የተፈናቃዮች ምሬት በደቡብ ወሎ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 2017በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ከተለያዮ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈናቀሉ ቁጥራቸዉ ከ40 ሽህ በላይ የሆኑ ተፈናቃዮች የምግብ ድጋፍ መቆራረጥ እየገጠማቸዉ መሆኑን ተናገሩ።
በተለይም ተፈናቃዮቹ ባለፉት ሦስት አመታት ሲጠቀሙባቸዉ የነበሩ የመጠለያ ድንኳን ለስድስት ወራት አገልግሎት እንዲሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸዉን ነዉ በገራዶና በሀይቅ መካነ ኢየሱስ የስደተኛ ጣቢያ ያነጋገርኳቸዉየሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች የሚገልፁት።
በገራዶ የመጠለያ ጣቢያ ያሉ ተፈናቃዮች የምግብ መቆራረጡ ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ ተንቀሳቅሶ ስራ ለመስራትና የዕለት ጉርስ ለመሸፈን የኗሪነት መታወቂያ ካርድ የሌለን በመሆኑ ለእንግልትና ድብደባ እየተዳረግን ነዉ ይላሉ።
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትናተጠሪ ፅህፈት ቤት በበኩሉ ለህዳርና ታህሳስ ወር ተብሎ የመጣዉ እርዳታ የአጠቃላይ ድጋፍ ፈላጊዉን 38 በመቶ ብቻ በመሆኑ ለማከፋፈል መቸገራቸዉን አቶ አሊ ሠይድ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ገልጸዋል።
እነኝህ ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል ተፈናቅለዉ ኑሯቸዉን በደብ ወሎ ዞን ያደረጉ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ እስካሁን ምንም አይነት ጥያቄ ባያቀርቡም ፍላጎቱ ካለ ግን በንግግር ችግሩን ለመፍታት ይሰራል ይላሉ አቶ አሊ ሠይድ።
በአሁኑ ወቅት በዞኑ ተፈናቃዮችን መሠረት አድርገዉ የሚሰሩ ግብረሠናይ ተቋማት እየወጡ መሆን ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም ተጨማሪ የመጠለያ ድንኳኖችን ለማግኘት እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞኑ የሚገኙ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑትን ዲያቆን ተስፋ ባንታብልን ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸዉ አልተሳካም።
ኢሳያስ ገላው
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ