የወባ ስርጭት በአማራ ክልል
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 25 2017በአማራ ክልል የወባ በሽታ ከምንጊዜውም በላይ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነዋሪዎችና የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል፣ ባለፉት 5 ወራት ከ1 ሚሊዮን 300ሺህ በላይ ሠዎች በበሽታው ተይዘዋል፣ ይህም ከአለፈው ተመሳሳይ ወቅት በ64% ጭማሪ እንዳለው ተነግሯል። ለበሽታው ስርጭት መስፋፋት የተለያዩ ምክንያቶች ተዘርዝረዋል፣
ወባ በደጋማ አካባቢዎችም እየተከሰት ነው
የአማራ ክልል 70% የሚሆነው አካባቢ ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ እንደሆን ባለሙያዎች ይገልፃሉ፣ በሽታው በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ መጨምሩን ነው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች የሚናገሩት።
በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዳህና ወረዳ ነዋሪ የወባ በሽታ ስርጭት ባልተለመደ ሁኔታ መጨመሩንና ለህብረተሰቡ ስጋት መሆኑን ገልጠዋል። አካባቢው ደጋማና ለወባ ስርጭት አመቺ ባይሆንም በዚህ ዓመት የታየው የወባ ህመም ግን ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
የፃግብጂ ወረዳ ነዋሪም ጤና ጣቢያዎች በብዛት በወባ ታማሚዎች መያዛቸውን ነው ያብራሩት። የወባ ታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ በሌሎች ህመሞች ለህክምና የሚመጡ ህሙማን ለመታከም ተቸግረዋል ነው ያሉት።
ሌላ አስተያያት ሰጪ በበኩላቸው በዚህ ዓመት የታየው የወባ ህመም በጣም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፣ ሁለት ለጆቻቸው በበሽታው ተይዘው በህክምና ማገገማቸውንም በስልክ ነግረውናል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ሆስፒታል አንድ የላቦራቶሪ ባልሙያ በየቅኑ በሆስፒታሉ ከሚመረመሩ ሠዎች 10% የሚሆኑት የወባ በሽታ ይገኝባቸዋል ብለዋል፣ ይህም ቀደም ሲል ከነበረው በግማሽ እንደጨመረ ገልጠዋል። ለበሽታው ስርጭት የግብዓት እጥረት፣ የፀጥታ ችግር፣ የመንገዶች መዘጋጋትና ሌሎችም እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።
እስከ 70% ሠዎች በወባ ይጠቃሉ
በሰሜን ወሎ ዞን የቡግ ና ወረዳ ጤና ጣቢያየህክምና ባለሙያ በበኩላቸው ባለፉት 5 ወራት ከተመረመሩ 8ሺህ ሠዎች በ6ሺህ ያክሉ የወባ በሽታ ተግኝቷል ነው ያሉት፣ በአማካይ ከሚመረመሩ ህሙማን መካከል 72% የሚሆኑት የወባ ታማሚዎች እንደሆኑ ገልጠዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊና የክልሉ ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ በሰጡት መግለጫ በአማራ ክልል በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሠው ሰራሽ ምክንያቶች የበሽታው ስርጭት በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል ብለዋል።
ባለፉት 5 ወራት በአማራ ክልል 1.3 ሚሊዮን በላይ ሠዎች በወባ ታመዋል
“... ከ3 ሚሊዮን በላይ ሠዎች የህክምና ምርመራ አድርገው ክ1.3 በላይ የሚሆኑት በወባ በሽታ የተያዙ ሆነው ተገኝተዋል፣ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር በ64% ጭማሪ አሳየቷል፣ ከታህሳሰ 7 እስከ ታህሳስ 14 ያለው የአንድ ሳምንት የወባ ሪፖርት የሚያሳየው120ሺህ 115 ሠዎች ተመርምረው ወደ 52 ሺህ የሚሆኑት በሽታው የተገኘባቸው ናቸው ። ለወባ በጣም ተጋላጭ ናቸው የምንላቸው የክልሉን 70% የሚሸፍኑ ናቸው፡፡” ሲሉ ገልጠዋል።
በዚህ ዓመት ለወባ ስርጭት መስፋፋት የህብርተሰቡ ቸልተኝነት፣ የሠዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ፣ ለልማት ተብለው የሚቆፈሩ ጉደጓዶች ውሀ ማቆርና ለወባ ትንኝ መራባት ምክንያት መሆን፣ የአልጋ አጎበርን በአግባቡ አለመጠቅም፣ የግብዓት እጠርትና በዋናንት ደግሞ በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ግበዓቶችን በተፈለገው ሁኔታ ለማሰራጨት እንቅፋት መሆን ተጠቃሽ እንደሆኑ አብራርተዋል።
የግብዓት እጥረቱን ከፌደራል ጤና ሚኒስቴር፣ ክሀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከክልል ጤና ቢሮ ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ መደረጉንም ጠቀሰዋል፡፡
“የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ በሽታን ይገታሉ”
“የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ በሽታን ይገታሉ” በሚል መሪ መልዕክት ከጥቅምት 15/2017 ጀምሮ በየሳምንቱ አርብ ጠዋት ጠዋት 822ሺህ ሠዎች በተሳተፉበት የፅዳት ዘመቻም ስርጭቱ ሊደርስ ከሚችልበት ከፍተኛ መዛመት መግታት መቻሉንም አመልክተዋል።
በአማራ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም አንድ የወባ መከላከል ባለሙያ የግብዓት እጥረቶች እንደነበሩ ጠቅሰው አሁን ግብዓቱ ቢሟላም በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በተፈለገው ፍጥነት ግብዓት ወደ ጤና ተቋማት ማድረስ አልተቻለም ነው ያሉት።
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ