1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሳስ 29 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2017

https://p.dw.com/p/4ov7S

በትግራይ ክልል ጦርነቱ ከቆመ ከሁለት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም  በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጦርነቱ ተፈናቃዮች  መንግስት ረስቶናል ሲሉ ከሰሱ። 

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮችን ለመመለስ በዕቅድ  እየሰራሁ ነው ብሏል።

በመጠለያ ጣቢያዎች ዓመታት ያሳለፉት ተፈናቃዮች በበሽታና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች እየደረሰብን ነው የሚመለከተው አካል ወደ ቄዬአችን ይመለስን ሲሉ ጠይቀዋል። በተለይም ከምዕራብ ትግራይ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር ከሚዋሰኑ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በክልሉ የተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ግዚያዊ መጠልያዎች አስቸጋሪ ኑሮ እየገፉ መሆናቸውን የጠቀሱት ተፈናቃይ ብርሃነ ታፈረ የተፈናቃዮች ጉዳይ መዘንጋቱን ይናገራሉ።

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮች ለመመለስ ጥረት ላይ መሆኑ የሚገልፅ ሲሆን፥ ለዚህ ማስፈፀሚያ ዝርዝር እቅድ መውጣቱ፥ ሂደቱ ለማስፈፀም ደግሞ 2 ነጥብ 1 ቢልዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከደረሱ ሁለት ዓመት ከሁለት ወር ቢያስቆጥርም  አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ሊሆን አልቻለም ።

የኢትዮጵያ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዛሬ ታህሳስ 29/2017 ዓ.ም አመሻሽ ጀምሮ በሥራ ላይ የሚውል የነዳጅ ምርቶች ችርቻሮ መሸጫ የተሻሻለ ዋጋ ይፋ አደረገ። ሚኒስቴሩ ማምሻውን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ አንድ ሊትር ቤንዚን በብር 101.47 ሆናል። በሚኒስቴሩ መግለጫ መሰረት በናፍታ እና በኬሮሲን ላይ የዋጋ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል። በዚህ መሰረት ናፍጣ በብር 98.98፣ ኬሮሲን በብር 98.98 ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዛሬ ታህሳስ 29/2017 ዓ.ም አመሻሽ ጀምሮ በሥራ ላይ የሚውል የነዳጅ ምርቶች ችርቻሮ መሸጫ የዋጋ ጭማሪ ይፋ አደረገ።

ሚኒስቴሩ ማምሻውን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ አንድ ሊትር ቤንዚን በብር 101.47 ሆናል። በሚኒስቴሩ መግለጫ መሰረት በናፍታ እና በኬሮሲን ላይ የዋጋ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል። በዚህ መሰረት ናፍጣ በብር 98.98፣ ኬሮሲን በብር 98.98 ሆነዋል።መስሪያ ቤቱ የነዳጅ ምርቶችን ችርቻሮ ዋጋ መሸጫ ዋጋ ይፋ የሆነው በየወሩ እየተከለሰ በስራ ላይ እንዲውል በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ውሳኔ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት መሆኑንም ጠቅሷል።

 

ሃያ ወራትን ባስቆጠረው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ከሰላሳ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምግብ ርዳታ ጠባቂዎች መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አመለከተ።

ከከርዳት ጠባቂዎች ከግማሽ በላይ ቁጥር ህጻናት ናቸው ያለው ድርጅቱ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ ርዳታ ለማድረስ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ  ኦቻ ከሰላሳ ሚሊዮን ለሚልቁ ሱዳናዉያን ርዳታ ለማድረስ የ4.2 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ዘመቻ መክፈቱን ዛሬ ኒውዮርክ ውስጥ ይፋ አድርጓል።

በመንግስታቱ ድርጅት የኦቻ ተወካይ ኤዴም ዎሶርኑ እንዳሉት "በሱዳን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተከሰተው የርዳታ  የፍላጎት መጠን በተመሳሳይ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማሰባሰብን ይጠይቃል።"

 በጎርጎሪዎሱ  ሚያዝያ 2023 በሱዳን ብሄራዊ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሱዳን ለአስከፊ ሰብአዊ ቀውስ ተጋልጣለች።

በጦርነቱ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤  ከስምንት ሚሊዮን በላይ ደግሞ ተፈናቅለዋል።  ይህም ከጦርነቱ በፊት ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃይ የነበራት ሀገር ጦርነቱ ሲጨመርባት  በዓለም ላይ ከፍተኛው የአገር ውስጥ መፈናቀል ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።

 

ተመራጩ የጋና ፕሬዚዳንት ጆህን ማህማ ዛሬ በመዲናዋ አክራ ቃለ መሃላ ፈጸሙ ።

በፕሬዚዳንታዊው የቃለ ማሃላ ስነስረዓት የሃያ ሃገራት መሪዎች ተገኝተዋል።  ማህማ ለሁለት የምርጫ ዘመናት ካገለገሉት ከተሰናባቹ ፕሬዚደንት ናና አኩፎ አዶ እጅ ስልጣኑን ዛሬ በይፋ በይፋ ተረክበዋል።

የ66 አመቱ አዲሱ ፕሬዝዳንት የምዕራብ አፍሪካዊቷን ሀገር ብሄራዊ ልብስ ለብሰው  ለተሰበሰበው ህዝብ በደስታ ባደረጉት ንግግር  "ዛሬ አገራችንን ወደ ነበረችበት ለመመለስ እድሉን ያገኘችበት ነው" ብለዋል።

ከጎርጎርሳዉያኑ 2012 እስከ 2017 መጀመሪያ ድረስ ጋናን የመሩት ማሃማ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ቢወዳደሩም ሳያሳካላቸው ቆይቶ ነው በሶስተኛው ድሉ ያዘነበላለቸው።  

የ33 ሚሊዮን ህዝብ ያላት እና ከአፍሪካ ወርቅ በመላክ ቀዳሚ እንዲሁም በአለም ሁለተኛዋ ካካዋ አምራች ሀገር ፕሬዚደንት ሆነው ቃለ መሃላ የፈጸሙት ማህማ ብርቱ ፈተና የገጠመውን የሀገሪቱን ኤኮኖሚ የመከላከል ኃላፊነት ተሸክመዋል።

 

ኢንዶኔዢያ በይፋ ብሪክስን ተቀላቀለች።

ደቡብ ኢስያዊቷ ሀገር በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት የኤኮኖሚ ጥምረት የሆነውን በእንግሊዘኛ ምህጻሩ ብሪክስን መቀላቀሏን ከመስራቾች አንዷ ብራዚል ዛሬ ይፋ አድርጋለች።

የወቅቱ የብሪክስ ፕሬዚዳንት ብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳለው ኢንዶኔዥያ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ነበር ለኤኮኖሚ ጥምረቱ ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘው።  በዓለም አራተኛው የህዝብ ብዛት ባለቤት ሀገር ኢንዶኔዢያ ጥምረቱን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረበችው በሀገሪቱ መንግስታዊ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ እንደነበር የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል።

ኢንዶኔዢያ የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏን ተከትሎ የአባል ሀገራቱ ቁጥር አስር ደርሷል። በጎርጎሪዎሱ 2009 ብራዚል ፣ ሩስያ ፣ ህንድ እና ቻይና ያቋቋሙት የኤኮኖሚ ጥምረቱ ከአንድ ዓመት በኋላ አፍሪካዊቷን ሀገር ደቡብ አፍሪካን አካቷል።

የመስራች ሀገራት የመጀመሪያ ፊደላት ጥምር መጠሪያን የያዘው ብሪክስ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን ጨምሮ ኢራን ፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን በአባልነት ተቀብሏል። ሳኡዲ አረቢያ ጥምረቱን እንድትቀላቀል ግብዣ ቢቀርብላትም እስካሁን መልስ አልሰጠችም።

ቱርክ ፣ አዛርባጃን እና ማሌዢያም በተመሳሳይ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያኤ አቅርበው መልስ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ያመለከተው ዘገባው ሌሎች ሃገራትም በተመሳሳይ ፍላጎታቸውን እያንጸባረቁ ነው ብሏል።

 

ሩስያ ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚዎች እየደገፈች ነው ስትል አሜሪካ በመንግስታቱ ድርጅት ከሰሰች።

አሜሪካ ትንናት ሰኞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባሰማችው ክስ ሩስያ ፖለቲካዊ ዓላማውን ለማሳካት ስትል ሁለቱን ወገኖች በደገፍ ጦርነቱ መቋጫ እንዳይኖረው አድርጋለች ፤ ስትል ወንጅላለች።

"ሩሲያ ለሁለቱም ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ  እንቅፋት መሆንን መርጣለች» ሲሉ በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ትናንት ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል። ሩስያ በሱዳን የወርቅ ማዕድን ማውጣት እና ማዘዋወር ተሳትፎ እንዳላት መረጃ እንዳላቸው የገለጹት በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ቃል አቃባይ ሩስያ ይህንኑ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትል የተከተለችው መንገድ ሱዳናዉያን በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንዲቆዩ አድርጋለች በማለት ክሳቸውን አጠናክረዋል።

ለአሜሪካ ክስ መልስ የሰጡት በተመድ የሩስያ  ምክትል  አምባሳደር ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ በበኩላቸው “አሜሪካ በራሷ መለኪያ ሌሎች  ኃያላን መንግሥታት ላይ ለመፍረድ በመሞከሯ እናዝናለን።»  ብለዋል።

ባለፈው የህዳር ወር ሩሲያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ተፋላሚ ወገኖች በአስቸኳይ ጦርነቱን አቁመው በአስቸኳይ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦትን እንዲያረጋግጡ የሚጠይቀውን ረቂቅ ውሳኔ ድምጽን ድምጽ በመሻር መብቷ ውድቅ አድርጋለች።  ነገር ግን የተቀሩት አስራ አራቱ የምክር ቤት አባላት ረቂቁን ደግፈው ድምጻቸውን ሰጥተው እንደነበር ሮይተርስ በዘገባው አስታውሷል።

 

አሜሪካ አፍጋኒስታን ውስጥ ታስረው የሚገኙ ዜጎቿን ለማስለቀቅ ከጣሊባን ጋር ንግግር እያደረገች ነው ተባለ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ዎል ስትሬት ጋዜጣን ጠቅሶ እንደዘገበው የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር አፍጋኒስታን ውስጥ ታስረው የሚገኙ ሶስት አሜሪካዉያንን ቢያንስ በአንድ ስመ ጥር የጓንታናሞ ቤ እስረኛ የመቀየር ፍላጎት አሳይቷል። የዜና ወኪሉ ዘገባውን በተመለከተ ከኋይት ሃውስም ሆነ የጣሊባን ባለስልጣናት ወዲያው መልስ ማግኘት አለመቻሉን አመልክቷል።

በጎርጎርሳዉያን 2022 አፍጋኒስታን ውስጥ ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙት ሶስቱ አሜሪካውያን ሪያን ኮርቤት ፣ ጆርጅ ግሌዝማን ፣ እና መሐሙድ ሐቢቢ ሲሆኑ በለውጣቸው ከጓንታናሞ ቤ ይለቀቃል የተባለው እስረኛ ማንነት በይፋ ባይገለጥም አፍጋኒስታናዊ የሆነ እና ከቀድሞው የአልቃኢዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ጋር ግንኙነት የነበረው ሰው ነው ተብሏል።

አሜሪካውያኑ አፍጋኒስታን ውስጥ የተያዙት አንዱ ጣሊባን ካቡልን በተቆጣጠረበት ወቅት አሜሪካ ጦሯን አዋክባ ባወጣችበት ወቅት ሲሆን ሌሎቹ ቆየት ብሎ ሀገር በመጎብኘት ላይ ሳሉ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።

የዋሽንግተን እና ካቡል ንግግሮች ካለፈው ዓመት ሐምሌ  ወር ጀምሮ በሂደት ላይ መሆኑን ያመለከተው ዘገባው ሂደቱ ይፋ ባይሆንም ለንግግሮች ከተሳተፉ አካላት ጋር ቅርበት ካላቸው የመረጃ ምንጮች ማረጋገጡን አስነብቧል።

ታምራት ዲንሳ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።