1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሳስ 30 ቀን 2027 የዓለም ዜና

ነጋሽ መሐመድረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2017

-በደቡብ ኢትዮጵያ ኮሬ ዞን፣ ጎርካ ወረዳ ታጣቂዎች ሁለት ገበሬዎችን በጥይት ደብደዉ፣ በገጀራ ተልትለዉ ገደሉ።የኮሬ ዞን ባለሥልጣናት ገዳዮቹን ከአጎራባች ወረዳ የገቡ «ፀረ-ሠላም» ኃይላት ብለዋቸዋል።በዞኑ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰዎችን ይገድላሉ።-----ዩናይትድ ስቴትስ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሕምዲቲ)ና ቤተሰቦቻቸዉ አሜሪካ እንዳይገቡ አገደች---የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጭ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፓናማ ቦይን፣የዴንማርክን ግሪንላንድንና ካናዳን በኃይል ጭምር ለመያዝ መዛታቸዉ የአዉሮጳና የአሜሪካ መንግሥታትን አስደግጧል።

https://p.dw.com/p/4oxUA

ሐዋሳ፣ ታጣቂዎች ሁለት ገበሬዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገደሉ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ሁለት አርሶአደሮች በጥይት ተደብድበውና አካላቸው ተቆራርጦ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ገለጹ፡፡ አርሶአደሮቹ የተገደሉት ጎርካ ወረዳ ከሬዳ እና ጀሎ በተባሉ ሁለት የተለያዩ ቀበሌያት ውስጥ ትናንት ነው ፡፡የሟች አርሶአደር አድማሱ አሰፋ የሥጋ ዘመድ መሆናቸውን የተናገሩት አንድ የአይን እማኝ ግድያውን ዘግናኝ ብለዉታል።
  የኮሬ ዞን  መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ የኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ አማረ አክሊሉ ለግድያዉ ከምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የተነሱ «ጸረ ሰላም» ያሏቸዉን ወገኖች ተጠያቂ አድርገዋል።
      
የሐዋሳዉ ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ የታጣቂዎቹ መነሻ ነው የተባለውን በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን ባለሥልጣናትን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ከ2010 ጀምሮ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለዋል።ከሃምሳ ሺህ በላይ ነዋሪዎች  ተፈናቅለዋል።

ዋሽግተን-ዩናይትድ ስቴትስ በሐሚቲ ላይ ማዕቀብ ጣለች

ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ)ና በቤተሰቦቻቸዉ ላይ ማዕቀብ ጣለች።የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴ እንዳለዉ ሐምዲቲ የሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት የዘር ማጥፋት ማድረሱን፣ ወንዶችን መገድሉንና ሴቶችን መድፈሩን የሚያረጋግጥ መረጃ ደርሶታል።ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ የሚያዙት ፈጥኖ ደራሽ ጦርና ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን የሚያዙት የሱዳን መከላከያ ጦር ዉጊያ ከገጠሙበት ከሐቻምና ሚዚያ ወዲሕ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግፍ መዋላቸዉን የተለያዩ ወገኖች በየጊዜዉ ይዘግባሉ።የዩናይትድ ስቴትስ ከተፋላሚ ወገኖች አንዱን በዘር ማጥፋት ወንጅላ በማዕቀብ ስትቀጣ ግን ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ይፋ ባደረገችዉ ዉሳኔ መሠረት ሐምዲቲና ቤተሰቦቻቸዉ አሜሪካ መግባት አይችሉም፤ ተጨማሪ እገዳም ሊጣልባቸዉ ይችላል።

 

ፖርት ሱዳን-550 ሴቶች ተደፍረዋል-የሱዳን መንግሥት
ይሕ በእንዲሕ እንዳለ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ባልደረቦች ከ550 በላይ ሴቶችና ልጃገረዶችን መድፈራቸዉን በሱዳን መከላከያ ሠራዊት የሚደገፈዉ የሐገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።በሴቶች ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት የሚከታተለዉ መስሪያ ቤት የበላይ ወይዘሮ ሱላይማ ኢሻቅ አል-ኸሊፋ እንዳሉት ከተደፈሩ ሴቶች፣ ከሐኪሞችና ከስነ-ልቡና ባለሙያዎች ባሰባሰቡት መረጃ መሠረት ሴቶቹ የተደፈሩት ጦርነቱ ከተጀመረበት ከሚያዚያ 2015 እስከ ሚያዚያ 2016 በነበረዉ አንድ ዓመት ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት አጥኚ ቡድን ባለፈዉ ጥቅምት ባወጣዉ ዘገባ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርም የመከላከያ ሠራዊት ባልደረቦችም በሴቶች ግፍ መዋላቸዉን አስታዉቋል።

ካይይሮ-እስራኤል ጋዛ ዉስጥ 27 ፍልስጤሞች ገደለች

የእስራኤል ጦር ዛሬ በተለያዩ የጋዛ ቀበሌዎችና ከተሞች በከፈተዉ ጥቃት በትንሹ 27 ፍልስጤማዉያንን ገደለ።ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ አቆሰለ።ሐኪሞችና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እንዳሉት አብዛኞቹ ሟቾች ሴቶች፣ ሕፃናትና አዛዉንታት ናቸዉ።ከሟቾቹ 10 የተገደሉት የእስራኤል ጦር ጋዛ ከተማ የሚገኝ አንድ ፎቆን በማጋየቱ ነዉ።እስራኤል ጋዛ ላይ የምትፈፅመዉን ጥቃት ለማቆምና የታገቱ የእስራኤል ዜጎችን ለማስለቀቅ የሚደረገዉ ዉጤት አልባ ዲፕሎማሲ ዛሬም መቀጠሉ ተነግሯል።

 

ሰነዓ-የአሜሪካ ጦር የመንን ደበደበ
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የየመን ሁቲዎች «ጦር መሳሪያ የተከማቸበት» ያለዉን አካባቢ መደብደቡን አስታወቀ።የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ እንደሚለዉ ጦሩ የየመንን ጦር መሳሪያ ያወደመዉ ኢላማዉን ነጥሎ በሚመታ ሚሳዬል ጭምር ነዉ።ጦሩ አክሎ እንዳለዉ ያወደመዉ ጦር መሳሪያ ሁቲዎች የአሜሪካን የጦርና የንግድ መርከቦች ለመደብደብ ያከማቹት ነበር።አዣንስ ፍራንስ የጠቀሰዉ የአሜሪካ ጦር መግለጫ የወደመዉን የጦር መሳሪያ ብዛት፣ ዓይነትም ሆነ የነበረበትን ሥፍራ አልጠቀሰም።እስራኤል በጋዛ ፍልስጤሞች ላይ የምትፈፅመዉን ግፍ በመቃወም የየመን ሁቲዎች እስራኤልንና ከና ወደ እስራኤል የሚጓዙ መርከቦችን ማጥቃት ከጀመሩ ወዲሕ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የብሪታንያና የተባባሪዎቻቸዉ ሐገራት ጦር ኃይላት የየመንን ሥልታዊ ሥፍራዎች በተደጋጋሚ ይደበድባሉ።

ፓሪስና የተለያዩ-የትራምፕ ዛቻና የአዉሮጳ-አሜሪካኖች ሥጋት
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የተለያዩ ሐገራት ግዛቶችን ለመቆጣጠር መዛታቸዉ የአዉሮጳና የአሜሪካ መንግሥታትን አስደንግጧል።ትራምፕ የማዕከላዊ አሜሪካዋን የፓናማ ቦይን፣ የዴንማርክን ግዛት ግሪንላንድንና ካናዳን በኃይል ጭምር ለመቆጣጠር እየዛቱ ነዉ።የሜክሲኮ ባሕረ ሠላጤ ደግሞ የአሜሪካ ባሕረ ሠላጤ ተብሎ እንዲሰየም ሐሳብ አቅርበዋል።የትራምፕን ዕቅድ ፓናማ፣ሜክሲኮ፣ ፈረንሳይና ጀርመን አጥብቀዉ ተቃዉመዉታል።የፈረንሳይ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዤን-ኖኤል ባሮት ዛሬ እንዳሉት አዉሮጳ ከሌላ ኃይል የሚደርስባትን ጥቃት ለመከላከል መዘጋጀት አለባት።ይሁንና ባሮት ዓለም «በጫካ ሕግ»  ወደ መገዛቱ እየተጓዘች መሆንዋን ጠቁመዋል።እየጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ Ueቴፋን ሔቤሽትራይት በበኩላቸዉ «ድንበሮች በይል አይጣሱም።» ብለዋል።የአዉሮጳ ሕብረት የትራምፕን ዕቅድ «ልቅ መላምት» በማለት ሲያጣጥለዉ፣ የሜክሲኮ ፕሬዝደንት ክላዉዲያ ሽይንባዉም በበኩላቸዉ «የሜክሲኮ ባሕረ ሠላጤ» ዓለም አቀፍ ዕዉቅና ያገኘ ሥም ነዉ ብለዋል።ማንም አይለዉጠዉም።
 

ቤጂንግ-በመሬት መንቀጥቀጥ 126 ሞቱ፣ 400 ዳኑ
የቻይናን ደቡብምዕራብ ራስ ገዝ ግዛት ሺዛንግን በመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ150 ሊበልጥ እንደሚችል የአደጋ ሰራተኞች አስታወቁ።ታሪካዊቱ ቲቤት  የምትገኝበትን ግዛት ትናንት የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እስካሁን 126 ሰዎች መግደሉ፣ ሁለት መቶ ያክል ማቁሰሉ ተረጋግጧል።የቻይና የአደጋ ሠራተኞች እንዳስታወቁት በሬክተር መመዘኛ 6.8 የተለካዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ካፈራረሳቸዉ ሕንፃዎች ዉስጥ 400 ሰዎች በይሕወት አድነዋል።ጉዳተኞችን ለመርዳት የዘመተዉ ጦር ኃይል መኮንን እንዳሉት አደጋዉ ከደረሰባቸዉ አካባቢዎች በርካታ ሰዎችን አሽሽተዋል።
               
«በአካባቢዉ እንደደረስን አደጋዉ ከባድ መሆኑን ተረዳን።ከበላይ አካል በተሰጠን ትዕዛዝ መሠረት በቡድን ተከፋፍለን ነዋሪዎችንና እንስሶችን ወደ ሌላ ሥፍራ እያሸሸን ነዉ።ይሁንና አሁንም ቢሆን የድሕረ መቀጥቀጥ ተደጋጋሚ ንዝረት አለ።ነብስ ለማደን እየጣርን ነዉ።»
የነብስ አንድ ሰራተኞች ፍርስራሽ የተጫናቸዉን ሰዎች ለማግኘት ከዜሮ በታች 18 ዲግሪ ሴልስየስ ከሚደርሰዉ ቀዝቃዛ ዓየር ጋር እየታገሉ ነዉ።የመሬት መንቀጥቀጡ ኔፓል ዉስጥም በሕንፃዎችን አፈራርሷል።
 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።