1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“እፎይታ ልናገኝ ነው ብለን ተስፋ ነበረን” የሰላም ንግግሩ መቋረጥ ያሳዘናቸው የወለጋ ነዋሪ

ሐሙስ፣ ኅዳር 13 2016

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን የሰላም ውይይት ያለ ሥምምነት መቆሙ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው የቄለም፣ የምሥራቅ እና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች ተናገሩ። “እፎይታ ልናገኝ ነው ብለን ተስፋ ነበረን” የሚሉ አንድ ነዋሪ “ለዚህ ምስኪን ሕዝብ ሲሉ ቢታረቁ በጣም ደስ ይለኝ ነበር” ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4ZLfc
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የኦሮሞ ፈረሰኞች በአዲስ አበባ አቀባበል ሲያደርጉ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ በአዲስ አበባ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎለት ነበር። ምስል Michael Tewelde/AFP

የሕዝብ አስተያየት

በኢትየጵያ መንግስትና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ሲካሄድ የነበረው ሁለተኛ ዙር የሠላም ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቅ እንዳሳዘናቸው የቄለም ወለጋ፣ ምስራቅና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ነዋሪዎች ተናግሩ። አቶ ያሲን ኢብራህም በቄለም ወለጋ ዞን መቻራ የተባለ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ድርድሩ ያለ ስምምነት መጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን ሰላም ይበልጥ ወደ ከፋ ደረጃ ሊወስድ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

በዞኑ ጊዳሚና መቻራ እንዲሁም አዋሳኝ በሆኑ ስፍራዎች በጸጥታ ችግር እና ህክምና እጦት ምክንያት ከአንድ ቀበሌ ከ5 እስከ 10 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል። የሰላም ድርድሩ አሁንም መቀጠል እንዳበለት እና በአካባቢው የሚስተዋለውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት እንደሚስፈልግ አብራርተዋል፡፡

በሰላም እጦት የተፈናቀሉ ዜጎች

በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የሚገኙ ሌላው ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ከሚገኙበት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ወደቤታቸው የመመለስ ህልም እንደነበራቸው ጠቁመዋል። በወረዳው ባለፉት 3 ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሚገልጹት ነዋሪው በአካባቢው የሚገኙ የአማራ እና ኦሮሞ ተወላጆች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ በማያውቁት ጉዳይ መፈናቀላቸውን ገልጸዋ።

በሰላም እጦት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ በርካቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ኑሯቸውን እየመሩ ይገኛሉ ብለዋል። በኪረሙ 52 ሺ የሚጠጉ የተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚገኙ የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር መረጃ ያመለክታል፡፡

በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በሻምቡ ዩኒቨርሲቲ
በአሮሚያ ክልል በበረታው ግጭት በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል ተገደዋልምስል Seyoum Getu/DW

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የነቀምቴ ነዋሪ “የሰላም ድርድሩ ለከልብ የመነጨና ዘላቂ ሰላም ለማስፍን ያለመ አልነበረም” የሚል ትችት አላቸው።  በአካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመገደቡ ህብረተሰቡ ለችግር ተጋልጦ መቆየቱን የተናገሩት ነዋሪው የስምምነቱ አለመሳካት “ክልሉ በተራዘመ የጸጥታ ችግር ውስጥ እንዲቆይና የነዋሪውን ህይወት አስከፊ ያደርጋል” ሲሉ ሥጋታቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል።

ድርድሩ መቀጠል አለበት

የሆሮ ጉደሩ ወለጋ ነዋሪው አቶ በከልቾ ያሚ ድርድሩ ህዝብን ታሳቢ በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አሁንም መቀጠል አለበት የሚል ሀሳብ አላቸው። በወለጋ ከትልልቅ ከተሞች ውጭ በርካታ አካባቢዎች ላይ ተቋማት በተሟላ መልኩ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ አመልክተዋል። በመንግስት እና ኦ.ነ.ሠ መካከል ተጀምሮ የነበረው ድርድር በስምምነት ይቋጫል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ እንደነበረም ተናግረዋል። ድንገት መጀመሩ የተነገረው ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁ እንዳሳዘናቸው አክለዋል።

በኢትዮጵያ መንግስትና ኦነሠ መካከል በታንዛኒያ ለ2ኛ ዙር ለሁለት ሳምንት ያህል የተካሄደው የሰላም ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ከትናንት በስቲያ ህዳር 11 ቀን 2016 ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው ባወጧቸው መግለጫዎች አስታውቀዋል።

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር