1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሳስ 25 ቀን 2017 የዓለም ዜና

ነጋሽ መሐመድዓርብ፣ ታኅሣሥ 25 2017

-ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሠላም ለማስከበር አዲስ ተልዕኮ ከተቀበለዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ጋር እንደምትተባበር አስታወቀች።የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር የኢትዮጵያን ዕቅድ ይፋ ያደረገዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስትር ከሶማሊያ ፕሬዝድንትና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ትናንት ከተነጋገሩ በኋላ።----ኢትዮጵያ ዉስጥ የአፋር ክልልን በተከታታይ የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ እሳተ ጎሞራ ሳያፈነዳ እንዳልቀረ ተነገረ።-----ጀርመንና ፈረንሳይ ለአዲሶቹ የሶሪያ ባለሥልጣናት ድጋፍ እንደሚሰጡ የሁለቱ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች አስታወቁ።ሁለቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ደማስቆ ዉስጥ ከአዳዲሶቹ የሶሪያ መሪዎች ጋር ተነጋግረዋል።ዜናዉ በዝርዝር።

https://p.dw.com/p/4ono4

ሶል-የቀድሞዉን ፕሬዝደንት ለማሰር የተደረገዉ ሙከራ ከሸፈ

ያለመከሰስ መብታቸዉ በቅርቡ የተገፈፈዉን የደቡብ ኮሪያ የቀድሞ ፕሬዝደንት ዩን ሱክ የኦልን ለማሰር የሐገሪቱ የወንጀል መርማሪዎችና ፖሊሶች ያደረጉት ሙከራ ከሸፈ።የደቡብ ኮሪያ የሙስና መርማሪ ቢሮ እንዳስታወቀዉ በወንጀል የሚጠረጠሩትን የቀድሞዉን ፕሬዝደንት እንዲይዙ  መርማሪዎችንና ፖሊሶችን ሶል ወደሚገኘዉ ፕሬዝደንታዊዉ መኖሪያ ቤት አዝምቶ ነበር።በአካባቢዉ የነበረ አንድ ጋዜጠኛ እንደዘገበዉ 140 የሚሆኑት መርማሪዎቹና ፖሊሶች ወደ ፕሬዝዳንታዊዉ መኖሪያ ተጠግተዉም ነበር።

«120 ፖሊሶች፣ 20 የፀረ ሙስና መርማሪዎችና ባለሥልጣናት ወደ ፕሬዝደንታዊዉ መኖሪያ ቅጥር ግቢ ተጠግተዉ ነበር።ቅጥር ግቢዉ ከመድረሳቸዉ በፊት  የተወሰኑ የጦር ሠራዊት ባልደረቦችና ሰልፈኞች ሊያስቆሟቸዉ ሞክረዉ ነበር።ሁለቱን ክልከላ አልፈዉ ቅጥር ግቢዉ ከደረሱ በኋላ የፕሬዝደንታዊዉ ዘብ ባልደረቦች ወደ ዉስጥ እንዳይገቡ አግደዋቸዋል።« 
መርማሪዎቹና ፖሊሶቹ የፕሬዝደንታዊዉ ልዩ ጠባቂዎች ጋር  ለስድት ሰዓታት ያክል ከተፋጠጡ በኋላ ባዶ እጃቸዉን ለመመለስ ተገድደዋል።ዩን አላግባብ አስኳይ ወታደራዊ አዋጅ ደንግገዋል በሚል ባለፈዉ ታሕሳስ 4 ከሥልጣን ከተወገዱ ወዲሕ የደቡብ ኮሪያ ፖለተከኞችና ሕዝቡ ለሁለት ተከፍለዉ እየተወጋገዙ ነዉ።
 

ዴይር አል-በላሕ-የእስራኤል ጦር በ24 ሰዓት፣ 56 ፍልስጤሞችን ገደለ
የእስራኤል ከትናንት ሌሊት እስከ ዛሬ ማርፈጃዉ ድረስ በተለያዩ የጋዛ ቀበሌዎች ባደረሰዉ ድብደባ በትንሹ ሠላሳ ፍልስጤማዉያንን ገደለ።በርካታ አቆሰለ።የሆስፒታል ምንጮች እንዳስታወቁት የእስራኤል ጦር ጋዛ ዉስጥ ባለፉት 24 ሰዓታት የገደላቸዉ ፍልስጤማዉያን ቁጥር 56 ደርሷል።የአል አቅሳ ስዉዓን መታሰቢያ ሆስፒታል ባልደረቦች ከሟቾቹ አብዛኞቹ ሕፃናትና ሴቶች ናቸዉ።ትናንት ከተገደሉት ቢያንስ አንዱ ጋዜጠኛ ነዉ።የእስራኤል ጦር በጋዛ ሠርጥ የተለያዩ ቀበሌዎች ሰሞኑን የከፈተዉ ጠንካራ ድብደባ የጋዛን እልቂት ለማስቆምና የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ያገቷቸዉን እስራኤላዉንን ለማስለቀቅ ደንበር-ገተር የሚለዉን ድርድር እያደናቀፈዉ ነዉ።በተያያዘ ዜና ዛሬ ሲነጋጋ ከየመን የተተኮሰ ሚሳዬልና የማስጠንቀቂያ ደወል የእየሩሳሌምና የማዕከላዊ እስራኤል ነዋሪዎች ሲያተራምስ አንግቷል።የእስራኤል ጦር ኃይል ሚሳዬል መተኮሱን ከማስታወቅ ባለፍ ሚሳዬሉ ያደረሰዉ ጉዳት ሥለመኖር አለመኖሩ ያለዉ ነገር የለም።
 

ደማስቆ-የጀርመንና የፈረንሳይ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በሶሪያ
ጀርመንና ፈረንሳይ አዲስ ለሚመሰረተዉ የሶሪያ መንግስት ድጋፋቸዉን እንደሚሰጡ የሁለቱ ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ቃል ገቡ።የጀርመኗ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክና የፈረንሳዩ አቻቸዉ ዤን-ኖኤል ባሮ ከአዲሶቹ የሶሪያ መሪዎችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ዉይይት የሶሪያና የአዉሮጳ ግንኙነት አዲስ ይዘትና መልክ እንደሚኖረዉ ቃል ገብተዋል።ሁለቱ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የሶሪያን ጊዚያዊ መሪ አሕመድ አል ሻራና ሌሎች ባለሥልጣናትን ከማነጋገራቸዉ በፊት ደማስቆ አጠገብ የሚገኙ እስር ቤቶችንና ሌሎች ተቋማትን ጎብኝተዋል፣ ሚንስትሮቹ በበሽር አል አሰድ ዘመን አሰቃቂ ግፍ ተፈፅሞባቸዋል የሚባሉ እስር ቤቶችን ሲጎበኙ የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ባለ ነጭ ቆብ የሚባሉት የሶሪያ የሲቢል አደጋ መከላከያ ሠራተኞች አመስግነዋል።
«አንዳድ አካባቢ የተፈፀመዉን ዘግናኝ ግፍ መግለፅ ይከብዳል።እዚሕ ርዕሰ ከተማ ደማስቆ አጠገብ ሰዎች ከገሐነብ ጋር ተጋፍጠዋል፤ በሰለጠነዉ ዘመን ይደርሳል ተብሎ በማይታሰብ መንገድ ተገድለዋል።ይሁንና ዛሬ ከፈረንሳዩ ባልደረባዬ ጋር እዚሕ የተገኘሁት በሁለታችን ሐገራት ብቻ ሳይሆን ባዉሮጳ ሕብረት ስም ጭምር ነጭ ቆብ ለባሾች ለበርካታ ዓመታት ላደረጉት ግልፅ አስተዋፅኦ ላመሰግን ነዉ።»
የበሽር አል አሰድ መንግሥት ከተወገደ ወዲሕ ምዕራባዉያን መንግሥታት ለሶሪያ ድጋፍ እንደሚሰጡ ቃል እየገቡ ነዉ።እስካሁን ድረስ ግን በሶሪያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ አላነሱም።የአሰድን መንግሥት በግንባር ቀደምትነት ባስወገደዉ  በሐያት ታሕሪር አሕ-ሻም (HTS) ቡድን ላይ የወሰኑትን የአሸባሪነት ፍረጃም እስካሁን አላነሱም።
 

አክራ-ጋና ለአፍሪቃዉያን የቪዛ ቁጥጥር አነሳች
ጋና የአፍሪቃ ሐገራት ፓስፖርት የያዙ መንገደኞች ያለ መግቢያ ፍቃድ (ቪዛ) ወደ ሐገሯ እንዲገቡ ፈቀደች።ተሰናባቹ የጋና ፕሬዝደንት ናና አኩፉ-አብዶ ዛሬ ለሕባቸዉ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት አዲሱ ደንብ ከያዝነዉ ወር ጀምሮ ይፀናል።አኩፉ-አብዶ አክለዉ ደንቡ የአፍሪቃን የነፃ የንግድ ትስስርን ገቢር ለማድረግ የመጀመሪያዉ ርምጃ ነዉ።የንግድ ትስስሩን ለማስረፅ ከዚሕ ቀደም ርዋንዳ፣ ሲሼልስ፣ጋምቢያና ቤኒን አፍሪቃዉያን ያለቪዛ ወደየሐገራቸዉ እንዲገቡ ፈቅደዋል።
 

 

ፍቼ-ሶስት ባለሥልጣናትና ሁለት ረዳቶቻቸዉ ተገደሉ
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉሌሌ ወረዳ ሶስት የዞን ባለስልጣናትን ጨምሮ አምስት ሰዎች ዛሬ ጠዋት መገደላቸውን የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ባለሥልጣናቱ የተገደሉት ያያ ጉሌሌ ወረዳ ፊታል ከተማ ውስጥ ሁለት ቀናት  ቆይተው ዛሬ ጠዋት 3 ሰዓት ተኩል ግድም ወደ ዞን ከተማ ፊቼ በመመለስ ላይ ሳሉ ባደፈጡ ታጣቂዎች ድንገተኛ ተኩስ ተከፍቶባቸው ነው፡፡ 
ከተገደሉት የዞን ባለስልታናት የሰሜን ሸዋ ዞን የገቢዎች ኃላፊ፣ የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የዞኑን ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊዎች ይገኙበታል፡፡ከሶስቱ አመራሮች በተጨማሪ አሽከርካሪያቸው እና አንድ የአከባቢው ቀበሌ አመራርም ሲገደሉ ሁለት የቀበሌ ባለስልጣናት ክፉኛ ቆስለው በህይወት ተርፈዋል፡፡አንድ የአካባቢዉ ነዋሪ እንዳሉት ከሟች ቁስለኞቹ በተጨማሪ የታገቱ ሰዎችም አሉ።
የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ስዩም ጌቱ እንደዘገበዉ የያያ ጉሌሌ ወረዳ ዋና ከተማ ፊታል ከፊቼ 28 ኪ.ሜ.  ርቀት ላይ ነው ትገኛለች፡ በወረዳ የሸመቁ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ሰዎችን ይገድላሉ።ያግታሉም።ከሁለት ሳምንታት በፊትም በቀለ ሰርቤሳ የተባሉ ባለስልጣን በታጣቂዎች ተገድለዋል።
 

አዲስ አበባ-ከእሳተ ጎሞራዉ አካባቢ ሰዎች እየተነሱ ነዉ-መንግስት
ዘግይቶ በደረሰን  ዘገባ የአፋር ክልል መስተዳድር የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምልክት ከተያባቸዉ አካባቢዎች ነዋሪዎችን እያሸሸ ነዉ።ሮይተርስ ዜና አገልግሎት ለኢትዮጵያ መንግሥት ቅርበት ያለዉን ፋና ብሮድካስትን ጠቅሶ እንደዘገበዉ ከአዲስ አበባ 165 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኙ አካባቢዎች ነዋሪዎች ተነስተዋል።የተነሱትን ሰዎች ብዛት፣የሰፈሩበትን አካባቢም ሆነ የተደረገላቸዉን ርዳታ ግን ዘገባዉ አልጠቀሰም።በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የጆኦሎጂካል ኢንስቲትዊት እሳተ ጎመራ መፈንዳቱን የሚጠቁሙ የአዋራና የጢስ ምስል የያዘ ቪዲዮ በፌስ ቡክ ገፅ ለጥፏል።የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ዝግጁነት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሺፈራዉ ተክለ ማርያም ግን በመሬት መንቀጥቀጥ በሚመቱ አካባቢዎች ያለዉን እንቅስቃሴ «የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ» ለማለት ጊዜዉ ገናነዉ ማለታቸዉን ሮይተርስ ጠቅሷል።ኮሚሽነሩ ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖችን ለማሸሽ «እየተዘጋጀን ነዉ» ብለዋልም።እስካሁን ያልተዘጋጁበትን ምክንያትም ሆነ፣ ከእንግዲሕ ዝግጅቱ የሚፈጀዉን ጊዜ ግን ኮሚሽነር ሺፈራዉ አልተናገሩም።
 

 

አዲስ አበባ-ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ እሳተ ጎሞራ ፈነዳ
ኢትዮጵያ ዉስጥ በአፋር ክልል የሚገኙ ሁለት ወረዳዎችን ሲያርገፈግፍ የነበረዉ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ዛሬ እሳተ ጎሞራ መሰል ትፍ አፈንድቷል።የዓይን ምሥክሮችና ነዋሪዎች እንዳሉት ዱለቻ ወረዳ ሰጋንቶ ቀበሌ ከሚገኘዉ ዶፈን ኮረብታና ከአካባቢዉ ከትናንት ማምሻ ጀምሮ ሲጤስ ሲዥሞለሞል ነበር።ዛሬ ማለዳዉ ላይ ደግሞ ከባድ ፍንዳታ ተሰምቶ የእሳተ ጎሞራ ትፍ የሚመስል ነገር ከምድር እየፈለቀ ነዉ።የመሬት መንቀጥቀጡ ከዚሕ ቀደም ዶለቻ ወረዳ ላይ ፍል ዉኃ፣ ፈንታሌ ተራራ ላይ ደግሞ ጢስ ማስከተሉ ተዘግቦ ነበር።አንዳድ ነዋሪዎች እንደሚሉት ዛሬ ከማለዳዉ ጀምሮ የመሬቱን ንጣፍ እየሸነቆረ የሚወጣዉ የድንጋይ ቅላጭ የሚመስለዉ  ትፍ በትንሽ ግምት አስር አካባቢዎች ታይቷል።በአፋር ክልል አዋሽ 7 ኪሎ፣ ሳቡሬ፣ ዶፈን ቦለሐሟ፣ ከሰም፣ ዱለቻና ሌሎች ከተሞችንና ቀበሌዎችን ለወራት የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በርካታ ቤቶችን አፍርሷል፤ በሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ አፈናቅሏል፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለድንጋጤ፣ሥጋትና በሽታ አጋልጧል።በነዋሪዎቹ አስተያየት መሠረት የፌደራሉ፣የክልል መንግሥታትም ሆኑ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ወይም ባለሙያዎች እስካሁን ድረስ የወሰዱት የጥንቃቄ ርምጃ ግን የለም።
 

አዲስ አበባ-የኢትዮጵያና ሶማሊያ ትብብር በAUSSOM 
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሠላም ለማስከበር አዲስ ከተመሰረተዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት  ጋር ተባብራ እንደምትሰራ አስታወቀች።የአፍሪቃ ሕብረት የድጋፍና የማረጋጋት ተልዕኮ በሶማሊያ ( AUSSOM) የተሰኘዉ አዲስ የሠላም አስከባሪ ሠራዊት ተልዕኮ ባለፈዉ ሮብ ሥራ ጀምሯል።ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ወደብ የመኮናተር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረሟ ምክንያት የኢትዮጵያ ሠራዊት የአዲሱ ተልዕኮ አካል እደማይሆን የሶማሊያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ሲያስታዉቁ ነበር።የኢትዮጵያና የሶማሊያ ባለሥልጣናት በቱርክ ሸምጋይነት ከተቀራረቡ ወዲሕ ግን የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ የሻከረ ግንኙነት እየተሻሻለ ነዉ።ትናንት ሞቃዲሾን የጎበኘዉ በኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስትር አይሻ መሐመድ የተመራዉ የኢትዮጵያ የመልዕክተኞች ጓድ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድን ጨምሮ ከተለያዩ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረዋል።የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ የሁለቱ ወገኖች ባለሥልጣናት ባደረጉት ዉይይት አሸባሪነትን ለመዋጋትና የAUSSOMን ተልዕኮ ለማሳካት ሁለቱ መንግሥታት በጋራ እንደሚጥሩ አስታዉቀዋል።የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንደዘገበዉ የሶማሊያዉ መከላከያ ሚንስትር አብዱልቃድር ኑር ጃማ ኢትዮጵያዊ አቻቸዉን ሲያነጋግሩ የሶማሊያን ሠላም ለማስከበር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለከፈለዉ መስዋዕትነትና ላበረከተዉ አስተዋፅኦ አመስግነዋል።

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።