም ላይ ጉዳት ማድረሱን አስረድተዋል፡፡
ሌላም ሀሳባቸውን የሰጡን የአከባቢው ነዋሪ አሁንም ድረስ ቀጥሏል ባሉት ሰሞነኛው ግጭት ከየቦታው የአከባቢው ማህበረሰብ ተፈናቅሎ የከፋ ያሉት ሁኔታ ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል፡፡
“ልጆቻችንን ይዘን አሁን ያለነው በጫካ ነው፡፡ እዚህም ዋስትና የለም፡፡ ማን ችግራችንን እንደሚፈታው በጣም አስቸጋሪ ነው” ያሉት በአቤ ዶንጎሮ ወረዳ ከቤት ንብረታቸው ወጥተው እንደምገኙ የሚገልጹ አስተያየት ሰጪ፤ አሁን ላይ የሚሰራበት ሁኔ አስቸጋሪ በመሆኑ ርሃብ ላይ መውደቃቸውን አስረድተዋል፡፡ የተፈናቃዮች ቁጥር “ስፍር ቁጥር የለውም” የሚሉት አስተያየት ሰጪዋ ካባድ ያሉት ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋልም።
በአሙሩ ወረዳ በታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ
ዶይቼ ቬለ ስለዚሁ ሰሞነኛ ግጭት ምንነትና እልባቱን በተመለከተ ከአከባቢው ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት እስካሁንም አልሰመረም፡፡ አንድ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣን በነዚህ የምዕራብ ኦሮሚያ አከባቢን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች የጸጥታ ይዞታን ለማሻሻል ወታደራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ እነዚህን ኦፕሬሽኖች የሚመራው የአገር መከላከያ ሰራዊት እንደመሆኑ ይፋዊ አስተያየት የመስጠት ስልጣን እንደማይኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ሂደትና የተፈናቃዮች ስጋት
የአገር መከላከያ ሰራዊት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሰፋፊ የጸጥታ ማስከበር ወታደራዊ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ ደጋግሞ ብገልጽም ስለዚህ አከባቢ በተናጥል ያለው ነገር አልተሰማም፡፡
የወለጋው ግጭት ዳራ
ባለፉት አራት ዓመታት በአራቱ የወረጋ ዞኖች ግጭት አለመረጋጋቱ ከተስፋፋ ወዲህ በተደጋጋሚ የሚከሰተው በተለይም ብሔረን መሰረት ያደረገው ግጭት በርካቶችን አፈናቅሎ ቁጥራቸው የማይናቅ ዜጎችንም ህይወት መቅጠፉ ይታወቃል፡፡ በዚህ አከባቢ በተለይም የኦሮሞ እና አማራ ብሔር ማህበረሰቦች ለዘመናት ተዋደው መኖራቸው ብነገርም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ግጭቶች፤ በተለይም አልፎ አልፎ የታዩ የብሔር መልክ የያዙ የተባሉ ግጭቶች የአከባቢውን የጸጥታ ሁኔታ አወሳስበውት መዝለቁ ይታወሳል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ማህበረሰቡ መካከል የተፈጠሩትን ግጭቶች በእርቅና ውይይት የመፍታት ጥረቱ ስለመጀመሩ ተደጋግሞ ብነገርም አሁንም ድረስ ከአከባቢው ግጭትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ግን ብያንስ እስካሁን ቀላል አለመሆኑ ነው የሚነገረው፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ