አማራ ክልል ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ተጠቅተዋል
ሐሙስ፣ ሰኔ 6 2016በአማራ ክልል ባለፉት 11 ወራት ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ መታመማቸውን የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ዐስታወቀ ። ነዋሪዎች ደግሞ በዚህ ዓመት የተከሰተው የወባ በሽታ በእጅጉ በርካታ ሰዎችን አጥቅቷል ይላሉ ። የክልሉ ጤና ቢሮና የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ኃላፊዎችም የወባ በሽታ በከፋ ሁኔታ እየከፋ መጥቷል ብለዋል፡፡
«በአማራ ክልል ያለው ግጭትና በተደጋጋሚ የመንገዶች መዘጋጋት የወባ ሥራ ቁጥጥርን አዳክሞታል፣ የመድኃኒት ስርጭትን ደግሞ አስተጓጉሎታል» ሲሉ የክልሉ ጤና ተቋማት ኃላፊዎች ይናገራሉ። ኅብረተሰቡ ወባን ለመከላከል ያለው ዝቅተናኛ ግንዛቤና ቸልተኝነት ሌላው ምክንያት እንደሆነ ነው የሚገልፁት፡፡
በዚህም ምክንያት በአማራ ክልል የወባ ስርጭት መበራከቱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፤ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት መለአከ ብርሐን ፍሰሐ ጥላሁን አስተያየታቸውን ከሰጡን የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች አንዱ ናቸው፡፡
"አሁን በባሕር ዳር ወባ ከቤቴ ጀምሮ አለ፣ ህፃናት እየታመሙ ነው፣ ባሕር ዳር ውስጥ ግንቦት ወር የወባ መነሻ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ለህክምና ሰዎች ወደ ጤና ተቋም ሲሄዱ ወባ እየተገኘባቸው ነው፡፡” ብለዋል፡፡ ሌሌ አስተያየት ሰጪም እንዲሁ የወባ በሽታ ስርጭት በከፋ ሁኔታ መስፋቱን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
50 ዓመት አድሜ ያላቸው እኚሁ ነዋሪ "የወባ በሽታዘንድሮ እውነቱን ለመናገር በእኔ እድሜ እንደዘንድሮ ተከስቶ አያውቅም፣ የወባ ወረርሽኝ ነው ያለው፣ የወባ በሽታ ከየት እንደሚመጣ መረጃው አለን፣ ግን አጎበርን የመጠቀም ፍላጎትና ልምድ ከራሴ ጀምሮ የለም፣ በዚህ ዓመት በሽታው በጣም አይሏል፣ ከሚገመተው በላይ ነው፡፡”
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለም አሰፋ ሰሞኑን ለዶቼ ቬሌ እንደተናገሩት ህብረተሰቡ ያለው የትንኝ መከላከያ የአልጋ አጎበር አጠቃቀም ዝቅተኛ በመሆኑና ሌሎች የመከላከል ስራዎችን ቸል በማለቱ በሽታው በብዛት በከተማዋ መታየቱን አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት 7ሺህ ሰዎች የወባ ምርመራ አድርገው በ2ሺህ 460 ሰዎች ላይ በሽታው ተገኝቷል ብለዋል፡፡
"የወባ በሽታ አሁን አሁን በተለይ፣ ከሳምንት ሳምንት እየጨመረ ለበት ሁኔታ ይታያል፣ የወባ ትንኝ መከላከያ የአልጋ አጎበር አጠቃቀም ችግር አለ፣ የወባ በራቢያ ተብለው የተለዩ ቦታዎችን ማህበረሰቡ ከመከላከል ስራ ላይ ክፍተቶች አሉ፣ የሚዳፈኑ፣ የሚታጨዱ የሚፋሰሱ ቦታዎችን እነኚህን ቦታዎች ከማፅዳት አንፃር ክመቶች አሉ፣ ሆኖም የግንዜቤ ፈጠራ ስራዎችን እየሰራን ነው፣ ህክምናም እየተሰጠ ነው፡፡ ”
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በወባ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው ህብረተሰቡ የመከላከያ ዘዴዎችን እንዲጠቀም ጠይቀዋል፡፡
"ወባ በአሁኑ ሰዓት በጣም ከባድ ችግር እየፈጠረ ነው፣ወባ ሊራባ የሚችልባቸውን ቦታዎች በማዳፈን፣ በማፋሰስ፣ የአካባቢ ቁጥጥር ስራን ማጠናከር ይጠይቃል፣ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የወባ ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡”
የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ትናንት በቢሯቸው በሰጡት መግለጫ ደግሞ በክልሉ ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታና በሌሎች ምክንያቶች ካለፈው ሐምሌ 2015 ዓም ጀምሮ በአማራ ክልል አንድ ሚሊዮን 200ሺህ ሰዎች በወባ ታምመው ወደ ህክምና ተቋማት መምጣታቸውን ገልጠዋል፡፡ በሽታው በዋናነት በምዕራብ የአማራ ክልለ ዞኖች መበራከቱንም አመልክተዋል፡፡
"... የጤና አገልግሎቱን በተለይ የወረርሽን ቁጥጥርና የሌሎችን በሽታዎች ቁጥጥርና ቅኝት ላይ በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ተፅዕኖ አሳድሯል፣ ባለሞያዎች እንደፈለጋቸው በየትኛውም ሁኔታ በራሳችን ተሸከርካሪዎች ሄደን እንደበፊቱ ለመደገፍ አልቻልንም፣ ገደቦች አሉ፣ ከሐምሌ 1/2015 ዓ ም ጀምሮ ከአንድ ሚሊዮን 200ሺህ ሰዎች የወባ በሽታ ህክምና አግኝተዋል፣ ይህ ከፍተኛ ቁጥር ነው፤ በሽታው በተለይ ምዕራብ አማራ በምንለው በጎጃም፣ ጎንደር እስከ ሁመራ ያለው 90 ከመቶ የወባ ስርጭት ለበት አካባቢ ሲሆን፣ በምስራቅ አማራ በተለይም በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ዞኖች በሚገኙ ቆላማ ወረዳዎች የሽታው ይታያል፡፡” ነው ያሉት፡፡
አሁን በተጨባጭ ምን ያክል የወባ ታማሚ ቁጥር እንደሚገኝ እንዲገልፁለት በዶቼ ቬሌ የተጠየቁት ዋና ዳይሬክተሩ "ቁጥሩ ብዙ ነው” ከማለት በስተቀር ትክለኛ ቁጥሩን መናገር አልፈለጉም፣ ባለፉት 11 ወራት የሽታው ስርጭት ሰለመስፋፋቱ እንጂ ምንያክል ሰዎች በበሽታው ሕይወታቸው እንዳለፈም አቶ በላይ በመግለጫቸው ያሉት ነገር የለም፡፡፡
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ