1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይና ለአፍሪቃ ወታደራዊ ግንባታ የ1 ቢሊዮን ዬን ገንዘብ ቃል ገባች

ቅዳሜ፣ ጥር 3 2017

ምዕራባውያኑ ኃያላን አገራት በተለይም ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ የነበራቸው ተጽእኖ በወቅቱ የአካባቢው ፖለቲካዊ ለውጥ መቀዛቀዙ ለቻይና መልካም አጋጣሚ ይመስላል ። ሰሞኑ ቻይና ለአፍሪቃ የ1 ቢሊዮን የቻይና የን ማለትም የ136 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ርዳታ ለማድረግም ቃል መግባቷ ይፋ ሁኗል ።

https://p.dw.com/p/4p2Px
ከአፍሪቃ ጋር ግንኙነቷን ያጠናቀረችው ቻይና  ለአፍሪቃ ወታደራዊ ግንባታ የ1 ቢሊዮን ዬን ገንዘብ ቃል ገብታለች
ከአፍሪቃ ጋር ግንኙነቷን ያጠናቀረችው ቻይና ለአፍሪቃ ወታደራዊ ግንባታ የ1 ቢሊዮን ዬን ገንዘብ ቃል ገብታለችምስል CFOTO/picture alliance

ቻይና በአፍሪቃ ተጽእኖዋን እያጎለበተች ነው

ምዕራባውያኑ ኃያላን አገራት በተለይም ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ የነበራቸው ተጽእኖ በወቅቱ የአካባቢው ፖለቲካዊ ለውጥ መቀዛቀዙ ለቻይና መልካም አጋጣሚ ይመስላል ። ቻይና የአፍሪቃ የውስጥ ፖለቲካን ለአፍሪቃውያን በመተው በከፍተኛ ሁኔታ አፍሪቃ ውስጥ መዋዕለ-ንዋይ ታፈሳለች ። ያም ብቻ አይደለም ወታደራዊ ርዳታም ለማድረግ ቁርጠኝተነቷን ዐሳውቃለች ። ከሰሞኑ ቻይና ለአፍሪቃ የ1 ቢሊዮን  የቻይና ዩዋን  ማለትም የ136 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ርዳታ ለማድረግም ቃል መግባቷ ይፋ ሁኗል ።

ቻይና ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጎለበት በመጣር ላይ ነች ። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዋንግ ዪ ከአፍሪቃ ጋር ለሦስት ዐሥርተ-ዓመታት የዘለቀውን ግንኙነት በማጠናከር አራት አገራትን ጎብኝተዋል ። የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፤ ናይጄሪያ፤ ቻድ እና ናሚቢያ ናቸው በውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ የተጎበኙት ።

ቻይና ለአፍሪቃ 1 ቢሊዮን የቻይና የን ማለትም የ136 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ርዳታ ለማድረግም ቃል መግባቷ ተዘግቧል ። ይህም የተገለጠው የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሐሙስ ዕለት ናይጄሪያን በመጎብኘት የአፍሪቃ ጉዟቸውን ባጠቃለሉበት ወቅት መሆኑን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል ። ርዳታውም አፍሪቃ ውስጥ 6,000 ወታደሮችን እና 1,000 ፖሊሶችን ለማሰልጠን የሚውል ነው ተብሏል ።

ቻይና አፍሪቃ ውስጥ ያላትን የንግድ ተጽእኖ በማጎልበት ቀደም ሲል የዘራችውን ለማጨድ መቃረቧን ቻይና አፍሪቃ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ በቅርበት የሚያጠኑት ናይጄሪያዊው ተንታኝ ኦቪግዌ ኤጌዌጉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።

«አኅጉሪቱ ከእነ ችግሮቿ በፍጥነት ሕዝብ አላት፥ መካከለኛ የኑሮ ሁኔም እየጨመ ነው እናም በውጭ ንግድ ላይ እንደተመሰረተችው ቻይና ያሉ አገራት በእርግጥም መልካም አጋጣሚ ነው ቻይናዎች በአሁኑ ወቅት አፍሪቃ ውስጥ በየትኛውም አይነት የፖለቲካ ሥጋት ምንም አይነት ተግዳሮት ቢገጥም ይህን የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ገበያ ወደ ባሕር ማዶ እንደ መውጫ ነው የሚጠቀሙበት። »

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዋንግ ዪ ከናይጄሪያ ፕሬዚደንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ ጋር
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዋንግ ዪ ከናይጄሪያ ፕሬዚደንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ ጋር በአቡጃ ናይጄሪያምስል Yang Zhe/Xinhua/IMAGO Images

ምዕራባውያን በተለይም አውሮጳውያን ከአፍሪቃ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለአፍሪቃውያን መሪዎች በሚመች መልኩ ማድረጉ ላይ በተቸገሩበት በአሁኑ ወቅት አጋጣሚው ለቻይና መልካም ይመስላል ። የቻይና ደቡብ ንፍቀ-ክበብ ፕሮጄክት ተንታኙ ክርስቲያን ጌሩድ ኒማ እንደሚሉት ከሆነ አፍሪቃ ከቻይና የምታገኘው ወታደራዊ ድጋፍ ወደፊት ይበልጥ መጨመሩ አይቀርም ።

«በእርግጥም ከቻይና ይበልጥ በዛ ያሉ ወታደራዊ መርከቦች ያለ አንዳች ኮሽታ ወደተለያዩ የአፍሪቃ አገራት መላካቸው አይቀርም፤ ምክንያቱም ፍላጎቱ እዚያ አለና በእርግጥም ከሩስያ ባሻገር አዲስ የደኅንነት አጋር የሚሹ እንደ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ያሉ አገራት ሲኖሩህ የሚያማትሩት ወደ ቻይና ነው ምክንያቱም ለነሱ ከቻይና ጋር በወታደራዊ ቁሶች ግብይት መሳተፍ በይበልጥ ቀላል እና ርካሽም ነው »

ቻይና አፍሪቃ  ውስጥ ይበልጥ ተሳትፎዋ የጎለበተው ቀደም ሲል ቅኝ ገዢ የነበሩ አገራት ከአፍሪቃ በተባረሩበት ወቅት ነው ።  የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ቀደም ሲል በታኅሣሥ ወር ቻድን በጎበኙበት ወቅት ጉብኝታቸው በድንገት በወታደራዊ መግባባት መቋረጡ በራሱ በተለይ በምዕራባውያን ዘንድ ጥርጣሬ አጭሯል ። ክርስቲያን ጌሩድ እንደሚገምቱት ከሆነ ግን ሁኔታው ተገጣጠመ እንጂ ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም ። ለዚህም ቻድ ውስጥ የሆነውን እንደ አብነት ያነሳሉ ።

 የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዋንግ ዪ ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ዴኒስ ሳሱዎ ንጉሴዎ ጋር
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዋንግ ዪ ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ዴኒስ ሳሱዎ ንጉሴዎ ጋር ብራዛቪል ውስጥምስል IMAGO/Xinhua

«የመጀመሪያው ምክንያት ፈረንሳይ ወታደራዊ ሠፈሯን በመዝጋት ነቅላ እንድትወጣ ብቻ ነው የተጠየቀችው ሆኖም በፈረንሣይ እና ቻድ መካከል ያለው ኤኮኖሚያዊ ግንኙነት ይቀጥላል ሁለተኛው ጉዳይ ምንም እንኳን ፈረንሳይ ቻድ ውስጥ ብትኖርም ቻይናም ቀደም ሲል እዚያው ነበረች የቻይና መኖር በደንብ ነው የሚታየው፦ እናም ፈረንሣይ ኖረችም አልኖረችም ቻይና ቻድ ውስጥ ባላት አቋም ላይ አንዳችም የሚቀይረው ነገር የለም ሦስተኛው ምክንያት፦ እንደሚታወቀው ቻድ የወዳጆች የምትላቸው ጦር ሠራዊቶች አገር ለቅቀው እንዲወጡ ጠይቃለች ያን ክፍተት ቻይና ትሸፍናለች ማለት ግን አይደለም ምክንያቱም ቻይና እንደ ቻድ ባሉ አገራት ውስጥ እንዲያ ያሉ ጦር ሠፈሮችን የማቋቋም ልማድ የላትምና »

አፍሪቃ ውስጥ በተለይም በምዕራቡ ክፍለ አኅጉር ቻይና እና ሩስያ ይበልጥ ወጣ ገባ ሲሉ አውሮጳውያን ቀድሞም የነበራቸው ይዞታ እየቀነሰ ነው ። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ብዙም አፍሪቃ ላይ እንደ ቀድሞው ያተኮረ አይመስልም ። ተሰናባቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ባለፈው ታኅሣሥ ወር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪቃን የጎበኙት በዘመነ-ሥልጣናቸው አመሻሽ ላይ ነበር ። ምናልባትም በተለይ በምዕራብ አፍሪቃ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ለውጥ ቻይና እና አፍሪቃ  በሦስትዮሽም ሩስያን አካትቶ የሚቀጥል ይመስላል እንደ አካባቢው ተንታኞች ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti