አንድ ለአንድ፦ ከተስፋዬ ዳኜ ጋር፤ አሰቃቂው የመንገድ አደጋ በኢትዮጵያ ለምን በረታ?
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 25 2017በሲዳማ ክልል ቦና ዙሪያ ወረዳ ሠርገኞች ጭኖ በመጓዝ ላይ የነበረ ተሽከርካሪ ታኅሳስ 20 ቀን 2017 በገጠመው አደጋ 71 ሰዎች መሞታቸውን እና አራት መጎዳታቸውን ፖሊስ አስታውቋል። ከሟቾቹ መካከል ሙሽራ እና አጃቢዎቹ ይገኙበታል። አሰቃቂ አደጋ የገጠመው አይሱዙ የደረቅ ጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ነው።
እንዲህ አይነት አደጋዎች እየተከሰቱ የዜጎችን ሕይወት ሲነጥቁ፣ አካል ጉዳተኛ ሲያደርጉ እና ንብረት ሲያወድሙ በተደጋጋሚ ይታያል። በኦሮሚያ ክልል ሰብስቤ ዋሻ በተባለ ቦታ ተሽከርካሪ ገደል ገብቶ 16 የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በግንቦት 2015 ሕይወታቸውን አጥተዋል። ጨምሯል አልጨመረም ለማለት የሚያስችል የተደራጀ መረጃ ባይኖርም እየደረሱ የሚገኙ አደጋዎች አሰቃቂነት እየከፋ መሔዱ ይታያል።
በ2016 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 1 ሺሕ 358 ሰዎች በመንገድ ላይ አደጋዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቆ ነበር። በአደጋዎቹ 2,672 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።
በኢትዮጵያ በዓመት ከሚደርስ ሞት የመንገድ አደጋ 17.7 በመቶ ድርሻ እንዳለው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በጎርጎሮሳዊው 2021 ይፋ ያደረገው ሠነድ ያሳያል። ሠነዱ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች የበለጠ በመንገድ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የሚያሳይ ነው። በሰነዱ መሠረት በየዓመቱ ከሚከሰተው የወንዶች ሞት የመንገድ አደጋ 24.2 በመቶ ድርሻ አለው።
አስከፊውን የመንገድ አደጋ በተመለከተ ዶይቼ ቬለ የሕብረተሰብ ጤና ተመራማሪው አቶ ተስፋዬ ዳኜን አነጋግሯል። አቶ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ናቸው።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ