1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ አከባበር

ቅዳሜ፣ መስከረም 23 2013

በአዲስ አበባ ከ150 ዓመታት በኋላ አምና ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ ተከብሮ ዋለ። በዓሉ ኮቪድ 19 አሳድሯል በተባለው ጫና ምክኒያት ግን በተለመደው ድምቀት ሳይሆን በውስን ሰዎች ተሳትፎ ነው ተከብሮ የዋለው።

https://p.dw.com/p/3jNx8
Äthiopien | Oromo Thanksgiving Irreecha in Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ አከባበር

የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ፀሃፊና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ በበዓሉ አከባበር ወቅት ባስተላለፉት መልእክት የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል አከባበር በውስን ሰዎች ታዳሚነት ብቻ እንዲከበር ያስገደደው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት መሆኑን በማስረዳት፤ ህብረተሰቡ በየአከባቢው በዓሉን እንዲያከብሩት ጠይቀዋል፡፡ ወጣቶች በተለይም የሆራ-ፊንፊኔ ኢሬቻ አከባበር እንደሚናፍቁ እረዳለሁ ያሉት አባገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ ለከርሞ በዓሉን በተለመደው ደማቅ ተሳትፎ ማክበር ይቻልም ዘንድ ምኞታቸውን አስረዱ፡፡

Äthiopien | Oromo Thanksgiving Irreecha in Addis Abeba
የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ አከባበርምስል Seyoum Getu/DW

የአባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢና የጉጂ አባገዳ ጂሎ ማንኦ በበኩላቸው የዘንድሮ እሬቻ በውስን ሰዎች ተሳትፎ ብቻ እንዲከበር ውሳኔውን ያስተላለፈው የአባገዳዎች ህብረት መሆኑን በማስረዳት ይህም በኮሮና ተዋሲ ስርጭት ስጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቨሌ የገለጹት የበዓሉ ታዳሚዎችም፤ ኢሬቻ የሰላምና የአንድነት መገለጫ ስፍራ፣ የኦሮሞ ህዝብ ከየአቅጣጫው ተሰባስበው በዓመት አንዴ መገናኛ ቦታ መሆኑን በመግለጽ፤ የዘንድሮ በዓል ግን እጅጎን ተቀዛቅዞ መስተዋላቸውን ተናገሩ፡፡ ይህም የኮሮና ተዋሲ ያሳደረው ትልቁ ተጽእኖ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች ለከርሞ ግን የተለመደው ደማቁ እሬቻ በሽታው ጠፍቶ፣ ሰላሙም ሰፍኖ ዴሞክራሲውም በልጽጎ እንገናኝ ዘንድ ምኞታችን ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አከሉ፡፡

Äthiopien | Oromo Thanksgiving Irreecha in Addis Abeba
የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ አከባበርምስል Seyoum Getu/DW

ዛሬ ከማለዳው በርካቶች ተነስተው እሬቻ ወደ ሚከበርበት ስፍራ ለማቅናጽ ቢተሙም፤ መግቢያ ካርድ ከያዙና ከተፈቀደላቸው ውጭ ማለፍ እንደሚከለከል የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ስዩም ጌቱ በቦታው ተመልክቷል፡፡ መግቢያ ካርድ ያልያዙ ወጣቶች አልፎ አልፎ ከመንግስት የጸጥታ አካላት ጋር ስወዛይ ገቡም ታይተዋል፡፡ የፀጥታ ሃይሎቹ ግን ለመስቀል አደባባይ ባሉት አራቱም አቅጣጫ፤ በየመተላለፊያ መንገዶቹ ቆመው ነበርና በከፍተኛ ፍተሸ ውስን ታዳሚዎችን ብቻ ሲያሳልፉ ነበር፡፡

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቨሌ ያገሩን ውስን ወጣቶችም የመግቢያ ካርዱን ማግኘትና የዛሬው ኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ ላይ መታደም ከፍተኛ ትግል የምጠይቅ ብለውታል፡፡

ስዩም ጌቱ