1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታህሳስ 27 ቀን 2017 የዓለም ዜና

Yohannes Gebreegziabherእሑድ፣ ታኅሣሥ 27 2017

የሱዳን የሰላም ተስፋ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ጥቃት በአለፉት 24 ሰዓታት 88 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ዩክሬይን የሩስያ ግዛት በሆነችው የክርሱክ ግዛት ዛሬ መጠነሰፊ የመልሶ ማጥቃት ማካሄዷን

https://p.dw.com/p/4oqAu

የሱዳን የሰላም ተስፋ

የሱዳኑ ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕረዚደንት ጀነራል ዓብዱልፋታህ አልቡርሃን ቱርክ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የጀመረችውን ጥረት አንደሚደግፉ የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። አልቡርሃን በቱርክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራውን የልዑካን ቡድን በፖርት ሱዳን ተቀብለው አነጋግረዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በታህሳስ 2024 የቱርኩ ፕሬዚደንን ረሲብ ጠይብ ኤርዶጋን ከሱዳኑ ጀነራል አብደፋታሕ አልቡርሃን በስልክ ባካሄዱት ውይይት ሃገራቸው 20 ወራትን ያስቆጠረውን ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት አብቅቶ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልጸውላቸው ነበረ። በዚሁም መሰረት በምክትል የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡርሃንቲ ዱራን የተመራው ልኡክ ከጀነራሉ መወያየቱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። 
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓሊ ዩሱፍ ሰይድ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች፤ የቱርኩ ፕረዚደንት የሰላም ጥረት «በሱዳን ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር በር ከፋች ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።
በሱዳኑ ሉአላዊ የሽግግር ፕረዚደንት ጀነራል ዓብደልፋታህ አልቡርሃንና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መሪ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል በተነሳ ጦርነት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ሲገደሉና ሲቆስሎ፤ ሚልዮኖች ደግሞ መፈናቀላቸውን አልያም አገር ጥለው መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣው መረጃ ያመላክታል።

እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ጥቃት በአለፉት 24 ሰዓታት 88 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን

እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ጥቃት በአለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 88 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ። እስራኤል በበኩሏ በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎችን መግደሏን አስታውቃለች።
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ ከሞቱት ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶችና ሕጻናት ናቸው ብሏል። በጃባሊኢና ናዛሪያ በተፈጸሙ ጥቃቶች በቤታቸው ውስጥ የነበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውንም ታውቋል። የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አክሎም 15 ወራትን ባስቆጠረው የእስራኤል ሀማስ ጦርነት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 45,805 ደርሷል ብሏል። የዜናው ምንጭ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።
የእስራኤል የመከላከያ ሰራዊት ያሰራጨውን ዘገባ ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ደግሞ እስራኤል በሳምንቱ ማገባደጃ በተለያዩ የጋዛ አካባቢዎች የሚገኙ ከ100 በላይ የሐማስ ወታደራዊ ዒላማዎችን መመታቷን አስታውቃለች። 
በጥቃቱ በደርዘን የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎች መገደላቸውንም በመግለጫው ተጠቅሰዋል። ሐማስ በአጎራባች የእስራኤል ከተሞች ላይ ጥቃት ይፈጽምባቸው ነበር ያለቻቸውን የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ ተቋማትን ማውደሟንም አክላለች።

ዩክሬይን የሩስያ ግዛት በሆነችው የክርሱክ ግዛት ዛሬ መጠነሰፊ የመልሶ ማጥቃት ማካሄዷን

ዩክሬይን የሩስያ ግዛት በሆነችው የክርሱክ ግዛት ዛሬ መጠነሰፊ የመልሶ ማጥቃት ማካሄዷን የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። ዩክሬይን በበኩሏ «ሩስያ የእጇን አግኝታለች» ብላለች።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ያሰራጨውን መግለጫን ጠቅሶ አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው፤ የዩክሬይን ጦር ዛሬ ድንገተኛ የመልሶ ማጥቃት ጦርነት አድርጓል። የሩስያ ወታደሮች ጥቃቱን መመከታቸውን በማከል።
የዩክሬይን ፕረዚደንት ፅሕፈት ቤት ሃላፊ አንድሬይ ያርማክ በቴሌግራም ገጻቸው የጻፉትን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA እንደዘገበው ደግሞ፤ ዩክሬይን በክርሱክ ግዛት መጠነ ሰፊ ማጥቃት መፈጸሟን አረጋግጠዋል። ሃላፊው « ሩስያ የእጇን እያገኘች ነው» ሲሉ ቢጽፉም ተመዘገበ ስለተባለው ድል የገለጹት ነገር የለም።
በትላንትናው ዕለትም ዩክሬን ከአሜሪካ ያገኘውን ሚሳይሎችን በመጠቀም  የቤልጎሮድ ግዛት ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን፤ ጥቃቱ በሩስያ ሃይሎች መክሸፉንም ታውቋል። ለጥቃቱ አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥም ሩስያ መዛቷ ይታወሳል።

 በጀርመን በበረዶ ምክንያት 120 በረራዎች መሰረዛቸውን

 በጀርመን የፍራንክ ፈርት ከተማን ጨምሮ በአብዛኞቹ ደቡባዊ ግዛቶች  ዛሬ በጣለው በረዷማ ዝናብ 120 በረራዎች መሰረዛቸውን የአውሮፕላን ማረፊያው ባለስልጣናት አስታወቁ። በታላቋ ብሪታንያም በረራዎች ተስተጓጉለዋል፤ መንገዶችም ተዘግተዋል ነው የተባለው።
የፍራንክፈርት አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቃል አቀባይ ለጀርመን ዜና አገልግሎት እንዳሉት የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ ሜዳው በበረዶ ተሸፍኗል። የአየር ጠባዩም ለበረራ አዳጋች አድርጎታልም ብለዋል። በመሆኑም ዛሬ በአውሮፕላን ማረፊያው ያርፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ከ1,000 በላይ በረራዎች ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 120ው ተሰርዘዋል።
በታላቋ ብሪታንያ በሚገኙ በርካታ ከተሞችም በተመሳሳይ ችግር በረራዎች ተስተጓጉለዋል፤ የኤሌክትሪክ መቋረጥም አጋጥሟል ሲል የዘገበው ደግሞ አሶሽየትድ ፕረስ ነው።
በናጋሳኪ ከአቶሚክ ቦምብ ጥቃት በሕይወት የተረፉት ጃፓናዊ በ93 ዓመታቸው አረፉ።

አሜሪካ በጃፓኗ ናጋሳኪ ከተማ  እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1945 ከጣለችው አቶሚክ ቦምብ በሕይወት የተረፉትና ዕድሜ ልካቸው ሰላምን ሲሰብኩ የነበሩት ጃፓናዊ በ93 ዓመታቸው አረፉ።
ሺሚ ፉካሃሪ አሜሪካ ናጋሳኪን በአቶሚክ ቦምብ ስትደበድብ ገና የ14 ዓመት አዳጊ ነበሩ። በድብደባው ቤተሰባቸው በሙሉ አልቀዋል። እንደ እድል የተረፉት እኚህ አዛውንት በጃፓን የሰላም ተምሳሌት ተደርገው ይወሰዱ እንደነበርም አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀናቸው

በጎርጎሮሳውያኑ 2025 በመጀመሪያው የሺያሚን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌሎች ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር በወንዶችም በሴቶችም ድል ቀንቷቸዋል።
በሴቶች ምድብ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ማንንም ሳይያስገቡ አሸንፈዋል። አትሌት ሩቲ አጋ ሶራ 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ46 ሰኮንድ በሆነ ሰዓት የስፍራውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ውድድሩን በአንደኝነት አሸንፋለች። አትሌት ጉተሜ ሾኔ 2ኛ፤ አትሌት ፍቅርተ ወረታ 3ኛ በመሆን ውድድሩን አሸንፈዋል።
በወንዶች ምድብ አትሌት ዳዊት ወልዴ 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ፤ ከ06 ሰኮንድ በመግባት ቀደም ሲል የተያዘውን ክብረወሰን  በመስበር የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆኗል። አትሌት አሰፋ ቦኪ በውድድሩ 3ኛ ደረጃን ይዟል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።