1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያና አዲሱ «የአፍሪቃ ኅብረት የድጋፍና ማረጋጋት የሶማሊያ ተልዕኮ»

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26 2017

ኢትዮጵያና ሶማሊያ መቅዲሾ ውስጥ ከትናንት በስተያ ካካሄዱት ውይይት በኋላ ለሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ ተልዕኮ ስኬት በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ኢትዮጵያ አስታውቃለች።ሶማሊያም ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረውን የተራዘመ ያለችውን ዲፕሎማሲያዊ ግጭት መፍታቷን ተናግራለች። ሆኖም ኢትዮጵያ በአዲሱ ተልዕኮ የሚኖራት ሚና በግልጽ አልተነገረም።

https://p.dw.com/p/4onCI
Türkei, Ankara | Erdogan, Mohamud und Ahmed bei gemeinsamer Pressekonferenz
ምስል Murat Kula//TUR Presidency/Handout/Anadolu/picture alliance

ኢትዮጵያና አዲሱ «የአፍሪቃ ኅብረት የድጋፍና ማረጋጋት የሶማሊያ ተልዕኮ»


የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ልዩ ልዑክ አምባሳደርና የአዲሱ የሶማሊያ ተልዕኮ ሃላፊ መሐመድ ኤል-አሚን  አዲሱ «የአፍሪቃ ኅብረት የድጋፍና ማረጋጋት የሶማሊያ ተልዕኮ» በእንግሊዘኛ ምህጻሩ(Aussom) የቀድሞውን «የኅብረቱ  የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ »፣በእንግሊዘኛ ምህጻሩ Atmisን ተክቶ ከትናንት በስተያ ስራ መጀመሩን  በጎርጎሮሳዊው አዲስ ዓመት መልእክታቸው ነበር ይፋ ያደረጉት። ይሁናና በአዲሱ የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ የተካተቱትን ሀገራት ዝርዝር ሶማሊያ እስካሁን ይፋ አላደረገችም። ይህም በአዲሱ የሶማሊያ ተልዕኮ ኢትዮጵያ እንደቀድሞው የመቀጠል አለመቀጠሏ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል።

የሰላም ማስከበር እና የባሕር በር ጉዳዮች እያነቃነቁት ያለው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ

በተልዕኮው የሚሳተፉ ሀገራት ማንነት ይፋ ባይሆንም ኢትዮጵያና ሶማሊያ፣ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ ተልዕኮ በሶማሊያን (AUSSOM) አውሶምን ስራ  ለማሳካት በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን  የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ትናንት አስታውቀል።  ሁለቱ ሀገራት እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ የተመራ የልዑካን ቡድን ከትናንት በስተያ በሞቃዲሾ ባካሄደው ውይይት ላይ ነው። ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንደምትሰራ ለአካባቢው መረጋጋት ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር  ለመንቀሳቀስ ቁርጠኛ መሆኗን  በውይይቱ ላይ ማሳወቋን የጠቀሱት አምባሳደር ነብያት፣ በዚህ ረገድ ከሶማሊያ ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።  

በቱርክ ፕሬዝዳንት ሽምግልና ለመነጋገር የተስማሙት የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች
በቱርክ ፕሬዝዳንት ሽምግልና ለመደራደር የተስማሙት የኢትዮጵያና የሶማሊያ መሪዎች ምስል DHA

የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ በበኩላቸው ከትናንት በስተያ ከኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ጋር ከተካሄደው ውይይት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ተፈጥሮ የነበረውን የተራዘመ ያሉትን ዲፕሎማሲያዊ ግጭት መፍታቷን አስታውቀዋል።  ሶማሊያ፣ ግዛቴ ናት ከምትላት ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ያስገኝልኛል ያለችውን ውል ከአንድ ዓመት በፊት የተፈራረመችውን ኢትዮጵያን ፣ በአዲሱ ተልዕኮ እንደማታካትት ከዚህ ቀደም በይፋ ማስታወቋ ይታወሳል ።

የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የአንካራ ስምምነት፥ የሶማሊላንድ በዓለ ሲመት

ሁለቱም ሀገራት ኢትዮጵያ በአዲሱ ተልዕኮ የሚኖራትን ተሳትፎ እስከዛሬ በግልጽ አልተናገሩም። በጉዳዩ ላይ ዶቼቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው አዲስ አበባ በሚገኘው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በተባለው አዲስ አበባ በሚገኘው የምርምር ተቋም ተመራማሪ ዶክተር ዳር እስከዳር ታዬ ኢትዮጵያ በአዲሱ የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተሳታፊ መሆንዋ እይቀርም ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ከአንካራው ስምምነት በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል ማሳየቱን  በዛሬው መግለጫቸው የጠቆሙት አምባሳደር ነብያት የሁለትዮሽ ውይይቱ በቅርቡ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ አዲስ አበባ ውስጥ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ተደርሷልም ብለዋል። 

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ