1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች ያለአግባብ ከሥራ ታግደዋል

ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2016

በትግራይ ክልል ከ3 ሺህ በላይ የፖሊስ አባላት በሕገ ወጥ መንገድ ከሥራ መታገዳቸውን የሕዝብ እንባ ጠባቂ አስታወቀ። የመንግሥት ሠራተኞች፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሌሎችም እንዲሁ በሕገወጥ መንገድ ከሥራ ታግደዋል፣ ከደረጃቸው እንዲወርዱ ተደርገዋል፣ የተለያዩ አስተዳደራዊ በደሎችም ደርሶባቸዋል ይላል በኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ የመቐለ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት።

https://p.dw.com/p/4YHvj
 የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ጽሕፈት ቤት መቀለ ቅርንጫፍ
የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ጽሕፈት ቤት መቀለ ቅርንጫፍ ምስል Million Haileselassie/DW

የእንባ ጠባቂ መቀሌ ቅርንጫፍ መግለጫ

በኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የመቐለ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት እንዳስታወቀው በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች አለአግባብ ከሥራ ተባርረዋል፣ ደሞዝ ተከልክለዋል እንዲሁም ሌሎች በደሎች እየደረሰባቸው ነው። በተለይም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከተቋቋመ በኋላ ባለው ጊዜ በርካታ ቅሬታዎች ወደ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም እየቀረቡ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከተሰጣቸው ሐላፊነት ውጭ ሥልጣን አለአግባብ መጠቀም፣ ሕጋዊ አሠራሮችን በመጣስ ውሳኔ መስጠት፣ አስተዳደራዊ በደሎችን መፈፀም፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ማባረር፣ ደሞዝ መከልከል፣ ከደረጃ ማውረድ የመሳሰሉ እና ሌሎች የአስተዳደር በደሎችን የሚያሳዩ ተግባራት ተፈጽመው ቅሬታ መቅረቡን በኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የመቐለ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት አስታውቋል። ለዚህ አንድ ማሳያ የሚሆነው በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ፖሊሶች በትግራይ ከሕግ አግባብ ውጭ ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉ በኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመቐለ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ዋና እምባ ጠባቂ ፀሐየ እምባየ ለዶቼቬለ ገልፀዋል።  

ፎቶ ከማኅደር፤ የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ
በኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የመቐለ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች አለአግባብ ከሥራ ተባርረዋል፣ ደሞዝ ተከልክለዋል እንዲሁም ሌሎች በደሎች ደርሶባቸዋል አለ። ፎቶ ከማኅደር፤ የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

እንባ ጠባቂ ተቋሙ በተሰጠው ሐላፊነት መሰረት ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች በክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት እየተከበሩ እንዳልሆኑም ተቋሙ ጨምሮ ገልጿል። በትግራይ የአስተዳደር በደሎች በስፋት እየታዩ መሆኑን ጨምረው ያነሱት  በእምባ ጠባቂው ተቋም የመቐለ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት እምባ ጠባቂው አቶ ፀሐየ እምባየ ፥ በየደረጃው የከፉ አስተዳደራዊ በደሎች በህዝቡ ላይ እየደረሱ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት ለዶቼቬለ ተናግረው የነበሩ በትግራይ ከሥራቸው የተባረሩ የቀድሞ ፖሊሶች ከሥራ ውጭ የተደረግነው አለአግባብ ነው ብለው ነበር። በጉዳዩ ላይ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ፖሊስ ኮሚሽን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ