የብክለት ሥጋት ያጠላበት የሀዋሳ ሐይቅ
ሰኞ፣ መጋቢት 30 2016ከኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች አንዱ የሆነው የሀዋሳ ሀይቅ ዙሪያ ሥፋቱ በ49 ኪሎ ሜትር ላይ የተንጣለለ ነው ፡፡ ሀይቁ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዓሳ ማጥመድና በጀልባ አስጉብኚነት ኑሯቸውን መሥርተውበታል ፡፡
የፍቅር ሀይቅ በሚል ቁልምጫ የሚጠራው የሀዋሳ ሀይቅ አሁን ላይ የተጋረጠበት አደጋ ፍርጀ ብዙ የሚባል አይነት ነው፡፡ ለወትሮው የፕላስቲክ ቆሻሻዎች የሚታዩበት የሀይቁ ዳርቻ አሁን ደግሞ ከፍተኛ የደልል ክምችት እየተስተዋለበት ይገኛል ፡፡
የሥጋቱ መነሻ በባለሙያዎች እይታ
በሀይቁ ዙሪያ የሚገኙ የጎርፍ መግቢያ ጎርጆች ላይ ልኬት መካሄዱን የጠቀሱት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ መምሪያ የአየር ብክለት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አመለወርቅ ገብሩ “ ውጤቱ ሊያነቃን የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል “ ይላሉ ፡፡
በሀይቁ የውሃ መግቢያዎች ላይ ባደረግነው ክትትል ሥፋቱ 12 ሜትር ጥልቀቱ ደግሞ 16 በሆነ የጎርፍ ጎርጅ አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው ደለል ወደ ሀይቁ እየገባ እንደሚገኝ የተናገሩት አስተባባሪው “ በእኛ ድምዳሜ መሠረት ሀይቁ አደጋ ላይ ይገኛል ፡፡ ሥራዎች ካልተሠሩ ውሎ አድሮ ሀይቁ ከእጃችን ሊያመልጥ ይችላል ፡፡ አሁን ላይ ደለሉን ለመከላከል በጎርፍ መውረጃ ጎርጆች ላይ ጋቢዎን የተባለ የደለል መከላከለያ ግድቦች ሊሠሩ ይገባል “ ብለዋል ፡፡
ሀይቁን የመታደግ ዘመቻ
አሁን ላይ የሀይቁ በደለል እየተሞላ መምጣት ያሳሰባቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የስካውት አባላት ከከተማ አስተዳደርሩ የአካባቢ ጥበቃ መምሪያ ጋር በመሆን አደጋውን የመቀልበስ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ ፡፡
በደለል ጠረጋና በቁሻሻ ማጽዳት ሥራው እየተሳተፉ ከሚገኙት የሲቪክ ማህበራት መካከል ጥምረት ለማህበራዊ ልማት ድርጅት አንዱ ነው ፡፡ በድርጅቱ የሀዋሳ ከተማና አካባቢው አስተባባሪ ሀገሬ ጌቱ “ የሀይቁ ሥነ ምህዳራዊ ሁኔታ አደጋ ውስጥ እየወደቀ ሥለመሆኑ በአይን የሚታይ ፣ ባለሙያ መሆንን የሚጠይቅ አይደለም “ ትላለች ፡፡
እንደማህበረሰብ ሀይቁ የሁላችንም ነው የምትለው ሀገሬ “ በተለይም ብዙዎች ኑሯቸውን የመሠረቱበት ፣ ነዋሪውም ሆነ ጎብኚው የሚዝናናበት በመሆኑ ደህንነቱን መጠበቅ ይኖርብናል ፡፡ ከዚህ በመነሳት ድርጅታችን ከሌሎች ጋር በመሆን የገባውን ደለል እና የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን የመጽዳት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል “ ብላለች ፡፡
የትብብር ጥሪ
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርር የአካባቢ ጥበቃ መምሪያ የአየር ብክለት ዘርፍ አስተባባሪው አቶ አመለወርቅ ገብሩ ሥራዎች ካልተሠሩ ሀይቁ ለከፋ ሥነ ምህዳራዊ ጉዳት ሊዳረግ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ይናገራሉ ፡፡ በመሆኑም እየመጣ ያለውን አደጋ በመከላከል ሀይቁን ከጉዳት ለመታደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሲሉ አስተባባሪው ጥሪያቸውን አቅርበዋል ፡፡
በተለይም ከከተማው የአካባቢ ጥበቃ መምሪያ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሥምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ባለሥልጣን እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋነኛ ባለድርሻ አካላት ናቸው ያሉት አስተባባሪው “የሀዋሳ ሀይቅን መሠረት አድርገው የመዝናኛ ሪዞርቶችን የገነቡ ባለሀብቶችም ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ፡፡ ያ ካልሆነ ነገ ላይ የሀዋሳው ሀይቅን የሚወድ ሊያዝን ይችላል “ ሲሉም አስጠንቅቀዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ