የመንገድ መዘጋት በምዕራብና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች
ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 2016የመንገድ መዘጋት በምዕራብና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች
በአማራ ክልልም በምዕራብና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች ያሉ መንገዶች በመዘጋታቸው ነዋሪዎቹ ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን ተናግረዋል፣ ችግሩ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና ፈጥሯል ተብሏል፡፡ እንደነዋሪዎቹ የመንገዶች መዘጋጋት 6 ቀናትን አስቆጥሯል፡፡
እንቅስቃሴዎቹ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ መቆማቸውን ዶይቼ ቬሌ ያነጋገራቸው የምዕራብ ጎጃምና የምስራቅ ጎጃም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ የመንገዶች መዘጋጋት በተለይ ለስራ ወደ ሌላ ቦታ የሄዱ ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዳመለሱ ማድረጉን፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ በተሰማሩ ሰዎች ላይም የኢኮኖሚ ጉዳት ማድረሱን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡
ጫናው በተለይ ለወላዶች ፈተና እንደሆነባቸው በሰሜን ጎጃም ዞን የጎንጂ ቆለላ ነዋሪ አመልክተዋል፡፡
“... እውነት ለመናገር መንገድ መዘጋቱ ህብረተሰቡን ነው እንጂ የሚጎዳው የሚጠቅም ነገር የለውም፣ እናቶች አሉ፣ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ ሄደው መውለድ የማይችሉ፣ በእግራቸው እስከ ሞጣ የሄዱ አሉ (በግምት ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ) ጉዳዩ በጣም አስቀያሚ ነው፡፡”
በምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ ከተማ ነዋሪ የመንገድ መዘጋጋቱ በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ ስራ በተሰማሩ ወገኖች ላይ የኢኮኖሚ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡
“ በአጭር ጊዜ ለሚበላሹ ምግቦች መንገዱ መዘጋቱ ጫና ፈጥሯል፣እኔ በዓይኔ ያየሁት በእኛ አካባቢ ቃሪያ የጫነ ልጅ አለ፣ ቃሪያውን ጭኖ ዝናብም እየዘነበ ስለሆነ፣ ችነቱ ምንገድ ላይ በመቆሙ ቃሪያው ተበላሸበት፤ ሙዝ፣ ቲማቲም የመሳሰሉት አትክልቶች እየተበላሹ ነው፡፡ለተጠቃሚው አይደርሱም፣ ለአቅራቢዎች ደግሞ የኢኮኖሚ ክስረት እያደረሰ ነው፡፡ ”
በምስራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና ከተማ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው መንገዶች በመዘጋጋታቸው መኪናዎች በየቦታው መቆማቸውን አስረድተዋል፣ ለተለያየ ስራ ከቤታቸው ወጥተው የነበሩ ሰዎችም መንገድ በመዘጋቱ አስፈላጊ ላልሆነ ወጪ ተዳርገዋል ብለዋል፡፡
ሌላ የዚሁ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በመንገድ መዘጋት ምክንያት በተራራቀ ቦታ ሰርጋቸውን ያደረጉ ሴትና ወንድ ሙሽሮች ሳይገናኙ በያሉበት ሰርጋቸውን ለማክበር መገደዳቸውን ነው የገለፁልን፡፡
“ ሙሽሮቹ በተለያየ ቦታ ነው የሚኖሩት፣ ከቀበሌ ወደ ቀበሌ የትራንስፖርት አገልግሎት የለም፣ እንደዚያ ስለሆነ ሙሽራዋም በቤቷ፣ሙሽራውም በቤቱ ሰርጋቸውን አሳልፈዋል፣ የሙሽረራዋ አገር ደብረወርቅ የትመን የሚባል አካባቢ ነው፣ የሙሽራው ደግሞ ቢቸና ነው፡፡ በእግር አይደረስም መንገድ ዝግ ነው እንዴት ይገናኙ?”
በአማራ ክልል አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት በቀሩት ግጭት በርካቶች ሲሞቱ ሌሎች ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡የኢትዮጵያ መንግስት ግጭቱን አስመልክቶ ለሁለት ጊዜ የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዚህ ሳምንት የሚጠናቀቅ ሲሆን አዋጁ ለሌላ ጊዜ ስለመራዘሙም ሆነ ስለማብቃቱ እስካሁን ድረስ የተባለ ነገር የለም፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ