ከፍተኛ ስጋት የደቀነው የመሬት መንቀጥቀጥ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 2017አለመረጋጋት እየፈጠረ ያለው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ
በአፋር ክልል በትላንትናው ዕለት እና ከትናንት በስቲያ ሌሊት በተደጋጋሚ በሬክተር ስኬል ከ5 በላይ ሆኖ በተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በርካታ ቤቶች በመፍረሳቸው ነዋሪዎች አከባቢዎቹን ለቀው ለመሰደድ እየተገደዱ ነው፡፡
በክልሉ ገቢ-ረሱ ወይም ዞን 03 ውስጥ በዱለቻሳ ወረዳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ከፍ ብሎ በተስተዋለው ርዕደ መሬት ማህበረሰቡ መረጋጋት ተስኖት አከባቢውን መልቀቅ ጀምረዋል፡፡
አደጋው የቀሰም ስኳል ፋብሪካም በከፊል ስራው እንዲስተጓጎል ማድረጉን የፋብሪካው ኃላፊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
ሀሰን ካሚል በአፋር ክልል ዱለቻ ወረዳ የድሩፉሊ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በወርሃ መስከረም መጨረሻ ጀምሮ በተከታታይ ከተከሰተ በኋላ በመሃል እፎይታ የሰጠው የአዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰሞኑ ከፍቶ ቤቶችን እስከማፈራረስ በመድረሱ እሳቸውን ጨምሮ በርካቶችን ማፈናቀሉን አስረድተዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሌሊት በተከሰተው የመሬት መንቀትቀት ብቻ ከ20 በላይ ቤቶች እና ሱቆች መውደማቸውን የሚገልጹት ነዋሪው የመሬት መንቀጥቀጡ ትናንትም ሆነ ዛሬ ቀጥሎ “መሬት እየተርገበገበች ነው” ብለዋል። “እኛ ጋ አሁን እየባሰ ነው፡፡ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ወደ 20 ሺህ ህዝብም መኖሪያቸውን ጥለው በሰቆቃ ተፈናቅለዋል” ነው ያሉት፡፡
የበረታው የነዋሪዎች ስጋት
በዱለቻ ወረዳ ሳጋንቶ እና ድሩፉሊ ቀበሌያት የደረሰው አደጋ ይከፋል የሚሉት የአከባቢው ነዋሪ በብዛት ሰዎች የተፈናቀሉም ከዚህ አከባቢ ነው ብለዋል፡፡ በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በኩልም ቀበና እና ሳቡሬ ቀበሌዎች ተመሳሳይ አደጋዎችን እያስተናገዱ ነው ተብሏል፡፡ “ሳቡሬም ቤቶችን አፍርሷል ግን ሰው አላፈናቀለም፡፡ ትልቁ ስጋት ያመጣው ከሰም ስኳር ፋብሪካ ያለበት ሁለት ቀበሌ ላይ ነው፡፡ መሬት ተሰንጥቋል፡፡ ከፍተኛ ድምጽም እየተሰማ ነው” በማለት አሁንም ከአከባቢው ያልወጡ የማህብረሰብ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
በተሰነጠቀ መሬት ውስጥ የሚወጣ ከየት መጣ ማይባል ውሃ አከባቢውን ማጥለቅለቅ ጀምሯልም የሚሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ የቀሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኛ እና ለዘመናት በአከባቢው የኖሩ፤ አንዳንድ ተራራማ ስፍራዎች ላይ እንደ እሳተ ገሞራ ያለ ፍም ያለው ጭስ እየታየም ነው ሲሉ አስተያየታቸው አክለዋል፡፡ “መሬቱ ሲፈነዳ እንደ ምንጭ ውሃ እያፈለቀ ኃይቅ ነገር ፈጥራል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው በአከባቢው በሚገኙ ፈንታሌ እና ዶፋን በተባሉ ሁለት ትላልቅ ተራራዎች ላይ ርዕደቱ ሲከሰት ከፍተኛ ድምጽ እንደሚሰማም አስረድተዋል፡፡
በመላው ዓለም የደረሱ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶችን የሚመዘግቡ ተቋማት አዋሽ አካባቢ ከሰሞኑ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጦች መድረሳቸውን እያስታወቁ ነው።የጀርመን ጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል እስካሁን ሬክተር ስኬል 5.1 የሚለካ ከፍ ያለ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን መረጃ አውጥቷል።
በአፋር ክልል ዱለቻ ወረዳ ድሩፉሊ ቀበሌ ቀበና አከባቢ ለውስን ሰከንዶች የቆየው የመሬት ርዕደት እቃዎችን እስከመሰባበርም መድረሱን ዶቼ ቬለ ከነዋሪዎች ተረድቷል፡፡ “አሁን እያወራን እራሱ መሬት ይንቀጠቀጣል፡፡ ዶፋን ተራራ አከባቢ እሳት ታይቷል” በማለት ቤቶች ወድቀው እቃዎች ሲሰባበሩ ሰው ከቤት ውስጥ ስለሚወጣ ሰው ላይ ግን ጉዳት አለመድረሱን አስረድተዋል፡፡
ነዋሪዎችን የመታደግ ቀጣዩ ተግባር
ዶቼ ቬለ የነዋሪዎቹን ስጋት እና የታሰበው እልባትን በተመለከተ ከዱለቻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ደስታ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የእጅ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብደውልም ስልካቸው ስለማይነሳ ጥረቱ አልተሳካም፡፡ የቀሰም ስኳር ፋብሪካ ስራ አስከያጅ አቶ አሊ ሁሴን ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ግን የፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የዞንና የሁለቱ ወረዳ አመራሮች ጋር በመሆን በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ “የፋብሪካው ሰራተኞች በመረበሽ ላይ ናቸው መሬቱም እየተሰነጣጠቀ ያለበት ድግግሞሹ እየጨመረ ነው” ያሉት ኃላፊው “ሰው መተኛት የማይችልበት የስነልቦና መቃወስ ላይ ደርሷል” ብለዋል፡፡ በአከባቢው የቀሰም ግድብ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ የተዛባ መረጃ መሰራጨቱንም የገለጹት ኃላፊው ግድቡ ላይ እስካሁን ግን ምንም አደጋ አለመከሰቱን ገልጸዋል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ ግን ቤቶችን ከማፈራረስ ጀምሮ ከጅቡቲ ዋና መንገድ ወደ አዋሽ 40 በመገንጠል ወደ ፋብሪካ የሚወስደውን አነስተኛ መንገድ መሰንጠቁን ያረጋገጡት የፋብሪካው ኃላፊ እየተፈጠረ ባለው የማህበረሰቡ ስነልቦና መቃወስ የፋብሪካው ስራ መስተጓጎሉ የማይቀር ነው ብለዋል፡፡ “ይህ የተፈጥሮ አደጋ በመሆኑ ቅድሚያ ለሰው ህይወት ስለምንሰጥ የፋብሪካው ስራ መስተጓጎሉ አይቀርም” በማለት እስካሁን አገዳ ምርት እና የተወሰኑ ስራዎች ግን በከፊል እየተሰሩ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡
በአከባቢው እየተደጋገመ የመጣውን መሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ ከአከባቢው ጀምሮ እስከ ፌዴራል ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት አደጋው ከመድረሱ አስቀድሞ የቅድመ ዝግጁነት ስራ እንዲሰሩ ባለሙያዎች መጠየቃቸውንም ከሰሞኑ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ