የሰሞኑ የአዲስ አበባ የነዳጅ ሰልፍ
ረቡዕ፣ መጋቢት 25 2016አዲስ አበባ ዉስጥ የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ባለፉት ጥቂት ቀናትነዳጅ በሚፈልጉ ተሽከርካሪዎች ሠልፍ ተጨናንቀዋል።በወራት ማብቂያ ቀናትና የነዳጅ ዋጋ ለወጥ በሚደረግበት ሰሞን በየነዳጅ ማደያዉ ረጃጅም ሰልፎችን ማየት የተለመደ ቢሆንም የሰሞኑ ግን ለብዙዎች እንግዳ ሆኗል። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ግን የነዳጅ እጥረቱና የረጃጅም ሠልፉ ምክንያት ጅቡቲ ዉስጥ የጣለዉ ከባድ ዝናብ እንደሆነ አስታዉቋል።ድርጅቱ እንደሚለዉ ችግሩን ለማቃለል ከነዳጅ ማከማቻ ዲፖዎች ነዳጅ እየተጫነ ለከተማው እየቀረበ ነዉ።ኢትዮጵያ ከነዳጅ ፍጆታዋ 80 በመቶዉን የምታስገባዉ በጅቡቲ ወደብ በኩል ነዉ።
ነዳጅ ለመቅዳት የተስተዋለው ሰልፍ ዋነው ምክንያት
አንድም በወራት ማብቂያ ቀናት፣ በሌላ በኩል የነዳጅ ዋጋ ክለሳ መኖሩን የሚገልጽ የጭምጭምታ መረጃ ሲወጣ የሚታየው የአዲስ አበባ የነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም የተሽከርካሪዎች ሰልፍ ትናንትና ከትናንት በስቲያ እንዲሁም ዛሬ በስፋት ተስተውሏል። አንዳንድ ማደያዎች ደግሞ ነዳጅ እንደሌላቸው በመግለጽ ማደያቸው ባዶ ሆኖ ታይቷል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አለማየሁ ፀጋዬ ሰሞነኛው የነዳጅ እጥረት ያስከተለው ነዳጅ የመቅዳት ሰልፍ ፤ ጅቡቲ ላይ የዘነበ ከባድ ዝናብ ያስከተለው መስተጓጎል እንደሆነ ገልፀዋል።
"የዝናብ ጉዳይ ነው። ዝናቡን ምንም ማድረግ አይቻልም፣ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው ይሄ። ሆኖም ግን ከዴፖ ነዳጅ ወጪ ሆኖ እየተሰራጬ ነው ያለው። ችግሩን ለማቃለል"
የአሽከርካሪ አስተያየት
አንድ ነዳጅ ጫኝ ቦቴ ተሽከርካሪ 48 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንደሚጭን የነገሩን አቶ መኮንን ለማ የተባሉ አሽከርካሪ የነበሩና አሁን በግል ሥራ የተሰማሩ ሰው የነዳጅ እጥረት በከተማው ቢስተዋልም እንደከዚህ ቀደሙ በቀን 300 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ከጅቡቲ ነዳጅ ይዘው እየገቡ መሆኑን ገልፀዋል። ጅቡቲ ውስጥ ያለው የነዳጅ ማከማቻ ዲፖም ሆነ ነዳጅ ወደ ተሽከርካሪዎች የሚሞላው ማሽንም ችግር እንዳልገጠመው ገልፀዋል። ይህ በሆነበት የሰሞኑ የነዳጅ እጥረት ምንጭ ምን እንደሆና ግልጽ እንዳልሆነላቸው የነገሩን እኒሁ ሰው ለአዲስ አበባ ሱሉልታ ከሚገኘው የነዳጅ ዲፖ ነዳጅ እየተጫነ መሆኑንም ገልፀዋል።
"ቀደም ሲልም በቀን 300 መኪና ነው የሚጫነው ፤ ያ 300 መኪና እየተጫነ ነው ያለው። ጎርፉም ቢሆን ከተማው ውስጥ ነው ያለው እንጂ ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ከሚገኙበት አካባቢ ላይ አይደለም ጎርፍ ያለው"
ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ኅልውና ያላት ሚና
ጅቡቲ ላይ ዝናብበመዝነቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የነዳጅ እጥረት መከሰቱን የሚገልፀው ምክንያት ኢትዮጵያ በጅቡቲ ላይ ምን ያህል ጥገኛ መሆኗን በግልጽ የሚያመለክት ብሎም ሀገሪቱ እንቅስቃሴዋ ምን ያህል በየብስ ማጓጓዣ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላት መሆኑን ያመለክታል።
"ኤርትራ ራሷን የቻለች ሀገር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ጅቡቲ በኢትዮጵያ ዓይን ስትታይ ፋይዳዋ ጎልቶ የወጣ እንዲሆን ሆኗል" የሚሉት ስማቸውን ትተው ሀሳባቸውን የሚያጋሩን የዓለም አቀፍ ሕግና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ፤ ጅቡቲ በኢትዮጵያ የፀጥታ፣ የደኅንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራት ተጽዕኖ እና ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳሉ።
"የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት መነሳትን ተከትሎ ለኢትዮጵያ እንደ ጉሮሮ ሆናለች ጅቡቲ"
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ዓለማየሁ ፀጋዬ ኢትዮጵያ በየእለቱ ከ 2 እስከ 2.5 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እንዲሁም ከ8 እስከ 8.5 ሚሊየን ሊትር ናፍጣ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል ብለዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ