1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራዩ ጦርነት ትቶት ያለፈው አካላዊ ስነ ልቦናዊ ጠባሳ ይሽር ይሆን ?

ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 2016

በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሰው ህይወት ከቀጠፈው ፤ ለአካል ጉዳት እና ለስነ ልቦና ቀውስ ከዳረገው ብሎም የንብረት ውድመት ካስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ ትግራይ ውስጥ ህይወት ሌላ የተስፋ መንገድ ይዛለች። በጦርነቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ካጡ እና የትናንቱ ህይወታቸው እንዳልነበር ከሆነባቸው መካከል ሴቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ

https://p.dw.com/p/4hCy6
Äthiopien Tigray Krieg
ምስል Ximena Borrazas

የትግራዩ ጦርነት ያስቀረው ጠባሳ ይሽር ይሆን ?

በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሰው ህይወት ከቀጠፈው ፤ ለአካል ጉዳት እና ለስነ ልቦና ቀውስ ከዳረገው ብሎም  በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት የንብረት ውድመት ካስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ ትግራይ ውስጥ ህይወት ሌላ የተስፋ መንገድ ይዛለች። በጦርነቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ካጡ እና የትናንቱ ህይወታቸው እንዳልነበር ከሆነባቸው መካከል ሴቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ ። ጦርነቱ በደረሰባቸው በትግራይ በአማራ እና አፋር ክልሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ለአስገድዶ መደፈር ጥቃት መጋለጣቸው ሲታወቅ ከእነርሱ ውስጥ አሁንም ድረስ ቁስላቸው አልሽር ብሎ ከማህበረሰብ እስከመገለል እና ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውስ ተጋልጠው ህይወት የጨለመችባቸው ቀላል ቁጥር የሚሰጣቸው አይደለም። ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን በዛሬው የጤና እና አካባቢ ዝግጅታችን በቅርቡ ወደ ትግራይ ክልል የተጓዘችው የዶቼ ቬለዋ ዜሚና ቦሮዛ በጦርነቱ ወቅት ትግራይ ውስጥ  የአስገድዶ መደፈር ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች አነጋግራ አስከፊ ፤ አሳዛኝ እና ምናልባትም አንደኛውን የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ የተመለከተችበትን ዘገባ ይዘን ቀርበናል። 

የትግራዩ ጦርነት እና በሴቶች እና ህጻናት ያስከተለው አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተቀሰቀሰባት ትግራይ ከአስከፊው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ነዋሪዎቿ ህይወት እንደ አዲስ ለመጀመር ተስፋ የሰነቁ ይመስላል። ምንም እንኳ የሞተውን ባይመልስ ፤ የአካል ጉዳተኛውን ጉዳት ባይጠግን ፤ ለአስከፊ የስነ ልቦና እና ማህበራዊ እንግልት የተዳረገውን የተሰበረ ልብ ባይጠግግ ፤ በእርግጥ ነገን ለመጨበጥ ዛሬ በብህሩህ ተስፋ መነሳቱ  ሌላ ምርጫ አይኖረውም ።

በጦርነት የተጎዱት የትግራይ ክልል የጤና ተቋማት

የዶቼ ቬለዋ ዜሚና ቦሮዛ መቀሌ ስትደርስ ከሰማችው እና በርቀት በመገናኛ ብዙኃን መስኮቶች ከተመለከተችው ባሻገር የጦርነቱ ሰለባ የሆነችውን የትግራይ ምድር በእግሯ ረግጣ ፤ በአይኗ አይታ በአንደበቷ ጠይቃ የተረዳችው እና የተሰማትን በምስል አስደግፋ ከትባለች ። ምንም እንኳ ጦርነቱ በተለይ በትግራይ ክልል በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሁሉንም ደጅ ያንኳኳ ቢሆንም እንደ ሴቶች እና ህጻናት የቀውሱ ሰለባ የሆነ የለም ትላለች።

በመቀሌ ጎዳናዎች ዞር ዞር ስትል ያገኘቻቸው አንዲት የ70 ዓመት ባልቴት ለምግብ መግዣ የሚሆን ምጽዋት ፍለጋ እጃቸውን ለልመና መዘርጋታቸውን እንደተመለከተች የምትገልጸው ጋዜጠኛዋ ይህ በከተማዋ እዚህም እዚያም የሚታይ የትናንት ህይወት ግልባጭ ሌላ አስከፊ ገጽታ መሆኑን ታነሳለች። በእርግጥ ነው ይህ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍልም ብዙም እንግዳ ነገር ላይሆን ይችላል፤ የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት እንኳንስ በጦርነት ውስጥ ያሳለፈ ህብረተሰብን ይቅር እና በሰላሙ አካባቢ ያለውንም በብርቱ ስለመፈታተኑ መናገሩ ጉንጭ ማልፋት ነው የሚሆነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር የትግራይ ተወላጆች ማኀበር በሰሜን አሜሪካ ጥሪ አቀረበ

 ለጋዜጠኛዋ  እርሷ ከመጣችበት ማህበረሰብ ህይወት አንጻር አመዛዝናም ይሆናል የባልቴቷን ለልመና እጃቸውን የመዘርጋት ጉዳይ  ከዘገባዋ ውስጥ የሰነደችው ።   ጋዜጠኛዋ መሸትሸት ሲል ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ሲገባቸው   ህይወት ለማሸነፍ  በየአውራ ጎዳናው ለልመና እና ምናምን ሸጠው ህይወት ለማሸነፍ  የሚሯሯጡ ህጻናትን ባየች ጊዜ  የጦርነቱ ጠባሳ እንዲሁ በቀላሉ የማይሽር ማህበራዊ ቀውስ ጥሎ ስለማለፉ ትገልጻለች። ነገር ግን ከዚህም የከፋ ነገር ስለመኖሩ የተረዳችው ዘግይቶ ነበር። ጋዜጠኛዋ ታሪኩን እንዲህ ሰንዳዋለች ።

የመቀሌ ጎዳና
በመቀሌ ጎዳናዎች ዞር ዞር ስትል ያገኘቻቸው አንዲት የ70 ዓመት ባልቴት ለምግብ መግዣ የሚሆን ምጽዋት ፍለጋ እጃቸውን ለልመና መዘርጋታቸውን እንደተመለከተች የምትገልጸው ጋዜጠኛዋ ይህ በከተማዋ እዚህም እዚያም የሚታይ የትናንት ህይወት ግልባጭ ሌላ አስከፊ ገጽታ መሆኑን ታነሳለች።ምስል Ximena Borrazas

ቤተሰብ በትኖ ምስቅልቅል ህይወት ያስከተለው የሰሜኑ ጦርነት 

የትግራዩ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የ42 ዓመቷ ከበደሽ እና ቤተሰቦቿ ሕይወት አሁን ከተፈጠረው በእርግጥ በእጅጉ የተለየ ነበር።  አነስተኛ ሆቴል ከፍታ የተቀናጣ ባይሆንም ቤተሰቦቿን በአግባቡ ማስተዳደር የምትችል ብርቱ ሴትም ነበረች። በህወሃት እና በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት መካከል ትግራይ ውስጥ ግጭት ሲቀሰቀስ ግን ነገሮች በፍጥነት ተለዋወጡ ። ጦርነቱ ተጀምሮ ከአንድ ሳምንት በኋላ ከበደሽ የስምንት ዓመት ልጇን ይዛ ቃፍታ ወረዳ ውስጥ በእግሯ እየተጓዘች ሳለች ነበር ድንገት አምስት የወታደር መለዮ የለበሱ ሰዎች ያስቆሟት ። አራቱ ከጎረቤት ሀገር የመጡ ሲሆን አንደኛው የመከላከያ ሰራዊት አባል ነው ትላለች።

በትግራይ በጦርነት የተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች ጥሪ

ቁጣ በቀላቀለ ድምጸት ጠየቋት ፤ «ሕወሓት ውስጥ ሰው አለሽ ?» «አይ የለኝም»

ወታደሮቹ ለመልሷ ቁብም የሰጡ አይመስልም ። አምስቱም እየተፈራረቁ ደፈሯት ።

አብራት የነበረችውን የስምንት ዓመት ልጅ ለእርዳታ እንዳትጮህ በሳንጃ ከወጓት በኋላ የፈላ ዉሃ ሆዷ ላይ ደፉባት ።  ወታደሮቹ ጥለዋት ከሄዱ በኋላ የጭካኔ በትር ያረፈባት ከበደሽ የተራረፈቻትን አቅም አሰባስባ እንደምንም ብላ ልጇን አቅራቢያ ወዳለ ወታደራዊ ህክምና ጣቢያ ወሰደቻት ።

ከበደሽ በትግራዩ ጦርነት ወቅት ተመሳሳይ ጥቃት ከደረሰባቸው 120 ሺ ሴቶች መካከል አንዷ እንደሆነች ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋም የሆው የፍትህ እና ተጠያቂነት ዓለማቀፍ የጠበቆች ማህበር ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።

የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ሠነድ ያዘጋጀው የባለሙያዎች ቡድን ሥራውን አጠናቀቀ

በደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት የተከተላቸውን የስነ ልቦና እና ማህበራዊ መገለል መቋቋም ተስኗቸው ራሳቸውን ያጠፉ መኖራቸውን የትግራይ የዘር ማጥፋት አጣሪ ኮሚሽን በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተከታታይ ቡድን ኃላፊ አቶ ይርጋለም ገብረጻድቃን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

በራሷ እና በልጇ ላይ ከደረሰው በጭካኔ የተሞላ ጥቃት በኋላ ከበደሽ  ቀጥሎ ስለሚሆነው በእርግጥ ምንም እርግጠኛ አይደለችም።  ለሶስት ወራት ያህል አድዋ ውስጥ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ቆይታለች። የአድዋ ከተማ እንደ ከበደሽ ተመሳሳይ ጥቃት ሰለባ የሆኑ 1,374 ተጎጂዎችን አስጠልላለች። ከእነዚህ ውስጥ 86ቱ ለኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ የተጋለጡ ሲሆን 72ቱ ህጻናት ናቸው። ጦርነቱ እንዲህ አይነቶች በርካታ ያልተነገረላቸው በሰቆቃ የተሞሉ ታሪኮች ቅሪት ትቶ አልፏልም ትላለች ዜሚና ቦሮሳ

አዲስ ተስፋ 

አሁን የከበደሽ እና  የልጇ ህይወት በአንጻራዊነት እያገገመ ነው። ዶን ቦስኮ በተሰኘ የረድኤት ድርጅት አማካኝነት እዚያው ትግራይ ውስጥ  ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በሚያገግሙበት ተቋም ውስጥ እየተረዳች ትገኛለች። አንድ ቤት ውስጥ እንደ እርሷ ካሉ 10 ተጠቂዎች ጋር በጋራ ይኖራሉ ። ያለፉትን 4 ዓመታት በፍርሃት ፣ ጭንቀት እና መገለል ውስጥ ላሳለፉት እናት እና ልጅ ህይወትን እንደ አዲስ መጀመር ለእነርሱ ቀላል ነገር አልነበረም።  የከበደሽን ህይወት አስቀድመው የሚያውቁቱ ሲናገሩ እንዲህ እርዳታ ጠባቂ አልነበረችም ።

የጥቃቱ ሰለባ ህጻን
ትንሽዬ ሱቅ ከፍቼ ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እፈልጋለሁ ፤ ልጄ ዶክተር ሆና ራሷን እና ህዝቡን ማገልገል  ትፈልጋለች  ምስል Ximena Borrazas

 « እርሷ በእርሻ ስራ ተምሳሌት የሆነች ሴት ናት ። ተሳትፎዋ የሚገርም ነው። ጥሩ ምርት ታስገባለች ፤ ቤተሰቧንም ከበቂ በላይ መመገብ ችላለች።  ሆቴልም ከፍታ ሌሎች ሰራተኞችንም ቀጥራ ታሰራ የነበረች ሰው ናት ።»

ጦርነቱ ሲጀመር አራት ልጆች ጥሎባት  የሄደው ባለቤቷ ጦርነቱ ቆሞ የሞቱ መርዶ እስኪሰማ ድረስ የት እንደደረሰ አይታወቅም ነበር። ከአራቱ ልጆቿ አንዱ የትግራይ ኃይሎች አባል ሆኖ ሱዳን ውስጥ እንዳለ ከበደሽ አረጋግጣለች።

ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ምስጋና ይግባው እና በእጁ ከትቦ የላከላት ደብዳቤም ደርሷታል።

ከዚያ ሁሉ አስከፊ የመከራ ጊዜ በኋላ የተስፋ ጊዜ እንደመጣ የምትናገረው ከበደሽ የሞተ ባለቤቷ ባይመለስላት ፤ የደረሰባት አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት ጠባሳው ባይሽርላት ለልጆቿ ስትል ህይወትን እንደ አዲስ ለመኖር ትጓጓለች።

በትግራይ ክልል የሚሞቱን ሕፃናትና እናቶች ቁጥር እየጨመረ ነዉ

 « ትንሽዬ ሱቅ ከፍቼ ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እፈልጋለሁ ፤ ልጄ ዶክተር ሆና ራሷን እና ህዝቡን ማገልገል  ትፈልጋለች  »

ይህ ተስፋ ቀላል ተስፋ አይደለም ።  ከ600 ሺ በላይ ነብስ ሳይጠፋበት እንደማይቀር ከሚነገርለት እና ከክፍለ ዘመናችን አስከፊ ጦነቶች አንዱ የትግራዩ ጦርነት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የጦርነቱ ሰለባዎች ከደረሰባቸው ሰቆቃ ለመውጣት ይጣጣራሉ ። ነገር ግን አሁንም ቢሆን የተረጋገጠ ነገር አለመኖሩ ለህዝቡ ሌላ ስጋት ሳይሆን አይቀርም። ትግራይ ከጦርነቱ በፊት እንደነበረችው ልትመለስ አልቻለችም። የአስገድዶ መደፈር ዜናዎች እዚህም እዚያም ይይሰማሉ ። የፕሪቶሪያውን ስምምት ተከትሎ በህወሃት እና በፌዴራል መንግስቱ መካከል የነበረው መካረር መለሳለስ ቢያሳይም በህዝብ የተመረጠ ክልላዊ እና አስተዳደር እና ክልሉ በፌዴራል መንግስቱ ውስጥ መወከሉ እስኪረጋገጥ ድረስ ነገሮች ገና ይመስላሉ ።

የትግራይ ተወላጅ የፖሊስ አባላት ላይ ደረሰ የተባለ የመብት ጥሰት

ግን ደግሞ ተስፋ አይቆረጥም። በአምስት ሰዎች የተደፈረችው ፤ አይኗ እያየ ልጃ በሳንጃ ስትወጋ እና የፈላ ውሃ ሆዳ ላይ ሲፈስ የተመለከተች እናት ከዚህ ሰቆቃ አገግማ ተስፋ አድርጋ የለ ? በጦርነቱ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ወታደሮች እና በጦርነቱ በተሳተፉ የታጠቁ ኃይሎች  የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል ስለመፈጸሙ ሀገር በቀል እና ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርቶች ያመለክታሉ ። ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ይወተውታሉ ፤ በእርግጥ ለጠፋ ህይወት ፣ ለፈሰሰ ደም ፤ እንደከበደሽ ደግሞ ህይወት ላጨለመ ጥቃት ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባ ነበረ፤ ጊዜው ገና አልረፈደም።

የፎቶ ጋዜጠኛዋ  ዜሚና ቦሮዛ ወደ ትግራይ ተጉዛ ያጠናቀረችውን አጭር ዘገባ ያስተናገድንበት የዕለቱን የጤና እና አካባቢ ዝግጅታችንንም በዚሁ አበቃን ሳምንት በሌላ ዝግጅት እንጠብቃችኋለን ቸር እንሰንብት ።

ታምራት ዲንሳ 

አዜብ ታደሰ