1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታህሳስ 22 ቀን 2017 የዓለም ዜና

Yohannes Gebreegziabherማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2017

https://p.dw.com/p/4oiCq

በታጣቂ ልጆቻቸው ምትክ የሚታሰሩ ወላጆች ስሞታ

በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ልጆቻቸው ከታጣቂዎች ጋር ተቀላቅለዋል የተባሉ  17 ሰዎች መታሰራቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ለዶቼቨለ ተናግረዋል፡፡ ሰዎቹ የታሰሩት «ልጆቻችሁ አምጡ» ተብለው እንደሆነም ያነጋርናቸው የታሳሪ ቤተሰቦች  አመልክተዋል፡፡  ለሰባት ወራት ያህል በወረዳው ያለፍርድ ታስረው ከነበሩት አርሶ አደሮች መካከል የተወሰኑት በህዳር ወር 2017 ዓ.ም ከእስር ተለቀው የነበረ ቢሆንም «ልጆቻቹ ከጫካ አልተመለሱም» ተብለው ድጋሚ የታሰሩ ሰዎችም መኖራቸውን ለአሶሳው ወኪላችን ነጋሳ ደሳለኝ ገልጸውለታል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ምላሽ የጠየቅናቸው የአሙሩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዲንሳ ዱጉማ ‹‹ ቤተሰብ ልጆቹን ከቻለ እንዲያመጣ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ቤተሰብ መያዙ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን 130 የተባለው ውሸት ነው፡፡ በየጊዜው እየጠየቅን፣እያጣራን ልጆቻቸውን እንዲያመጡ  አንድ ወርና ሁለት ወር  ይሰጣቸዋል፡፡ ታስረውም ብዙዎች እየተለቀቁ ነው» ብለዋል።
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ 130 የሚደርሱ ሰዎች በወረዳው ለ7 ወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው መቆየታቸውን ጥቆማ እንደደረሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ መግለጹን ይታወሳል፡፡ 

ደቡብ ሱዳን ያቋረጠችውን የድፍድፍ ነዳጅ ማምረት እጀምራለሁ አለች

ደቡብ ሱዳን ያቋረጠችውን የድፍድፍ ነዳጅ ማምረትና ወደውጭ የመላክ ስራዋን እንደምትጀምር አስታወቀች። የነዳጅ ምርቱ የተቋረጠው በሱዳን በሁለቱ ጀነራሎች ሲካሄድ በነበረው ውግያ ባለፈው የካቲት ወር የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ላይ ጉዳት ስለደረሰበት ነው ተብሏል።
እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2011 ነጻነቷን የተቀዳጀችው ደቡብ ሱዳን ከአጠቃላይ የሱዳን የነዳጅ ክምችት ሁለት ሦስተኛው በግዛቷ የሚገኝ ቢሆንም በውስጥ ባለው የእርስበእርስ ጦርነትና ስር የሰደደ ሙስና ምክንያት ከነዳጅ ሃብቷ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳልቻለች ዘገባዎች ያመለክታሉ። 
የነዳጅ ምርት ባለስልጣናት ምርቱን ለመጀመር ማቀዳቸውን ቢገልጹም ትክክለኛው የሚጀመርበት ጊዜ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል ያለው የፈረንሳይ የዜና አገልግሎት ከገለልተኛ ምንጭ ለማረጋገጥ እንዳልቻለም ዘግቧል።

በእስራኤል ጥቃት የጋዛ የጤና ሥርዓት መውደሙን

እስራኤል በጋዛ ላይ በፈጸመቻቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች «የጤና ሥርዓቱ በመውደቅ አፋፍ ላይ ይገኛል» ሲል  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ። ዛሬ ይፋ የተደረገው የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ሪፖርት እንዳለው እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃቶች የፍልስጤማውያን የጤና ጥበቃ ሥርዓት በመውደቅ አፋፍ ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል።
እስራኤል በሆስፒታሎችና አቅራቢያቸው ላይ በምትፈጽማቸው ጥቃቶችና ውግያዎች የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱ ወደ ሙሉ ውድቀት አፋፍ አድርሶታል ያለው መግለጫው በዚህም ምክንያት የጤናና የሕክምና አገልግሎቶች ለፍልስጤማውያን ተደራሽ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል ማለቱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።

የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን

በኢራን ይደገፋሉ ተብለው በምዕራባውያን ሃገራት የሚከሰሱት የየመን ሁቲ አማጽያን ቴልአቪቭ በሚገኘው አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በእየሩሳሌም በተመረጡ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ። የአማጺው ቃልአቀባይ በአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይም ጥቃት አድርሰናል ብለዋል።
የሁቲ አማጽያን በዛሬው ዕለት ቴልአቪቭ በሚገኘው የቦንጎሪዮን አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና  በእየሩሳሌም ጥቃት መፈጸማቸውን ቢገልጹም ስለደረሰው ጉዳት ግን ያሉት ነገር የለም።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ከየመን ሁቲዎች የተተኮሱ ሚሳይሎችን ማክሸፉን ገልጿል። በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ በማከል። አንዳንድ የአይን ምስክሮች ግን በእየሩሳሌም አቅራቢያ ከፍተኛ ፍንዳታን ያስከተሉ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ገልጸዋል ሲል የዘገበው የጀርመን ዜና አገልግሎት ነው።

የጀርመን መራሄ መንግስት የአዲስ ዓመት መልዕክት

የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ የጀርመን ሕዝብ ፈተናዎችን ለማለፍ በአንድነት መቆም እንዳለበት አሳሰቡ። ሾልስ አዲሱን የጎርጎሮሳውያኑ 2025 ምክንያት በማድረግ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ጥንካሬ የሚመጣው ከህብረት ነው ብለዋል።
የማግድቡርጉን የገና ገበያ ጥቃት ያወሱት መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ አደጋው በደረሰበት ወቅት የህክምና ባለሙያዎችና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ላደረጉት ሙያዊ ድጋፍ አመስግነዋል። 
እኛ የአለመግባባትና የግጭት አገር አይደለንም ያሉት ሾልስ ጀርመን የመተባበር አገር እንደሆነች ገልጸዋል። በመጨረሻም ለመላው ጀርመናውያን  አዲሱ ዓመት የደስታ ጊዜ እንዲሆን ተመኝተዋል ፤

«ውድ ወገኖቼ! እጣ ፈንታችን በእጃችን ነው። 2025 መልካም ዓመት ማድረግ እንችላለን፤ እርስ በእርስ በመከባበር፣ እርስ በእርስ በመተማመን፣ አንዳችሁ ለሌላኛው በመተሳሰብና በመረዳዳት። ውድ ወገኖቼ በዚህ አመለካከት ጀርመን ለወደፊት ብሩህ ተስፋን ማየት ትችላለች። ለሃገሬ የምመኘው ይሄ ነው። እና ለእርስዎና ለምትወዱአቸው ሰዎች በሙሉ መልካም ምኞቴን ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ፤ መልካም አዲስ ዓመት!።»
የጎርጎሮሳውያን አዲስ አመት ለመቀበል ጀርመንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለማችን ከተሞች ዛሬ እኩለ ሌሊት ላይ በርችት ይምቦገበጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

«ማንም አያስቆመንም» ቻይና

ታይዋንን ወደ ቻይና ለማዋሃድ የምናደርገው ጥረት ማንም ሊያስቆመን አይችልም ሲሉ የቻይናው ፕሬዚደንት አስጠነቀቁ። ፕሬዚደንት   ዢ ጂንፒንግ ዛሬ እኩለ ሌሊት የሚቀበሉትን አዲሱን የጎርጎሮሳውያኑ 2015 አመትን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት በደሴቲቱ ውስጥም ሆኑ በውጭ የሚገኙትን የነጻነት ሃይሎችን አስጠንቅቀዋል።
የታይዋን እና የቻይና ሕዝብ አንድ ቤተሰብ ነው ያሉት ዢ ጂንፒንግ ይሕን የተሳሰረ ገመድ መበጠስ አይቻልም ሲሉ ተደምጠዋል። ከታይዋን ጋር የሚደረግ ውህደት የማይቀር መሆኑን በማከል።
ቻይና ታይዋን እንደ አንድ የግዛቷ አካል አድርጋ የምትመለከታት ሲሆን ታይዋን በበኩሏ ነጻ ሉአላዊ ሐገር ሆና መቀጠሉን ትመርጣለች። በመሆኑም ቻይና ታይዋን ዓለምአቀፍ ግንኙነቶችን እንዳታደርግና በግዛቷ ሥር ለመጠቅለል ከምን ጊዜውም በላይ አጥብቃ እየሰራች እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

ሩስያና ዮክሬይን መጠቃቃታቸውን እንደቀጠሉ ነው

ሩስያ በሰሜን ዩክሬይን ግዛት በምትገኘው የሾትካ ከተማ ባካሄደችው የሚሳይሎች ጥቃት በርካታ የትምህርት ተቋማትና የስቪል ህንጻዎችን ማውደሟን የከተማዋ ከንቲባ ገለጹ። ሩስያ በበኩሏ ዩክሬይን በምዕራባዊ ግዛቴ በምትገኘው ስሞልንስክ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት በአንድ የነዳጅ ማከማቻ ላይ ውድመት ደርሷል ብላለች።
ከክዬቭ በስተደቡብ ምስራቅ 250 ኪሎሜትሮችን ርቃ የምትገኘው የሾትካ ከተማ ከንቲባ ኒኮላ ኖሃ ዛሬ በፌስቡክ ገጻቸው ያስነበቡትን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA እንደዘገበው 12 የመኖሪያ ሕንጻዎችና 2 የትምህርት ተቋማት በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል። 
በምዕራባዊ የከተማዋ መንደሮች ላይም የሚሳይሎች ድብደባ መድረሱን የገለጹት ከንቲባው በሰው ሕይወት ስለደረሰ ጉዳት ግን ያሉት ነገር የለም።
በተመሳሳይ ዜና የክየቭ ከተማም በሩስያ የክሩዝና ባልስቲክ ሚሳይሎችና ድሮኖች ስትደበደብ ማደሯን ዜናው አክሏል። የጥቃቱ ዒላማ በከተማዋ ያለ የአየር ሃይል ወታደራዊ ሰፈር ሳይሆን እንደማይቀር ዘገባዎች ያመላክታሉ። 
ሩስያ በበኩሏ ዩክሬይን በምዕራባዊ ግዛቴ በምትገኘው ስሞልንስክ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት በአንድ የነዳጅ ማከማቻ ላይ ውድመት ደርሷል ነው የተባለው። ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው በአካባቢው ለጥቃት ከተሰማሩት 10 የዩክሬይን ድሮኖች ተመትተው መውደቃቸውንና አንዱ የተመታው ድሮን በነዳጅ ማከማቻ ላይ በመውደቁ ፍንዳታው ሊከሰት እንደቻለ ታውቋል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ታምራት ዲንሳ
 


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።