ትግራይ ክልል ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ ተገቢ ርምጃ ይወሰድ ተባለ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 24 2017በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ለማስቆም፥ በአጥፊዎች ላይ ተገቢ ርምጃ እንዲወሰድ በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ተቋማት ጥሪ ቀረበ ። በዓድዋ ከተማ የ16 ዓመትዋ አዳጊ ሴት አግተው በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ ፍርድቤት የሞት እና የእድሜ ልክ አስራ ብይን ሰጥቷል ።
የ16 ዓመትዋ ታዳጊዋ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ
የ16 ዓመትዋ ታዳጊ ማኅሌት ተክላይ፥ መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓመተምህረት አመሻሽ ላይ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት እየሄደች በነበረችበት ሰዓት ከመንገድ በተሽከርካሪ አግተው በመውሰድ፥ ወደ ወላጆችዋ በመደወል ገንዘብ በመጠየቅ፥ እንዲሁም በተመሳሳይ ቀን ታዳጊዎ በመግደል ወንጀል ተይዘው ጉዳያቸው በመቐለ መካከለኛ ፍርድቤት ሲታይ የነበረ ተከሳሾች ትላንት ፍርድቤቱ በዋለው ችሎች በአንደኛ ተከሳሽ የ24 ዓመቱ ወጣት ዓወት ነጋሲ የሞት ፍርድ ያስተላለፈ ሲሆን፥ በሁለተኛ ተከሳሽ የ20 ዓመት ወጣት ናሆም ፍፁም ላይ ደግሞ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
የመቐለ ከተማ ፍትህ ጽሕፈት ቤት አቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ሓዱሽ አባዲ፥ በታዳጊ ማህሌት ላይ በወንጀለኞቹ ከባድ ስቃይ እና አሰቃቂ ግድያ መድረሱ በማንሳህ፥ የፍርድቤቱ ውሳኔ አስተማሪ ይሆናል ተብሎ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።
ፍርዱ ምን ያህል አስተማሪ ነው?
አቶ ሓዱሽ "ተሰጥቶ ያለ ፍርድ በአንደኛ ተከሳሽ አቶ ዓወት ነጋሲ ሓጎስ የሞት ፍርድ ሲሆን፥ ተባባሪ የነበረው ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ናሆም ፍፁም ሀይሉ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ነው። ይህ ቅጣት ተመሳሳይ ወንጀል ለሚፈፅሙ አስተማሪ ነው ብለን ነው የምንወስደው" ብለዋል። የሟችዋ ታዳጊ ወላጅ አባት አቶ ተክላይ ግርማይ የፍርድቤቱ ውሳኔ እንደሚቀበሉ ይናገራሉ።
በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መበራከታቸው ይገለፃል። የትግራይ ሴቶች ማሕበር በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፥ በአንድ አመት ግዜ ውስጥ በክልሉ 783 ፆታ መሰረት ያደረጉ በሴቶች ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች መመዝገባቸው የሚያመለክት ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል 44ቱ የግፍ ግድያዎች ናቸው ብሏል ። ከእነዚህ ግድያዎች ደግሞ 24ቱ የተፈፀሙት ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ መሆኑ ተጠቅሷል። ለእነዚህ ግድያዎች እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች ፍትህ ማጣት ደግሞ በተበዳይ ቤተሰቦች ላይ እና በአጠቃላይ ማሕበረሰቡ ቁጣን የፈጠረ ነው።
በደሉን ለማስቆም ምን እየተሠራ ነው?
በትግራይ በሴቶች ላይ የሚደረስ በደል ለማስቆም ከሚሰሩ ሲቪል ተቋማት መካከል የሆነው ይኾኖ የተሰኘ ተቋም መንግስት ጥቃቶች በመከላከል፣ ሲፈፀሙ ደግሞ አጥፊዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ያቀርባል። እየታዩ ናቸው የተባሉ የፍትህ መጓደል እና መዘግየት ችግር እንዲፈታም የይኾኖ ስራ አስከያጅ ፅዴና አባዲ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ