የኮሬ ዞን መንግሥት ሠራተኞች አቤቱታ
ሰኞ፣ ጥር 5 2017ሠራተኞቹ እንደሚሉት ቀደምሲል በልዩ ወረዳ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ በዞኑ ደረጃ በተዋቀረው የኮሬ ዞን መስተዳድር ከ20 እስከ 30 ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል ፡፡ አሁን ላይ ግን የዞኑ መስተዳድር ያለምንም ማስጠንቀቂያና ዝግጅት ወደ ወረዳ እንደበተናቸው ነው የሠራተኞው ተወካዮች ነን ያሉ ለዶቼ ቬለ የገለጹት ፡፡ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ኮሬ ዞን ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች ተገደሉ
ከዞን መዋቅር ወደ ወረዳ እንዲሄዱ ከተገደዱት ሠራተኞች መካከል አብዛኞቹ አነስተኛ ተከፋይና ቀሪዎቹም የጡረታ ጊዜያቸው የደረሱ መሆናቸውን የሚናገሩት የሠራተኞቹ ተወካዮች “ ውሳኔው ሠራተኛውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ የሚከት ነው ብለዋል። ውሳኔው የቤተሰብ መሠረትን የሚያናጋ ነው ፡፡ በወር ሁለት እና ሦስት ሺህ ብር የሚከፈለው ሠራተኛ ተመላልሶ ለመሥራት ደሞዙ የመጓጓዣ ወጪውን እንኳን አይሸፍንም ፡፡ ቤተሰብን ይዞ ለመሄድ ደግሞ የልጆች ትምህርት ቤትን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማት የሉም ፡፡ በዚህም የተነሳ ችግር ውስጥ ወድቀናል “ ብለዋል ፡፡
የዞኑ መስተዳድር ውሳኔ
ዶቼ ቬለ በሠራተኞቹ ቅሬታ ዙሪያ ያነጋገራቸው የኮሬ ዞን መስተዳድር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ ምደባው ሠራተኛው ወደ ማህበረሰቡ በመቅረብ አገልግሎት እንዲሰጥ ቀደምሲል የዞኑ ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የተፈጸመ ነው ብለዋል ፡፡ በዞን ደረጃ በሚገኙ ውስን መዋቅሮች ላይ ውድድር መደረጉን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው “ ውድድሩ የመንግሥት እና የሠራተኞች ተወካዮች በተካተቱበት ኮሚቴ አማካኝነት የተካሄደ ነው ፡፡
የዞኑ የሥራ መደብ መዋቅር ውስን በመሆኑ አብዛኛው ሠራተኛ ከመዋቅር ውጪ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ የተገመተ ጉዳይ ነው ፡፡ ነግር ግን መደቦችን ሳያገኙ የቀሩ ሠራተኞችን ወደ ወረዳ ደልድለናል ፡፡ በአጭሩ የተደረገው ይሄ ነው ፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነ ነገር የለም “ ብለዋል ፡፡
የውድድሩ ፍትሃዊነት
ሠራተኞቹ ግን ውድድር የተባለው መመዘኛ በራሱ ችግር ያለበትና አድሏዊ ነው ይላሉ ፡፡ በዞኑ ማዕከል ላይ የተመደቡት የአመራር ሚስቶችና የቅርብ ዘመዳሞች ብቻ መሆናቸውን የሚናገሩት ሠራተኞቹ “ አሁን ያለፉት ሠራተኞች እንዲያልፉ የሚፈለጉ ሰዎች ናቸው ፡፡ የውድድር ኮሚቴው አባላት መልማይም ፣ አወዳዳሪም ፣ ቅሬታ ሰሚም ራሳቸው ናቸው ፡፡ በእኛ በኩል አድሏዊ አሠራር አለ ብለን እናምናለን “ ብለዋል ፡፡
ኮሬ ዞን በልጃገረዶች ጠለፋ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ሰዎች በፖሊስ መያዛቸው
የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ ግን ሠራተኞቹ ያነሱትን ኢፍትሃዊነት አለ በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ አይቀበሉትም ፡፡ በእኛ እምነት ፍትሃዊ የሆነ ሥራ ነው የተሠራው ብለን እናምናለን ፡፡ ነገር ግን ጉድለቶች አይኖሩም ማለት አይደለም ፡፡ ሠራተኛው ቅሬታ ካለው ቅሬታውን ማቅረብና በሂደቱ ዙሪያ ማብራሪያ መጠየቅ ይችላል “ ብለዋል ፡፡
አሁን ላይ በዋና አስተዳዳሪው ምላሽ ያረኩት የዞኑ ሠራተኞች አቤቱታቸውን ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና ለፌዴራል የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ለማቅረብ ፊርማ እያሰባሰቡ እንደሚገኙ የሠራተኞቹ ተወካዮች ተናግረዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ
ፎቶ ኮሬ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን