1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎች

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 2017

"አራት በመቶ ነው የጨመረው፣ የተወሰነ ገበያ ውስጥ ያለውን ብድር የማግኘት ችግር በጥቂቱ ሊፈታው ይችላል እንጂ ሙሉ ለሙሉ አይፈታውም"። ባለሙያ

https://p.dw.com/p/4ojRt
Addis Abeba in Äthiopien
ምስል Seyoum Getu/DW

የባንኮች የማበደር ጣሪያ ጨመረ

የንግድ ባንኮች በየዓመቱ ለደንበኞቻቸው የሚሠጡት የብድር መጠን ከነበረበት 14 በመቶ ወደ 18 በመቶ እንዲያድግ ወሰነ።

ውሳኔው ባንኮች ባለፈው ዓመት ይሰጡት ከነበረው የብድር ጣሪያ በዚህኛው ዓመት በአራት በመቶ ጨምረው እንዲያበድሩ የሚያግዝ ነው።

አዲሱ የባንኩ ውሳኔ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስና የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመን መኖሩን ለማረጋገጥ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን አሁን ባለበት 15 በመቶ ሆኖ እንዲቆይ ያዛል።

የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ የያዘው ቁልፍ ጉዳይ

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ የቅርብ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ "አበረታች" እና በጥቅሉ "የመርገብ አዝማሚያ ቢያሳይም"፣ ጠበቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ የመጠቀም አስፈላጊነት ላይ በመቀጠሉ ረገድ እምነት መኖሩን አስታውቋል።

ኮሚቴው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነስ ህዳር 2017 መጨረሻ 16.9 በመቶ መድረሱን እና ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ከተመዘገበው ዐኃዝ ዝቅተኛው ነው ብሏል፡፡ 

በአኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው ጠቅላላ ገንዘብ እና የሀገር ውስጥ ብድር ጨምሯል ያለው ብሔራዊ ባንክ ያም ሆኖ ግን የገንዘብ ዝውውር አመልካቶች የመቀነስ አዝማሚያ እንደታየባቸው ጠቅሷል።

ብሔራዊ ባንክ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስና የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመን መኖሩን ለማረጋገጥ በሚል ባንኮች የሚሰጡትን የብድር መጠን ዕድገት ከፍ አድርጎታል። ይህም ባለፈው ዓመት 5 ቢሊየን ብር ያበደረ ባንክ ቢኖር በዚህ ዓመት የዚያን 4 በመቶ ያህል ጨምሮ ማበደር ይችላል ማለት ነው።

27 ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ የተባለ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የባንክ ባለሙያ የሆኑት አቶ አስቻለው ታምሩ ይህ አዲስ ውሳኔ በበጎ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"በርካታ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ አሁን ግብይቶችን፣ የገንዘብ ዝውውሮችንም በተለይ በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት እየከወነ ነው። ስለዚህ በኢኮኖሚው ላይ ያለው የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ከመቀነስም አንፃር እና የዋጋ ግሽበትንም ከመቆጣጠር አንፃር ብሔራዊ ባንክ ጠቃሚ መመሪያዎችን እያወጣ ነው ያለው"።

ውሳኔው የገንዘብ ብድር ፍሰት ላይ የሚኖረው አወንታዊ ሚና

የብሔራዊ ባንክ አንደኛው ዋና ዓላማ ገበያው ገንዘብ ሲያስፈልገው በመጨመር እና ሲበዛ በመቀነስ ዋጋን ማረጋጋት ነው የሚሉት የኢኮኖሚ አማካሪ እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት ታደሰ ይህ ውሳኔ አዳዲስ እና አቅማቸው አናሳ የሆኑትን ባንኮች በተመለከተ የተለየ የብድር መጠን ቢያስቀምጥ የተሻለ ይሆን እንደነበር ይገልፃሉ።

"አራት በመቶ ነው የጨመረው፣ የተወሰነ ገበያ ውስጥ ያለውን ብድር የማግኘት ችግር በጥቂቱ ሊፈታው ይችላል እንጂ ሙሉ ለሙሉ አይፈታውም"። 

ብሔራዊ በንክ ያስቀመጠው የባንኮች የማበደር መጠን ገደብ ያልተገባ የገንዘብ ፍሰትን በመቀነስ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የሚል ምክንያትነት ቀርቧል።
ብሔራዊ በንክ ያስቀመጠው የባንኮች የማበደር መጠን ገደብ ያልተገባ የገንዘብ ፍሰትን በመቀነስ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የሚል ምክንያትነት ቀርቧል።ምስል Solomon Muche/DW

ብሔራዊ በንክ ያስቀመጠው የባንኮች የማበደር መጠን ገደብ ያልተገባ የገንዘብ ፍሰትን በመቀነስ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የሚል ምክንያትነት ሲቀርብበት በሌላ በኩል ዜጎች ከባንኮች ብድር በመውሰድ የሚያደርጉትን የሥራ እንቅስቃሴ ገድቧል የሚል መከራከሪያ ሲቀርብበት ቆይቷል። 

አሁን ይህ ማሻሻያ ሊመጣ የቻለው ከምን መነሻ ይሆን የሚለው ላይ አቶ አስቻለው ታምሩ ተከታዩን ብለዋል።

"ምናልባት ይህ የዋጋ ግሽበቱን በተወሰነ ደረጃ ብሔራዊ ባንክ እየተቆጣጠረው መሆኑን እና በተወሰነ ደረጃ የኢኮኖሚ መረጋጋትም ስላለ ለዚያ ነው 14 በመቶ ላይ ተገድቦ የነበረው ወደ 18 በመቶ እንዲጨምር የሆነው"።

የባንኮች ማህበር ጉዳዩን በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ አስተያየት እንደሚሰጥበት ለዶቼ ቬለ ገልጿል።
የባንኮች ማህበር ጉዳዩን በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ አስተያየት እንደሚሰጥበት ለዶቼ ቬለ ገልጿል።ምስል MICHELE SPATARI/AFP

ሌሎች የባንኩ ውሳኔዎች ምንድን ናቸው ?

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ባንኩ ለንግድ ባንኮች የሚሰጣቸው የአንድ ቀን ተቀማጭ ሒሳብ አገልግሎት፣ ባንድ ቀን የብድር አገልግሎት ላይ የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሒሳብ ባለበት እንዲቀጥሉ ወስኗል።

የባንኮች ማህበር ጉዳዩን በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ አስተያየት እንደሚሰጥበት ለዶቼ ቬለ ገልጿል።

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ የግል የንግድ ባንኮች ከዚህ በፊት የተቀመጠው 14 በመቶ የማበደር ጣሪያ ላይ የደረሱ አይደሉም። በሌላ አገላለጽ በተፈቀደላቸው ልክ ማበደር አልቻሉም። በሀገሪቱ ያለው የኢኮኖሚው መቀዛቀዘ እና የባንኮቹ አቅም አነስተኛ መሆን ለዚህ በምክንያትነት ይጠቀሳል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁን የተደረገው አራት በመቶ የማበደር መጠን ዕድገት ውሳኔ ብድር የመስጠትና የማግኘት ነፃነት ላይ ውስን ቢሆንም በጎ ውጤት ያለው መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ