1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከተፈጥሮ ጋር ሰላም መፍጠር

ማክሰኞ፣ የካቲት 23 2013

አዲሱ የተመድ ዕቅድ ከአካባቢ ተፈጥሮ ጋር በተገናኘ የሚገጥሙ ችግሮችን ለማስወገድ አስቸኳይ ያለውን «የሰላም ዕቅድ» ነድፏል። ድርጅቱ አስቸኳይ መፍትሄ የሚያሻቸው ያላቸው ችግሮች የአየር ንብረት ቀውስ፣ የብዝሃ ሕይወት መመናመን እና ብክለት ናቸው። እነዚህ እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ያላቸውን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ መፍትሄ ያለውን ዕቅድ ነድፏል።

https://p.dw.com/p/3q6aI
Symbolbild Teamwork
ምስል Fotolia/shock

«የተመድ ያቀረበው ዘገባ»

የሰው ልጅ ከተፈጥሮ የተነጠለ ሳይሆን የዚያው አካል ነው። ሆኖም የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የገጠመው ጦርነት መኖሪያ ምድሩን እንዳልሆነ አድርጎ አሁን ያለ አማራጭ ባዶ እጁን እያስቀረው ነው ይላሉ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ።  ሰዎች በተለያየ መንገድ ተፈጥሮን እያራቆቱ መሄዳቸው እየዋለ ሲያድር በየፈርጁ ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን የሚያመላክቱ ክስተቶች እየታዩ ነው። የምድርን ጉዳት መረዳታቸውን የሚገልጹ ወገኖች የሰዎች ልጅ ከተፈጥሮ ጋር እርቅ ቢፈጥር እንደሚበጀው መምከር ጀምረዋል።

«ነገሩን ቀለል አድርጎ ለመግለጽ የፕላኔታችን ይዞታ ተበላሽቷል። ማሳያው ደግሞ ሰው በተፈጥሮ ላይ ጦርነት አውጇል። ይህ ደግሞ የራስን ሕይወት በራስ እጅ እንደማጥፋት ነው። ተፈጥሮ ደግሞ ሁልጊዜም የአጸፋ ጥቃት አለው። ይህንንም እያደረገ በመሆኑ ድርጊቱ ወደፊት በአስፈሪ ሁኔታ ቀጥሏል። »

ይላሉ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፤ ስጋታቸው ያተኮረው ጥንቃቄ የተለየው የሰዎች የየዕለት እንቅስቃሴ በተፈጥሮ ላይ ያሳደረው ጫና ያስከተለውን መዘዝ ማመላከት ላይ ነው። ዋና ጸሐፊው ስጋታቸውን ያሰሙት የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ተፈጥሮ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ቀውስ፣ የብዝሀ ሕይወት መመናመን እና ብክለት እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ ችግሮች መሆናቸውን ያመላከተበት ዘገባ ባለፈው ሳምንት ይፋ በሆነበት አጋጣሚ ነው።

BdTD Frankreich Korsika Ajaccio | Smog, Spaziergang
ምስል Pascal Pochard-Casabianca/AFP/Getty Images

«ከተፈጥሮ ጋር ሰላምን መፍጠር» የሚል ርዕስ የተሰጠው የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ የአየር ብክለት እየተባባሰ የአየር ንብረት ቀውስ አብሮ ሲያድግ፣ መዘዙ የብዝሀ ሕይወት መመናመንን አፋጥኖ አዳዲስ ወረርሽኞችን እንደሚጋብዝ ያመለክታል። ይኽ ደግሞ መፍትሄዎቹ አንዳቸው ከሌላቸው የማይነጣጠሉ መሆናቸውን አመልካችነቱንም ያትታል። ከዚህ ቀደም በድርጅቱ ይቀርቡ የነበሩ ዘገባዎች ችግሮቹን በተናጠል የሚያመላክቱ እንደነበር ነው የተገለጸው። ያ ደግሞ የየሃገራቱ መንግሥታት ችግሩን ነጣጥለው እንዲመለከቱና የሚሰጠው ትኩረትም እንዲሁ እንዲነጣጠል መንገድ እንደከፈተ ተነግሯል። ባለፈው ሳምንት በቀረበው አዲስ ዘገባ ግን ችግሮቹ እርስ በርስ የተቆላለፉ መሆናቸውን በማመላከት የጋራ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ምክረ ሃሳብንም ያካተተ ነው ተብሎለታል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በኢንተርኔት ግንኙነት በተካሄደው የተመድ የአካባቢ ተፈጥሮን የተመለከተ ጉባኤ ዋናው ትኩረት የምንኖርባት መሬት ጤና መሆን እንዳለበት ያመለከቱት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ልዩነቱን በመቶኛ በማስላትም ለማሳየት ሞክረዋል።

«በዕቅዶቻችንም ሆነ በፖሊሲያችን ማዕከላዊ ጉዳይ አድርገን መመልከት ያለብን የፕላኔታችንን ጤና መሆን አለበት። ኤኮኖሚው ግልጽ ነው፤ አብዛኛው ዓመታዊ ጥቅል ገቢያችን የሚገኘው ተፈጥሮ ላይ ተመርኩዞ ነው፤ ሆኖም የተፈጥሮ አቅማችን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ብቻ በ40 በመቶ ወርዷል።»

በዋናነትም መንግሥታትም ሆኑ ኅብረተሰቡ መረዳት ያለበት የአካባቢ ተፈጥሮ፣ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ፈተናዎች እርስ በእርሳቸው የተያያዙ መሆናቸውን ያመለከቱት ጉተሬስ፤ መፍትሄውን ለማግኘትም ሁሉንም አስተሳስሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህን ለማከናወን ያግዛል የተባለውን አዲሱን የምርምር ውጤት ካዘጋጁት አንዷ የሆኑት የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ተፈጥሮ መርሀ ግብር ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን በበኩላቸው ሁሉም ተባብሮ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2021 ከተፈጥሮ ጋር የሚደረገውን እርቅ መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል።

Öko-mode Biomode Mode Natur Umweltfreundlich
ምስል mago

«መሸነፍ አማራጭ አይደለም። የንግዱ ዘርፍ፣ ባለወረቶች፣ እንዲሁም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው 2021 ዓ,ም ከተፈጥሮ ጋር የምናደርገውን እርቅ የምንጀምርበት ለማድረግ ቆርጦ መነሳት አለበት።»

ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር እርቅ መስርተው የአሠራርና አኗኗር ዘይቤያቸውን ከመለወጥ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ያመላከቱት ደግሞ የ75ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላጉ ጉባኤ ፕሬዝደንት ቮልካን ቦዝኪር ናቸው።

«መሠረታዊና ወሳኝ ምርጫዎችን ማድረግ ይኖርብናል፤ ወይ በያዝነው መንገድ በመቀጠል ከፕላኔታችን የምንፈልገውን ሁሉ ለማግኘት ጫና ማድረግ፤ ወይም ምንም እንኳን አስቸጋሪነት ሊኖረው ቢችልም ባህሪያችንን አርቀን በዙሪያችን ካለው ዓለም ጋር ሚዛን ለመጠበቅ ግልኙነታችንን ወደስምምነት መውሰድ።»

ይኽ ሁሉ ስጋት ዋና መንስኤው 168 ገጾች ባሉት «ከተፈጥሮ ጋር ሰላምን መፍጠር» በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ዘገባ ለማሳየት መሞከሩን ያመለከቱት ከጸሐፊዎቹ አንዱ የሆኑት ሮበርት ዋትሰን፤ ባጭሩ ሲገልጹት፤ «ልጆቻች እና የእነሱ ልጆች የሚወርሷት ምድር የሚኖራት ጽንፍ የያዘ የአየር ጠባይ አይነት፤ ከፍታው የጨመረ ባሕር፤ ቁጥራቸው የቀነሰ ተክሎች እና እንስዳት፣ የምግብ እና ውኃ ዋስትና የሌለባት እንዲሁም ወረርሽኞች የሚበረክቱባት መሆኗን» እንደሆነ አመልክተዋል።

Libanon Tyre | Umweltverschmutzung durch Teer
ምስል Aziz Taher/REUTERS

እሳቸው እንደሚሉትም ይህ ዘገባ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደግምት ይነገሩ የነበሩት ከተፈጥሮ ጋር የተያያዙ ስጋቶች አስቸኳይ መፍትሄን የሚሹ እውነታዎች መሆናቸውን ማሳየት መቻሉንም አጽንኦት ሰጥተዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽም ዘገባው ያሳያቸውን አሳሳቢ ነጥቦች በማንሳት የዘንድሮው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ወሳኝ ርምጃዎች ሊወሰዱበት የሚገባ መሆኑን «መመለስ ወደማንችልበት ነጥብ እየደረስን ነው፤» በማለት አጣዳፊነቱን ለማመልከት ሞክረዋል። በጥናቱ የተሳተፉት ተመራማሪዎች እንደሚሉት የምድር ሙቀት በ3,5 ዲግሪ እየጨመረ መሄዱን፣ በየዓመቱም በአየር ብክለት 9 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች እየሞቱ መሆኑን፤ ምድር ላይ ካሉት 8 ሚሊየን አንድ ሚሊየን የሚሆኑት ወደ መጥፋት መቃረባቸው እየታየ ነው። ከ3 ቢሊየን የሚበልጠው የዓለም ሕዝብ ለምነቱን ካጣ መሬት ጋር ይታገላል፤ በየዓመቱም 400 ሚሊየን ቶን የሚሆን ከባድ የብረት ዘሮች እንዲሁም መርዛማ ፍሳሾች እና የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት ወደ መሬት የውኃ አካላት ይፈሳል፤ 7ከ400 የሚበልጡ ምንም አይነት ኦክስጅን የሌለባቸው የውኃ አካላት የተፈጠሩ ሲሆን ወደ ባሕርና ወንዞች የሚጣለው የፕላስቲክ ቆሻሻ ከፍተኛ ብክለት ፈጥሯል፤ ወደ 60 በመቶ የሚሆነው የዓሣ ክምችት በከፍተኛ መጠን እየተጠመደ በመጥፋት ላይ ነው።

ተፈጥሮ ላይ ያረፈ ይኽ ሁሉ ጫና ዞሮ ዞሮ የአጸፋ ዱላውን የሚሰነዝረው እኛው ላይ ነው ይላሉ ዘገባው ላይ በሳይንሳዊ አማካሪነት የተሳተፉት የስነተፈጥሮ ምሁሩ ቶማስ ላቭጆይ። የአሶሲየትድ ፕረስ የሳይንስ ጉዳዮች ጸሐፊ የሆነው ሴዝ ኖረንስታይን እንደሚለው በተመራማሪዎች ተዘጋጅቶ በመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ተፈጥሮ መርሃ ግብር አማካኝነት የቀረበው ዘገባ ችግሮቹን አጉልቶ ከማሳየት ባሻገር ዋነኛ አላማውን ይዘረዝራል።

Schlucht Wadi Qelt
ምስል dapd

«ዘገባው የችግሩን ግዙፍነት ብቻ አይደለም የሚናገረው፤ ይልቁንም አንዳንዶች በወጉ ትኩረት ሳይሰጡ ሊያልፉት ይችላሉና ዓለም አሁኑኑ አፋጣኝ በሆነ መንገድ አንዳች ርምጃ ይውሰድ የሚል ነው። ምክንያቱም በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ለውጥ እንዲኖር ይጠይቃሉ፤ መንግሥት ቀረጥ የሚወስደው ከየት ነው፤ የኤኮኖሚውን ውጤት እንዴት ነው የምናሰላው? ኃይልስ እንዴት ነው የምናመነጨው? የሰዎች እንቅስቃሴ እንዴት ነው? ዓሣ የምናሰግረው እንዴት ነው? እርሻችንስ? ምንስ ነው የምንመገበው? ይኽ ዘገባ ይኽን ሁሉ መለወጥ አለበት ይላል።»

ዓለም የተጋፈጠችውን የተፈጥሮ ቁጣ ለማረም እርስ በርሱ የተያያዘ የአካባቢ ተፈጥሮን ቀውስ በዘላቂነት ሊያስተካክል ይችላል የተባለው ዕቅድ የተመድ እስከ መጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2030 ድረስ ለማሳካት ካለመው ዘላቂነት ያላቸው የልማት ግቦች ጋርም እንደሚገናኝ ነው የተነገረው። ወደታለመው ግብ ለመድረስ ደግሞ እርስ በርሳቸው የተያያዙትን የአየር ንብረት ቀውስን፣ የብዝሃ ህይወት መመናመንና ብክለትን ለማረም የሚረዱ ተግባራትን ለማከናወን ሃገራት የየበኩላቸውን ሊያደርጉ ይገባል። ባለፈው ሳምንት የቀረበው ዘገባ ችግሮቹን በመዘርዘር የጋራ ርምጃ እንዲወሰድ ሁሉንም ለማንቃት ያለመ መሆኑን የሚናገሩት የመንግሥታቱ ድርጅት የአካባቢ ተፈጥሮ መርሀ ግብር ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን በተናጠል የተሞከረው ውጤት አላስገኘም።

«ቁንጽል የሆነ አቀራረብ ልንለው እንችላለን እዚህም እዚያም ኅብረተሰብና ኩባንያዎችም እንዲሁም ሃገራትን ያላሳተፈ ሥራ ካሰብንበት ሊያደርሰን አይችልም። ከ1990 አንስቶ የምናመርተው ካፒታል በእጥፍ አድጓል፤ የተፈጥሮ ማለትም መሬቱ፣ አየሩ፤ ውኃው፤ አፈሩ ወዘተረፈ የምንለው ካፒታል ግን እሴቱ በ40 በመቶ ቀንሷል።»

Antarktis Adelie Pinguin
ምስል picture-alliance/AA/O. Kizil

እሳቸው እንደሚሉትም ያልተቀናጀው የመፍትሄ ርምጃ የዓለም የሙቀት መጠን ከ3 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዲበልጥ እያደረገ ነው። ይኽ ሊያስከትን የሚችለውን መዘዝ ለመቀልበስ ታዲያ ምሳሌነት ያለው አቀራረብ ያስፈልጋል። የብዝሃ ሕይወት መመናመንን ለማዳን ተገቢውን ጥንቃቄና ጥበቃ ማድረግ፣ መሬትንም ከተፈጥሮ አቅሙ በላይ እንዲያመርት አለማስገደድ፣ ለተለያዩ ጥቅሞቻቸው ሲባል የሚታደኑ እንስሳትን መጠበቅ፤ ብክለትን መቀነስ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተላምዶ ለመኖር የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ አማራጭ የሌለው ከተፈጥሮ ጋር የመታረቂያው መንገድ መሆኑንም በማያዳግም መልኩ ገልጸዋል።

አንቶኒዮ ጉተሬሽ በበኩላቸው ተፈጥሮን የምንመለከትበትን መንገድ መለወጥ ያለውን እውነተኛ ዋጋ እንድናስተውል ይረዳናል ነው የሚሉት። ለፍጥረታት፣ ለልማት፤ ለጤና እንዲሁም ለደህንነታችን የምንሰጠው ዋጋ «የተፈጥሮ ካፒታል» መሆኑንም ያስገነዝባሉ። ይኽን ግንዛቤ በፖሊሶዎች፣ እቅዶችና በኤኮኖሚው ስርዓት ውስጥ እንዲታይ ማድረጉ ደግሞ ተፈጥሮ ከጉዳቷ እንድታገግም ስለሚረዳ በልዋጩ በጎ ጎኗን ልትሸልመን እንደምትችልም ተናግረዋል።

Weltspiegel 02.03.2021 | Indonesien Vulkanausbruch Mount Sinabung
ምስል Sastrawan Ginting/Antara Foto/REUTERS

ለተፈጥሮ ዋጋ ሊተመንለት እንደሚገባ ያስገነዘበው የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ የአየር ንብረት ላይ ጫና የሚያስከትለውን ብክለት ለምሳሌ ካርቦንን በዋጋ በመተመን፤ ከቅሪተአጽም የሚገኝ ነዳጅ ላይ የሚደረገው ድጎማ በዓለም ደረጃ ማቆም እንዳለበትም አሳስቧል።  በዓመት ከ5 ትሪሊየን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ለዚህ ዘርፍ እንደሚደረግ ነው የተገለጸው። ከተፈጥሮ ጋር ሰላምን ስለመፍጠር ያመለከተው ዘገባ ጎርጎሪዮሳዊው 2021 ዓ,ም እንዲህ ያሉ የድጎማ በጀቶች የዓለም የአካባቢ ተፈጥሮ በሚደግፉ መንገዶች ላይ የሚውልበት የመፍትሄ ጉዞ የሚጀመርበት መሆን እንደሚገባው ያሳስባል። 

ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በመላው ዓለም የሚከሰተው የተፈጥሮ ቁጣ መጠኑና ፍጥነቱ ጨምሮ በመሄድ ላይ ነው፤ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከባድ ዝናብና ጎርፍ፣ ከዚያም የመሬት መናድ፣ ከባድ ቅዝቃዜና በረዶ፣ ከባድ ሙቀትና ድርቅ፣ ሰደድ እሳት፣ እሳተ ጎሞራ እያልን የምንዘረዝረው የተፈጥሮ አደጋ ተበራክቷል። ለመፍትሄው ሰዎች የአኗኗር ልማዳቸውን ያስተካክሉ ነው የጥናቱ መልእክት፤ እንደታሰበው በየመንግሥታቱ የሚኖረው ተቀባይነትና ተግባራዊነት እንዴት ይሆናል? በዚህ ዓመት የምናየው ይሆናል። 

ሸዋዬ ለገሠ