1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 23 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 23 2017

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም መድረክ ምርጥ ተብለው ተመርጠዋል፤ ለድልም በቅተዋል ። ግብጻውያን የእግር ኳስ አጥቂዎች በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና ጀርመን ቡንደስ ሊጋ ገንነዋል ። ሊቨርፑል ከዋነኛ ተቀናቃኞቹ አንዱ ያለፈው የውድድር ዘመን ዋንጫ ባለድሉ ማንቸስተር ሲቲን ትናንት ጉድ አድርጓል ።

https://p.dw.com/p/4nf64
Monaco World Athletics Awards Sifan Hassan
ምስል FREDERIC DIDES/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም መድረክ ምርጥ ተብለው ተመርጠዋል፤ ለድልም በቅተዋል ። ግብጻውያን የእግር ኳስ አጥቂዎች በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና ጀርመን ቡንደስ ሊጋ ገንነዋል ። ሊቨርፑል ከዋነኛ ተቀናቃኞቹ አንዱ ያለፈው የውድድር ዘመን ዋንቻ ባለድሉ ማንቸስተር ሲቲን ትናንት ጉድ አድርጓል ። በጀርመን አራተኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ፉክክር ብጥብጥ 79 ሰዎች ተጎድተዋል ። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ባለፈው ሳምንት የዘንድሮ የዓለም አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው ሆላንዳዊው አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን በትናንትቱ ውድድርም አሸንፏል ።

አትሌቲክስ

ከስታዲየም ውጭ በተደረጉ ውድድሮች የ2024 የዓመቱ ምርጥ አትሌት ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ በዓለም አትሌቲክስ ተመርጦ አሸንፏል ። አዲስ ብቅ ካሉ አትሌቶች ደግሞ ከ20 ዓመት በታች በ3000 ሜትር የመሰናከል ሩጫ የዓለም ፉክክር ባለድሏ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሴምቦ ዓለማየሁ አሸንፋለች ። በኢትዮ ኤፍኤም 107.8 ኤፍ ኤም የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ የሁለቱን አትሌቶች እንቅስቃሴ በቅርበት ተከታትሏል ። ሁለቱ የኢትዮጵያ ድንቅ አትሌቶች በምን ይታወቃሉ፤ ለድልስ የበቁት በምን ምክንያት ነው? ምሥጋናው ሁለቱ አትሌቶች በጎርጎሪዮሱ 2024 ባስመዘገቡት አመርቂ ውጤት በኢንተርኔት ድምፅ አሰጣጥ እና በአትሌቲክስ ባለሞያዎች መመረጣቸው ገልጧል ።

የዓለም አትሌቲክስ ለፍጻሜው ለታጩት 12 አትሌቶች ደጋፊዎች የድምፅ አሰጣጥ ክፍት አድርጎ ነበር ።  ከ12ቱ የመጨረሺያ እጩዎች መካከል ነው ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ ለድል የበቃው ።

ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ
ከስታዲየም ውጭ በተደረጉ ውድድሮች የ2024 የዓመቱ ምርጥ አትሌት ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ ምስል Spada/LaPresse/IMAGO

እሁድ፤ ኅዳር 22 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ሞናኮ ፈረንሣይ ውስጥ በተደረገው የሽልማት ሥነሥርዓት አሸናፊነቷ ይፋ ከሆነው ሴምቦ ዓለማየሁ ጋር የሠርቢያዋ አንጄሊና ቶፒክ እና የቻይናዋ ዛን ዚዪ ለፍጻሜ ቀርበው ነበር ።  አንጄሊና የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ ስትሆን፤ ዛን ደግሞ በጦር ውርወራ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ናት ። በወንዶች አዲስ ብቅ ካሉ አትሌቶች አሸናፊው የእመርታ ዝላይ የኦሎምፒክ ባለድሉ የጣሊያኑ ማቲያ ፉርላኒ ነው ። ከዚህ በተጨማሪ፦ በሴቶች የስታዲየም ውድድር የ400 ሜትር መሰናክል ዝነኛዋ አሜሪካዊት ሲድኒ ማክላውግሊን፤ በሴቶች የጎዳና ውድድር ደግሞ ዩክሬናዊቷ ያሮስላቭ ማሁቺክህ አሸንፈዋል ። በምርኩዝ የከፍታ ዝላይ የኦሎምፒክ ባለድሉ ስዊድናዊው ሞንዶ ዱፕላንቲስ በወንዶች የጎዳና ውድድር አሸናፊ ሁኑ ተመርጧል ። የኅዳር 16 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ስታዲየም ውስጥ በተደረጉ ውድድሮች ደግሞ፦ የዓመቱ የዓለም ምርጥ አትሌት በሚለው ዘርፍ ደግሞ የቦትስዋናው ሌጺሌ ቴቦጎ አሸናፊ ሁኗል ። ይህ አትሌት ከትውልደ ኢትዮጵያ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሐሰን ጋር የዓለም የዓመቱ ምርጥ አትሌትም ተሰኝቷል ።

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና፦ ስፔን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የቫሌንሺያ ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መገርቱ ዓለሙ አሸናፊ ሁናለች ። በቫሌንሺያ ማራቶን በወንዶች ተመሳሳይ  የሩጫ ፉክክር  ኬንያዊው ሰባስቲያን ሳዌ አንደኛ በመውጣት አሸንፏል ።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መገርቱ ዓለሙ
የቫሌንሺያ ማራቶን አሸናፊ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መገርቱ ዓለሙ ምስል Pablo Morano/REUTERS

35,000 ሰዎች በተካፈሉበት 44ኛው የቫሌንሺያ ማራቶን መገርቱ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2 ሰዓት ከ 16 ደቂቃ ከ 49 ሰከንድ ነው ። ዩጋንዳዊቷ ስቴላ ቼሳንግ ሁለተኛ ፤ ኢትዮጵያዊቷ ጡሩዬ መስፍን ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በዚሁ የወንዶች ማራቶን ፉክክር ኬንያውያን አንደኛ እና ሁለተኛ ወጥተዋል ። አሸናፊው ሰባስትያን ሳዌ ሩጫውን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ02 ደቂቃ ከ 05 ሰከንድ ፈጅቶበታል ።  የትናንቱ ድሉም በወንዶች የማራቶን ታሪክ አምስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። ከአሸናፊው 33 ሰከንድ ዘግየት ብሎ የገባው ኢትዮጵያዊ ደሬሳ ገለታ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ዳንኤል ማታይኮ 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ 24 ሰከንድ በመሮጥ ሦስተኛ ሆኗል ። የኅዳር 09 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ፕሬሚየር ሊግ

የሊቨርፑል አጥቂ ሉዊስ ዲያዝ በሻምፒዮንስ ሊግ
ድሮ በዚህ አካሄዱ ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ አያጠራጥርም የሚሉ በርካቶች ናቸውምስል Carl Recine/Getty Images

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑልን የሚያስቆመው አልተገኘም ። ሊቨርል ትናንት ማንቸስተር ሲቲን አንፊልድ ሜዳው ላይ ማንቸስተር ሲቲን አስተናግዶ 2 ለ0 ሸኝቶታል ። ኮዲ ጋክፖ ከግብፃዊው አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅ ተመቻችቶ የተሰጠውን ኳስ 20ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል ። 78ኛው ደቂቃ ላይ ሞሐመድ ሣላኅ በፍጹም ቅጣት ምት ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል ። በዚህም በግብ ክፍያ በኧርሊንግ ኦላንድ በአንድ ብቻ ተበልጦ 11 ግቦችን አስመዝግቧል ። ግቧ ከተቆጠረች በኋላ ሞሐመድ ሣላኅ ለኧርሊንግ ኦላንድ በጆሮው አንዳች ነገር ሹክ ብሎት ሁለቱም ፈገግ ብለዋል ።  ሊቨርፑል በትናንቱ ድል ያገኘው ተደምሮ በ34 ነጥቡ ደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ነው ።

ዌስትሀምን ቅዳሜ ዕለት 5 ለ2 ያሸነፈው አርሰናል በ25 ነጥብ ይከተላል ። አስቶን ቪላን 3 ለ0 የሸኘው ቸልሲ በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው ።   ማንቸስተር ሲቲ  በተመሳሳይ 23 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ በብራይተን ተበልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ዘንድሮ በዚህ አካሄዱ ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ አያጠራጥርም የሚሉ በርካቶች ናቸው ። ትናንት ኤቨርተንን 4 ለ0 ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ በ19 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

ቡንደስሊጋ፦ ሳንክት ፓውሊ እና ሆልሽታይን ኪዬል
በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ሳንክት ፓውሊ እና ሆልሽታይን ኪዬልምስል Cathrin Mueller/REUTERS

ቡንደስ ሊጋ

ጃማል ሙሳይላ ባዬርን ሙይንሽ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር በነበረው ግጥሚያ ባለቀ ሰአት ታድጎታል ። በደረጃ ሰንዘጠረዡ በ26 ነጥብ ተከታይ የሆነው አይንትራኅት ፍራንክፉርት ድል ሲቀናው፤ ላይፕትሲሽ ም ብርቱ ሽንፈት አስተናግዷል ።

ጃማል ሙሳይላ ባዬርን ሙይንሽንን ከሽንፈት የታደገው 85ኛው ደቂቃ ላይ ነው ። እስከዚያ ድረስ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ27ኛው ደቂቃ ላይ በጃሚ ጊቴንስ ባስቆጠረው ግብ አንድ ለባዶ እየመራ ነበር ። ግብጻዊው አጥቂ ዖማር ማርሙሽ ሁለት ግቦችን ከመረብ ባሳረፈበት ግጥሚያ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ትናንት ሐይደንሀይምን 4 ለ0 በገዛ ሜዳው ጉድ አድርጎታል ።

በዚህ የጨዋታ ዘመን ለአይንትራኅት ፍራንክፉርት በ14 ጨዋታዎች 12 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ 8 ግብ የሆኑ ኳሶችን ያመቻቸው ዖማር ማርሙሽ ከአውሮጳ አሉ ከሚባሉ ግብ አዳኞች ተርታ መሰለፍ ችሏል ። ቅዳሜ ዕለት ዑኒዮን ቤርሊንን 2 ለ1 ያሸነፈው ባዬርን ሌቨርኩሰን በ23 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በቮልፍስቡርግ  የ5 ለ1 ሽንፈት ያስተናገደው ላይፕትሲሽ በ21 ዶርትሙንድ በ20 ነጥብ አራተኛ እና አምስተኛ ናቸው ። ትናንት ማይንትስ ሆፈንሀይምን 2 ለ0 አሸንፏል ።

ምሥራቃዊ ጀርመን ውስጥ በነበረ የአራተኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ፉክክር ብጥብጥ 79 ሰዎች ተጎድተዋል ። ከተጎጂዎቹ መካከል የስታዲየም አስተናጋጆች እና ፖሊሶችም ይገኙበታል ። ተፎካካሪ የነበሩት ሁለት ቡድኖች ብጥብጡን አውግዘዋል ። በደጋፊዎች መካከል ግጭቱ የተቀሰቀሰው፦ ካርል ሳይሲስ ዬና የተሰኘው ቡድን ኬሚ ላይፕትሲሽን ቅዳሜ ዕለት አስተናግዶ 5 ለ0 ካሸነፈ በኋላ ነው ። የኅዳር 02 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ከተጎጂዎቹ መካከል 10 ፖሊሶች እና አምስት የስታዲየም አስተናባሪዎች እንዲሁም 64 ደጋፊዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጧል ። ፖሊስ 40 ሰዎችን በወንጀል እና በሥርዓት አልበንነት ጠርጥሮ ክስ መስርቷል ። ዬና የተሰኘው የእእግር ኳስ ቡድን በምሥራቅ ጀርመን ቱሪንጊያ ግዛት ከላይፕትሲሽ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል ። 

በአራተኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ግጥሚያ ወቅት ፖሊስ ኹከቱን ለማብረድ ጣልቃ ገብቷል
በአራተኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ግጥሚያ ወቅት ፖሊስ ኹከቱን ለማብረድ ጣልቃ ገብቷል ምስል EHL Media/IMAGO

ብጥብጡ የተነሳው፦ 7,224 ተመልካቾች በነበሩበት ግጥሚያ ወደ 1,200 የሚጠጉ የተሸናፊው ቡድን ደጋፊዎች የዬና ቡድን ደጋፊዎች ወዳሉበት ስፍራ ጥሰው በማለፋቸው መሆኑን የካርል ሳይሲስ ዬና ቡድን ትናንት በጽሑፍ መግለጫ ዐሳውቋል ። ኬሚ ላይፕትሲሽ ቡድን በተመሳሳይ መግለጫ የቡድኑ «ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎች ያልተገባ ጠባይን» ነቅፏል ። ሁለቱም ቡድኖች ክስተቱ ላይ ምርመራ እንደሚያከናውኑ ይፋ አድርገዋል ። ኹከት ፈጣሪ ደጋፊዎቹ በአብዛኛው የግራ ዘመም ፖለቲካ ደጋፊዎች ናቸው ተብሏል ።

የመኪና ሽቅድምድም

የዘንድሮ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዓለም ባለድል ሆላንዳዊው ማክስ ፈርሽታፐን ትናንት በካታር የመኪና ሽቅድምድም ዳግም አሸንፏል ። ተከታታይ አራተኛ የውድድር ዘመን ድሉን ባለፈው የላስቬጋስ ውድድር ወቅት ያረጋገጠው የሬድ ቡል አሽከርካሪ በትናንቱ ፉክክርም አንደኛ ወጥቷል ።

ሆላንዳዊው ማክስ ፈርሽታፐን
የዘንድሮ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዓለም ባለድል ሆላንዳዊው ማክስ ፈርሽታፐንምስል Evelyn Hockstein/REUTERS

የጥቅምት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ የ27 ዓመቱ የሬድ ቡል አሽከርካሪ የትናንቱን ጨምሮ በአጠቃላይ 429 ነጥብ የውድድር ዘመኑ አሸናፊ ቢሆንም በሌሎች ተፎካካሪዎች ቅሬታ ቀርቦበታል ። በሽቅድምድሙ መጀመሪያ ላይ መንገድ ዘግቶብኛል ሲል የመርሴዲስ አሽከርካሪው ጆርጅ ሩሴል አማሯል ። በፍጥነት ሳሽከረክር መንገዱን ስለዘጋብኝ ለጥቂት ልጋጭም ነበር ብሏል ።  በውድድሩ ለሌላ አላሰበም የሚል ቅሬታ የቀረበበት ማክስ ፈርሽታፐን ከጆርጅ ሩሴል ጋር እንዲነጋገሩ ተጠይቆ ለጊዜው ፍላጎት እንደሌለው ዐሳውቋል ። ብሪታንያዊው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተንም ተግባራዊ ባይሆንም ማክስ እንዲቀጣ ክስ አቅርቦ ነበር ። በትናንቱ ፉክክር ሌዊስ የ12ኛ ደረጃ ይዞ ነው ያጠናቀቀው ። 

በትናንትናው የካታር ሉሳይል ሽቅድምድም ማክስ ፈርሽታፐን አንደኛ ሲወጣ፣ ሻርል ሌክሌር የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የማክላረኑ አሽከርካሪ ዖስካር ፒያስትሪ የሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አዜብ ታደሰ

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti