መቃድሹ፤ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር የሶማሊያ ጉብኝት
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር ወደ ሶማሊያ መጓዛቸውን የመቃዲሹ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን የጠቀሰው የሮይተርስ ዘገባ አመለከተ። ሮይተርስ አክሎም የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ኦማር፤ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ ወደ መቃዲሹ መጓዛቸውን ቢያረጋግጡም፤ ለምን ጉዳይ የሚለውን ግን ይፋ እንዳላደረጉለት ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይም በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው ምላሽ እንዳልሰጡ አስታውቋል። ኢትዮጵያ በአፍሪቃ የሰላም አስከባሪ ኃይል ስር 10 ሺህ የሚጠጋ ወታደር ሶማሊያ ውስጥ እንዳላት ያስታወሰው የሮይተርስ ዘገባ፤ በሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ ምክንያት፤ ሶማሊያ ወታደሮቹን አስወጣለሁ ስትል መቆየቷን ጠቅሷል። ሶማሊያ ባለችው ጸንታ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሚወጡ ከሆነ በአካባቢው የጽንፈኛው የአሸባብ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ሊጠናከር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም አመልክቷል። የአፍሪቃ ሕብረት ትናንት የሶማሊያ አዲስ ስምሪቱን መጀመሩን ይፋ አድርጓል። የትኞቹ ሃገራት ወታደሮችን ያዋጣሉ ስለሚለው ግን እስካሁን የወጣ መረጃ የለም።
ቱኒዝ፤ 27 ስደተኞች በቱኒዝያ የባሕር ዳርቻ መሞታቸው
ማዕከላዊ ቱኒዚያ አቅራቢያ ስደተኞችን የጫኑ ሁለት ጀልባዎች በደረሰባቸው አደጋ 27ቱ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ዛሬ አስታወቁ። 83ቱን ማትረፍ ተችሏል። ኬርክናህ ከምትባለው የቱኒዚያ ደሴት ግዛት አቅራቢያ የሞቱት አብዛኞቹ ወደ አውሮጳ ለመሻገር ከሰሀራ በስተደቡብ ሃገራት የመጡ ተሰዳጆች መሆናቸው ነው የተገለጸው። አሁንም ያልተገኙ እንዳሉ በሚል ፍለጋው መቀጠሉን የወደብ አካባቢን የሚጠብቀው የቱኒዚያ ብሔራዊ ዘብ አስታውቋል። በጣሊያን በኩል ወደ አውሮጳ ለመግባት ለሚያልሙ ተሰዳጆች ቱኒዚያ ዋነኛ ከሚባሉ የስደተኞች መሸጋገሪያ ሃገራት አንዷ ናት። በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩት ሜዲትራኒያን ባሕርን በአደገኛ ሁኔታ እያቋረጡ ወደ አውሮጳ ሃገራት ለመሻገር ይሞክራሉ። ሆኖም ጀልባዎች በሚያጋጥማቸው እክል ብዙዎች የባሕር እንስሳት ቀለብ እየሆኑ ነው። ከሁለት ሳምንታት በፊት እንኳን በተከታታይ ቀናት ከ45 በላይ ተሰዳጆች በተመሳሳይ ችግር ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ሞንቴኔግሮ፤ ሞንቴኔግሮ ውስጥ አንድ ታጣቂ 12 ሰዎችን ገደለ
ሞንቴኔግሮ ውስጥ አንድ ግለሰብ 12 ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን ታወጀ። ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ተጎድተዋል። በአንዲት መንደር ምግብ ቤት ውስጥ ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 12 ሰዎችን የገደለው የ45 ዓመቱ ታጣቂ በፖሊስ ሲከበብ እራሱን መግለደሉን ፖሊስ ዛሬ አስታውቋል። ወደ ሀኪም ቤት የተወሰዱት አራቱ ተጎጂዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሀኪሞች ተናግረዋል።
ፖሊስ እንደሚለው ግለሰቡ ትናንት ቀኑን ሙሉ አልክሆል መጠጥ ሲጠጣ መዋሉን መረጃ ደርሶታል። በነበረበት ምግብ ቤት ውስጥ ከሌላ ተስተናጋጅ ጋር መጋጨቱን ተከትሎ ወደ ቤቱ በመሄድ መሣሪያ ይዞ መጥቶ አራት ሰዎችን በዚያ ገድሎ ወደሌላ አካባቢ መሄድ ሌሎችንም መግደሉንም ዘርዝሯል።
ድርጊቱ የተፈጸመበት አካባቢና የዋና ከተማዋ ሴቴንጂ ጎዳናዎች ዛሬ ጭር ብለው የዋሉ ሲሆን ፖሊስ አካባቢውን እየቃኘ መሆኑ ነው የተገለጸው። አሰቃቂው ሀዘን የሁሉንም ስሜት መጉዳት ያመለከቱት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በግለሰቦች ጠብ ምክንያት የተፈጠረው ክስተት የሀገሪቱን የጦር መሣሪያ ይዞታ ደንብ እንዲጠብቅ መነሻ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ሶዑል፤ በደቡብ ኮርያ ፕሬዝደንቱን የደገፈውና የሚቃወሙት ሰልፍ
ደቡብ ኮርያ የሀገሪቱን ፕሬዝደንት የሚደግፉና የሚቃወሙ ዜጎችን ሰልፍ ስታስተናግድ ዋለች። እጅግ ኃይለኛውን ቅዝቃዜ ተቋቁመው ፕሬዝደንት ዮን ሱክ የኦል ሀገሪቱን ለማረጋጋት ከሥልጣን መነሳት የለባቸውም ያሉ ደጋፊዎቻቸው፤ ወደ የእርስ በእርስ ጦርነት ልትገባነው ያሏትን ሀገራቸውን እንዲያተርፉ ባሉበት እንዲቆዩ ጠይቀዋል። ፕሬዝደንቱን ከሚደግፉት አንዱ የ76 ዓመት አዛውንት በሥልጣን ይቆዩ ያሉበትን እንዲህ ያስረዳሉ።
«እዚህ ሀገር እያንዳንዱ የሕግ አፈጻጸም ሕገወጥ ነበር። የደቡብ ኮርያ ሕዝብ ይህን የሕግ ሥርዓት ማን እንዳመጣው እና እንዴት ተግባራዊ እንደሆነ አያውቅም። ሀገሪቱ በእርስ በእርስ ጦርነት እና በብጥብጥ ላይ ናት። ሀገሪቱን ለማረጋጋት ፕሬዝደንት ዮን ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው።»
በተቃራኒው እነሱ ከተሰለፉበት ብዙም ሳይርቁ ተሰባስበው አደባባይ የወጡት ተቃዋሚዎቻቸው፤ ፕሬዝደንታዊ ሥልጣናቸውን ማገድ ብቻ አይበቃም፤ ባስቸኳይ ከሥልጣናቸው ተነስተው ይታሰሩ እያሉ ነው። ፕሬዝደንቱን ተቃውመው ከወጡት መካከል በወንጀል መቀጣት ይኖርባቸዋል የሚሉም አሉ። የ27 ዓመቷ የፕሬዝደንቱ ተቃዋሚ ከእነሱ አንዷ ናት።
«የፕሬዝደንትነት ሥልጣናቸውን ማገዱ ብቻ በቂ አይደለም፤ ምንም ነገር ማድረግ እንዳይችሉ በወንጀል መቀጣት ይኖርባቸዋል። በፍጥነት ወደ አዲስ ማኅበረሰብ መሻገር እንድንችል ሕገ-መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ባስቸኳይ ሊከሳቸው ይገባል።»
የፕሬዝደንቱ ሥልጣን ከሁለት ሳምንታት በፊት በብሔራዊ ምክር ቤቱ ድምጽ ታግዷል። ቀጣይ እጣ ፈንታቸው በሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት የሚወሰን ይሆናል። የፕሬዝደንት ዮን ዘመነ ሥልጣን እንዲያከትም ቢያንስ ከፍርድ ቤቱ ዘጠኝ ዳኞች ስድስቱ መወሰን ይኖርባቸዋል።
ዋሽንግተን፤ ኒው ኦርሊየንስ፤ ኒውዮርክና ላስ ቬጋስ በአዲስ ዓመት ጥቃቶች
ኒውዮርክ ከተማ በጎርጎሪዮሳዊው በአዲስ ዓመት ምሽት 10 ሰዎች በተተኮሰ ጥይት መጎዳታቸው ተነገረ። ጥቃቱን የፈጸሙት ሦስት ወይም አራት የሚሆኑ ግለሰቦች ሲሆኑ ከመጠጥ ቤት ውጭ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን የኒው ዮርክ ፖሊስ ዛሬ ማለዳ ገልጿል። ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ስድስቱ ሴቶች ናቸው። ፖሊስ ድርጊቱ የሽብር ጥቃት አይደለም ነው ያለው። ኒውዮርክ ላይ ተኩስ የተከፈተው የኒው ኦርሊየንሱ ጥቃት በደረሰ በሰዓታት ልዩነት እንደሆነ ነው የተገለጸው። ትናንት በኒው ኦርሊየንስ 15 ሰዎችን በተሽከርካሪ የገደለው እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለውን ቡድን አርማ ያውለበልብ የነበረ ግለሰብ ለዚህ ድርጊት ያነሳሳውን ምክንያት እየመረመረ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል። በዚህ ጥቃት ሌሎች 30 ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል። በላስ ቬጋስም እንዲሁ ከትራምፕ ሆቴል ደጃፍ የጋየው ተሽከርካሪ ለአንድ ሰው ሞት እና ለሌሎች ሰባት ሰዎች ጉዳት ምክንያት ሆኗል። ባለሥልጣናት ጎርጎሪሳዊው አዲስ ዓመት በተከበረበት በትናንትናው ዕለት በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ከተሞች የተከሰቱት ጥቃቶች ከሽብር ጋር ትስስር እንዳላቸው እየመረመሩ መሆናቸው ተገልጿል።
ሞስኮ፤ ሩሲያ የዩክሬን የኃይል ተቋማት ላይ ጥቃት ማድረሷ
ሩሲያ ለዩክሬን ወራደራዊ ኢንደስትሪ ድጋፍ የሚሰጡ የኃይል ተቋማቶቿ ላይ ጥቃት ማድረሷን ዛሬ አስታወቀች። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ባለፉት 24 ሰዓታት የአየር ኃይል፤ ሰው አልባ አውሮፕላኖች፤ ሚሳኤል እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ተጠቅሞ የዬክሬንን የኃይል ተቋማት፤ ወታደራዊ አውሮፕላን መንደርደሪያዎችና በተለያየ ስፍራ የሚገኙ የዩክሬን ወታደራዊ ኃይሎች ላይ ጥቃት አድርሷል። ከዚህም ሌላ አንድ የዩክሬን ሱ 27 ተዋጊ ጀትና 97 ድሮኖችም መትቶ መጣሉን፤ ከአሜሪካ የተሰጣትን ስድስት ሚሳኤሎችንም ማክሸፉን አስታውቋል። እንዲያም ሆኖ ሮይተርስ የዜና አውታር የተባለው ጥቃት ስለመፈጸሙ በገለልተኝነት ለማጣራት እንዳልቻለ ነው ያመለከተው። ሩሲያ፤ ዩክሬን ወደ ግዛቷ ገብታ ጥቃት ለማድረስ የምዕራባውያንን ሚሳኤል እንደምትጠቀም በመግለጽ ለዚህ ደግሞ የአፀፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ካስጠነቀቀች ወዲህ በተደጋጋሚ እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን ማድረሷን እየገለጸች ነው።
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ