1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልልና የአማራ ፋኖ በጎጃም እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ ስለተባሉ ታጣቂዎች የተናገሩት

ዓለምነው መኮንን
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 24 2017

ለመንግሥት እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰራባ የተሀድሶ ማዕከል መግባታቸውን የቢሮው ም/ኃላፊ አቶ በሪሁን መንግሥቱ ተናግረዋል። የአማራ ፋኖ በጎጃም «አንድም የፋኖ ታጣቂ ለመንግሥት እጅ አልሰጠም»ብሏል“እጅ ሰጡ የተባሉት አካላት አንድም፣ የድርጅቱ አባላት አይደሉም፣ አሊያም መንግሥት ራሱ ያደራጃቸው አካላት ናቸው” ብሏል።

https://p.dw.com/p/4ole2
እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ የተባሉ ታጣቂዎች
እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ የተባሉ ታጣቂዎች ምስል Central Gondar Zone communications

የአማራ ክልልና የአማራ ፋኖ በጎጃም እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ ስለተባሉ ታጣቂዎች የተናገሩት

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ታጣቂዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ለመንግሥት እጅ እየሰጡ እንደሆኑ የአማራ ክልል መንግሥት እየገለፀ ነው፡፡ ቀደም ሲል በአማራ ክልል አዊ በሔረስብ አስተዳድር ነፍጥ አንስተው መንግስተን ሲወጉ ከነበሩ ታጣቂዎች መካክል “የመንግሥትን የሠላም ጥሪ ተቀብለዋል” የተባሉ ታጣቂዎች ከእነመሳሪያቸው ወደመንግሥት ሲገቡ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መንግሥት የሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሐን በተከታታይ ቀናት ሲያሳዩ ሰንብተዋል።

የመንግሥትን የሠላም ጥሪ ተቀብለው በሁሉም የአማራ ክልል አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከ4 ሺህ በላይ ታጣቂዎች ወደ መንግሥት መግባታቸውን የአማራ ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ስሞኑን ተናግረዋል። «በዚህ ሰሞን ከአዊ ዞን በተጨማሪ በሌሎችም በክልሉ ባሉ ቀጣናዎች ባሉ 4038 የሚሆኑ የታጠቁ ኃይሎች ይብቃ ብሎ መምጣት ጨዋነት ነው ። ይቅርታ ከምንም በላይ ለሰው ልጆች በጣም ትልቁ የሰውነት መገለጫችን መሠረታዊ ጉዳይ ነው።» 

በሠላማዊ መንገድ ወደ መንግሥት የገቡ ታጣቂዎች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሰራባ ወደተባለ የተሀድሶ ማዕከል መግባታቸውን ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሁን መንግሥቱ ተናግረዋል።
አቶ በሪሁን ታጣቂዎቹ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መንግሥት ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችም ገልጠዋል። «ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ በዘላቂነት ህይወታቸውን እንዴት መምራት መቻል አለባቸውየሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ አኳያ የክልሉ መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመሆን እነዚህ ልጆች የተደረገውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከመጡ ለነሱ የሚፈለገውን ነገር ሁሉ  የማድረግ ሀላፊነት አለ።» የአማራ ፋኖ በጎጃም በበኩሉ “አንድም የፋኖ ታጣቂ ለመንግሥት እጅ አልሰጠም” ብሏል፣ “እጅ ሰጡ የተባሉት አካላት አንድም፣ የድርጅቱ አባላት አይደሉም፣ አሊያም መንግሥት ራሱ ያደራጃቸው አካላት ናቸው” ነው ያለው።

እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ የተባሉ ታጣቂዎች
እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ የተባሉ ታጣቂዎች ምስል Central Gondar Communications


የአማራ ፋኖ በጎጃም የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ዓለማየሁ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢ እጅ ሰጡ ስለተባሉ ታጣቂዎች ሲናገሩ፣
«አጎ ሸንጎ የነበሩ ኑ ወደዚህ ከኛ ጋር እንታገል አብረን ወገን ነን ተብለው ተለምነው እምቢ ብለው በፋኖ ስም እየነገዱ አስቸግረው የነበሩ ሲሆን ፋኖ በነርሱ ላይ እርምጃ ሊወስድ እንቅስቃሴ ሲጀምር ከዚያ ለማምለጥ ድሮውንም የመንግሥት ተልዕኮ ይዘው ሲሰሩ የነበሩ ስለነበሩ እንዲህ ያለ ሲሆን ነው ወደነሱ የገቡት ።አ ዎ ገብተዋል። ግን ከመጀመሪያውም ከፋኖ ጋር አልነበሩም , የፋኖ ወገን አልነበሩም እያስመሰሉ የሚኖሩ ስለነበሩ ፋኖ አልነበሩም»ብለዋል ። በሌሎች አካባቢዎችም ቢሆን “ለመንግሥት እጅ ሰጡ” የተባሉ አካላት መንግሥት ራሱ ያደራጃቸው ኃይሎች እንጂ የፋኖ ታጣቂዎችን  አይወክሉምንም ሲሉም አብራርተዋል።

እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ የተባሉ ታጣቂዎች
እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ የተባሉ ታጣቂዎች ምስል Central Gondar Communications


«ፋኖ የሚመስል ነገር እንውለድ ብለው ስራ ሰጥተው ነበር። ለነርሱ የሚታዘዝ ይኽው ፋኖ እኮ ይሄ ነው ብለው ብዙ የሚያታልሉበት። የፋኖ አስመስለው ሚሊቴሪ ያልሆነ ሰው ፎቶ ሊያነሱ ይችላሉ እንዲህ ዓይነት ስራ ለመስራት ሞክረዋል። በየመንገዱ እያስቆመ የሚያዘርፍ አካል አለ። እነዚህ ፋኖን እያስመሰሉ ይዘርፋሉ። ህዝቡን ያስደበድባሉ፤መኪና ያስቃጥላሉ፤ስለዚህ ራሳቸው የወለዱት የራሳቸው አካል እንጂ ፋኖ በፍጹም እንዲህ የሚረግ ሞራልም ስራም የለንም። » በአማራ ክልል ያለው ጦርነት በሠላማዊ መንገድ እንዲቋጭ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጌያለሁ ቢልም ከታጣቂዎች በኩል እስካሁን ይፋዊ የሆን ምላሽ አልተሰማም። የክልሉን ልዩ ኃይል እንደገና ለማደራጀት በሚል ሰበብ በአማራ ክልል የተከሰተው አለመግባባትና ጦርነት ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል።