1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ እንዲገቡ ስለመወሰኑ የህዝብ አስተያየት

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 2 2014

አንድ አስተያየት ሰጭ «በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።የቴክኖሎጂ ሽግግር ይመጣል። ዘመናዊ የንግድ ሀሳቦች ወደ ሀገራችን ሊገቡ ይችላሉ።የሀገራችን ባንኮችም ውድድሩ በመምጣቱ አሰራራቸውን ይቀይራሉ ብዮ አስባለሁ።»ሲሉ ሌላኛው«የውጭ ባንኮች መግባታቸው በጣም የፈጠነ እርምጃ ይመስለኛል። ምክንያቱም ተወዳዳሪ ነን ወይ?»ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4GXAE
Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Solomon Muchie/DW

የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ እንዲገቡ ስለመወሰኑ የህዝብ አስተያየቶች

መንግሥት የውጭ አገራት ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ውስጥ ገብተው መሥራት እንዲችሉ የሚፈቅድ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ. ም አስታውቋል። 
ውሳኔውን በመደገፍ በተለይ የባንኮች ብድር አገልግሎት መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ያደርጋል፣ የሥራ እድሎች ይሰፋሉ በሚል ሀሳብ የሰጡ የመኖራቸውን ያህል ፣ ውሳኔው ሀገር በቀል ባንኮችን ከማቀጨጭ በተጨማሪ ለብሔራዊ ደህንነት ሥጋት ሊፈጥር ይችላል በሚል ውሳኔው ተገቢ አለመሆኑን የገለፁም አሉ።"ትልቅ ለውጥ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊያመጣ ይችላል። የቴክኖሎጂ ሽግግር ይመጣል። ዘመናዊ የንግድ ሀሳቦች ወደ ሀገራችን ሊገቡ ይችላሉ።የሀገራችን ባንኮችም ውድድሩ በመምጣቱ ያላቸውን የአሰራር ሥርዓት ቀይረው ተደራሽ ይሆናሉ ብየ አስባለሁ።" 
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ "አሁን ላይ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው በጣም የቸኮለ ወይም በጣም የፈጠነ እርምጃ ይመስለኛል። ምክንያቱም ተወዳዳሪ ነን ወይ?" ? በማለት ይጠይቃሉ።"ብድር በቀላሉ ሊሰጡና ተደራሽ ሊያደርጉ ይችላሉ። ግን ተያዥ የሚያደርጉት ነገር አለ። ለምሳሌ መሬትን መያዣ ቢያደርጉ እና እኔ መክፈል ቢያቅተኝ መሬቱን ነው የሚወስዱት። ይህ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስከበር አንፃር እንዴት ነው የሚታየው የሚለው ነገር በደንብ የተመረመራ አይመስለኝም። ብዙ ነገሩ የይድረስ ይድረስ ይመስላል" ብለዋል። እኚህ ደግሞ "ውሳኔውን ስሰማ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ደስ ብሎኛል። ምክንያቱም እኔ ተቀጥሬ ነው የምሰራው። ደሞዝተኛ ነኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮችን ስናነሳ የብድር አስጣጥ ሂደታቸው ለተቀጣሪ ወይም የመንግሥት ሰራተኛ ለሆኑት በተለይ ትንሽ ከበድ ያለ ነገር ይኖረዋል። አሁን እነሱ ሲመጡ ግን ምናልባትም ይሄን ነገር ያቀሉታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
በደሞዛችን ቤት፣ መኪና ለመግዛት ሌሎች ብድሮችንም ለማግኘት ይጠቅሙናል ብለን እናስባለን" በማለት ተስፋቸውን ገልፀዋል። "ተስፋም ስጋትም አለኝ" ይላሉ ሌላኛው ያነጋገርናቸው ሰው። "ተስፋዬ ምንድን ነው፣ የእኛ አገር ባንክ በየ ዓመቱ በጣም ብዙ በመቶ ሚሊዮኖች ነው የሚያተርፉት።  አንዳንዶቹ ቢሊየንም ይገባሉ።
ስታየው ይሄ በጣም የተጋነነ ነው። ባንኮች በብዛት ያገለግሉ የነበረው ላለው ሰው ነው። መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት ሲሰጡ አላይም። ይህ ውሳኔ የውጭ ባንኮች ተጨማሪ ተወዳዳሪ ስለሚሆኑባቸው ይህንን መካከለኛ እና ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያለውን ማህበረሰብ ዋነኛ ደንበኞቻቸው አድርገው ሊመጡ ይችላሉ።" ብለዋል።ሆኖም ግን "የሀገር ውስጥ ሀብትን ሊቀራመቱ ይችላሉ፣ መንግሥት የውጭ ባንኮችን ሊቆጣጠር ላይችል ይችላል፣ እጅ መጠምዘዝ ሊመጣ ይችላል የሚል ሥጋት ይኖርብኛል" በማለት የሚታያቸውን ሥጋት ተናግረዋል።

ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ