1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ቅድ ባለሙያዎቹ እንስቶች

ሐሙስ፣ መስከረም 26 2015

ሴና ግርማና ሃና በቃና የኦሮሞ ባህላዊ እና ዘመናዊ አልባሳት ቅድ ባለሙያ ናቸው። ባለሙያዎቹ ባህላዊ አልባሳት በአዳዲስ ዲዛይኖች ሲያዘምኑ ባህላዊ እሴቶቻቸውን እንዳይለቁ እንደሚጨነቁ ይናገራሉ። ለሁለቱ ወጣት ባለሙያዎች እንደ ኢሬቻ ያሉ ክብረ በዓላት ሥራዎቻቸው ለዕይታ እንዲበቁ አግዘዋቸዋል። የልብስ ቅድ ባለሙያዎቹን ሥዩም ጌቱ አነጋግሯቸዋል

https://p.dw.com/p/4Hreh
ዲዛይነር ሃና በቃና ኦሮሊያና የባህል አልባሳት ዲዛይን ባለቤት
ዲዛይነር ሃና በቃና ኦሮሊያና የባህል አልባሳት ዲዛይን ባለቤትምስል Seyoum Getu/DW

የባህል መድረክ፦ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ቅድ ባለሙያዎቹ እንስቶች

ዲዛይነር ሃና በቃና ኦሮሊያና የባህል አልባሳት ዲዛይን ስራዋን ከጀመረች ገና አንድ ዓመት ማለፉ ነው፡፡ ዲዛይነሯ “የልጅነት ህልሜ” የምትለውን ሙያውንም ድንገት ከመንገድ ጎራ ብላ እንዳልጀመረችውና ሙያውን በትምህርትም ጭምር ማስደገፏን ትገልጻለች፡፡ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በፋሽን ዲዛይን እና ኢሉስትሬሽን ለአምስት አመታት ተምራ በዲግሪ የተመረቀችበት ሙያዋ የግል ስራዋን የምትፈጥርብት እንደሆነም አስቀድማ ወጥናለች፡፡ ዲዛይነር ሃና ኦሮሊያና ያለችውን የዲዛይን እና የባህል አልባሳት ድርጅትም “የቆንጆ የኦሮሞ የባህል አልባሳት ቤት” የሚል ትርጓሜ ይኖረዋልና ለዚያው ትታትራለች፡፡

ሃና በአስተያየቷ ቀጥላ ስታስረዳ ዓመቱን ሙሉ በተመሳሳይ አኳኃን የማይቀጥለው የባህል አልባሳት ገበያ እንደየ የሚፈለጉበት ዓላማ ዲዛይን እና ቀለማቸው እንደሚለያይም ትገልጻለች፡፡ “ለልደትና፣ ለሰርግ እና ለሌሎች የአደባባይ በዓላት የምንጠቀመ የቀለም ቅይጦች የሚለያዩ ናቸው” ስትልም ሙያው ትኩረትና እውቀት እንደሚሻው ታስገነዝባለች፡፡

አሁን አሁን በሰፊው እየታወቀ የመጣው የሴና ዲዛይን እና የባህል አልባሳት ባለቤት እና መስራች ሴና ግርማ በበኩሏ ባለፉት 4-5 ዓመታት በስራው ላይ በቆየችባቸው ጊዜያት በኢንደስትሪው እምርታን አሳይታለች፡፡ ሴናም እንደምትለው በሙያው ላይ የነበራት ፍላጎት ወደ ስራው የገፋት ዋና ምክኒያት ነው፡፡ አላቂ ልብሶች እና ጫማዎችን በመሰብሰብ ለተለያዩ የሙከሪያ ስራ ይውሉበት የነበረው እሩቅ ቦታ ለመድረስ ዓልሞ የመነሳት ጥረት ዛሬ ላይ የእውቅ የባህል እልባሳት ዲዛይን የበርካታ ታዋቂ ሰዎች ጭምር ምርጫ ለመሆን በቃ፡፡ ሴና እንደምትለው ውጣ ውረዱ ግን ቀላል አልነበረም፡፡ በቅርብ ጊዜያት በርካታ እውቅ ሙዚቀኞች የሙዚቃ አልበምና ክሊፕ ሲሰሩ የእሷን የዲዛይን ጥበብ መርጠው ለአደባባይ አብቅተውታል፡፡

 የሴና ዲዛይን እና የባህል አልባሳት ባለቤት እና መስራች ሴና ግርማ
የሴና ዲዛይን እና የባህል አልባሳት ባለቤት እና መስራች ሴና ግርማ ምስል Seyoum Getu/DW

የባህል አልባሳቱን በራሷ ዲዛይን በማድረግ እስከ ስፌትም ከስሯ ከቀጠረቻቸው ሰዎች በተጨመሪ በመስራት የምትታወቀው ዲዛይነር ሃና በቃና እስካሁን ሰርታ በሰዎች ስለታወቀችባቸውና ስለተወደዱላት ዲዛይኖች ብሎም በጉልህ ስላስተዋወቃት መድረክም ታስታውሳለች፡፡ “ባለፈው ዓመት የ2014 ዓ.ም. የኢሬቻ ፋሽን ሾው ላይ ያቀረብኩት የባህል አልባሳት ዲዛይኖች በእጅጉ ተወደውልኝ ነበር፡፡ ያነ ብዙም አልታወኩም፡፡ በወረቀት ዲዛይን የማደርጋቸውን ሃሳቦች በጨርቅም እራሴ በመስፋት ወደ ልብስነት የምቀይረውም እነው እራሴ ነበርኩ፡፡ አሁን እንኳ የተወሰኑ ሰዎችን ቀጥሬ ማሰራት ጀምራለሁ፡፡” ሃና በአንድ ዓመቱ የባህል አልባሳት ዲዛይን ድርጅት ምስረታ ውስጥ ያሳየችው እምርታ “ተመስገን የሚያስብል ነው” ስትል ተስፈኝነቷንም ትገልጻለች፡፡ አሁን አሁን የበርካታ ታዋቂ ሙዚቀኞች እና የፊልም ባለሙያዎች ለባህል አልባሳቱ ዲዛይን ተመራጭ ሲያደርጓት ትስፋዋን ይበልጥ ማለምለሙንም ታስረዳለች፡፡

ዲዛይነር ሃና በቃና ኦሮሊያና የባህል አልባሳት ዲዛይን ባለቤት
ዲዛይነር ሃና በቃና ኦሮሊያና የባህል አልባሳት ዲዛይን ባለቤትምስል Seyoum Getu/DW

ዲዛይነሮቹ ባህላዊ የኦሮሞ አልባሳቱን በአዳዲስ ዲዛይኖች ሲያዘምኑ ባህላዊ እሴትና ይዘቱን እንዳይለቅ ግን ብዙ እንደሚጨነቁ ያነሳሉ፡፡ በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የሚለበሱ የባህል አልባሳቱ የተለያዩ የቀለም አይነቶች እና ይዘት ያላቸው መሆናቸው ደግሞ ለዚህ ለሚፈጥሩት የዲዛይን ፈጠራ አይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትላቸው ነው የሚገለጹት፡፡ 
የባህል አልባሳትን በዘመናዊ መልኩ የማዘወተሩ ነገር አሁን አሁን በሰፊው እየተስተዋለ ነው፡፡ ይሁንና በአንድ ሰው ላይ የሚታይ ወይም አብዝቶ ሚዘወተሩ ዲዛይኖችን መምረጥ ግን የብዙዎች ምርጫ አይሆንም፡፡ ይህ ደግሞ በዲዛይነሮቹ ላይ የእለት ተእለት የፈጠራ ብቃትና ጥረትን የሚጨምር ይሆናል፡፡ ዲዛይነሮቹ የኦሮሞ የባህል አልባሳቱን እለት ተእለት ጥቅም ላይ ወደ ሚውል አላባሳት ስለማምጣትም ያልማሉ፡፡

ስራው ብርቱ ፈተናዎችም ያሉት ነው፡፡ የግብዓት እጥረት፣ የባህል አልባሳቱ የተወሰኑ ወቅቶች ላይ ብቻ ጎልቶ መፈለግ እና በዚሁ ወቅት የበዛ የደንበኞች ትዕዛዝ ዲዛይነሮቹን ጫና ውስጥ የማስገባቱ ናቸው፡፡ በአዲስ ዓመት መባቻ በመስቀል እና ኢሬቻ የባህል አልባሳቱ በብርቱ ተፈላጊ ሲሆኑ አልፎ አልፎ ለልደት፣ ሰርግ እና መሰል ቤተሰባዊ ጉዳዮች ላይም ይፈለጋሉ፡፡ 
ከዶይቼ ቬለ ጋር ስለባህል አልባሳቱ የዲዛይን ጥበብ አስተያየታቸውን ለማጋራት ለቃለምልልስ የተቀመጡት ዲዛይነር ሴና ግርማ እና ዲዛይነር ሃና በቃና፤ አሁን አሁን ገበያውን እያሞቀ ስለሚገኘው የባህል አልባሳት ዲዛይን አዋጭነት እና ሊደርሱበት ሲለሚፈልጉ ግባቸውም አጋርተውናል፡፡ 

የዲዛይነር ሃና በቃና ሥራዎች
የዲዛይነር ሃና በቃና ሥራዎችምስል Seyoum Getu/DW

ምንም እንኳ የባህል አልባሳቱ የሚፈለጉባቸው ጊዜያት ውስን ሁነቶች ላይ የነበሩ ቢሆንም አሁን አሁን ለሰርግ፣ ልደት፣ ምርቃትና ሌሎችም አጋጣሚ መፈለጋቸው በስራው የመተዳደር ብሎም በዘርፉ በኢኮኖሚም ጭምር የመላቅ ተስፋቸውን ማለምለሙን ይገልጻሉ፡፡

በፋሽን ኢንደስትሪው የአገር ባህል አልባሳትን ወደ ትልቅ ኩባንያዎች በማሸጋገር ዓለማቀፋዊ ማድረግ እና አልባሳቱ የባህል ይዘታቸውን እንዳይለቁ መጣር አንዱና ዋነኛው ግባቸው መሆኑንም ዲዛይነሮቹ ያስገነዝባሉ፡፡

ለሌሎች ሰዎችም የስራ እድል መፍጠር የጀመሩት እነኚ ዲዛይነሮች የቢዝነስ ግባቸውን ከማሳካት ባሻገር የህዝባቸውን ባህል እና ማንነት ማስተዋወቅ እና ማሳደግ ላይ አተኩረው እንደሚሰሩም ነው የገለጹልን፡፡

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ