የዋጋ ግሽበት በባለሙያዎች እና ነዋሪዎች አተያይ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 25 2017
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋጋን የማረጋጋት ቀዳሚ ዓላማ ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን እንዲሰጥ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ እስካለፈው ህዳር ወር የነበረው እአአ የ2024 የዋጋ ግሽበት በተለይምምግብ ነክ ምርቶች ላይ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበው ጋር ሲነጻጸር መረጋጋት ማሳየቱን ጠቁሟል፡፡
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ግን በዚህ የሚስማሙ አይመስልም፡፡ ከአምና አንጻር ያልጨመረ ነገር የለም ባይ ናቸው፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያም በሰጡን አስተያየት ጭማሪው በሁሉም ረገድ የተስተዋለ በመሆኑ የመንግስት ወጪን በመቀነስ ግብርናው ላይ አተኩሮ መስራት ምናልባትም የዋጋ መረጋጋቱን ሊያመጣ ይችላል ይላሉ፡፡
አስተያየታውን የሰጡን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከአምና አንጻር ከዘይት እስከ ሽንኩርት፣ከጤፍ እስከ በርካታ የምግብ ፍጆታ እቃ እና የቤት ውስጥ መገልገያዎች ያልጨመረ ነገር የለም ባይ ናቸው፡፡
ይህ የሸማቾች አስተያየት ከዋጋ ግሽበት አኳያ ለምን ከሰሞነኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ምልከታ ጋር ተለያየ በሚል አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን፤ “እኔም ሸማች ስለሆንኩ የዋጋ መጨመር ብቻ ነው ሁሌም የምሰማው” የምሉት ባለሙያው፤ ምናልባትም የኮሚቴው ግምገማ ከብር መግዛት አቅም መዳከም ጋር ታይቶ ይሆናል ብለዋል፡፡ መንግስት ወጪውን በመቀነስና የባንኮች በብድር ገንዝብ መርጨትን በጥብቅ በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠሩን ግን ባለሙያው አልሸሸጉም፡፡
ይሁንና ይህም የራሱ የሆነ ጉድለት እንዳለው በመጠቆም፤ “ግን ደግሞ እዚህ ጋ ኢኮኖሚው ማምረት በሚችለው መጠን ገንዘብ መርጨት ይኖርበታል” ያሉት ባለሙያው “መንግስት እንደ ብሔራዊ ስታትስትክስ እና ፕላን ኮሚሽን ያሉ ተቋማት ተጠቅሞ መረጃ በማሰባሰብ የገንዘብ ፖሊሲ ጥብቅ ቁጥጥርም ሳይዘነጋ ምርት ግን እንዲመረት ገንዘብ ወደ ገቢያ መርጨት” እንዳለበትም መክረዋል፡፡
የፖለቲካል ኢኮኖሚው ባለሙያ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ስራ አጥነት እና መሰል ፈተናዎች እንዳይደቀኑም ግሽበቱን በተለይም የምግብ ዋጋን ማረጋጋት በሚችሉ በግብርናው ዘርፍ ላይ በማተኮር መስራት አይነተኛ መፍትሄ ነው ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ