አንጋፋው ፖለቲከኛና የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ቡልቻ ደመቅሳ አረፉ
አንጋፋው ፖለቲከኛና የምጣኔ ሐብት ባለሙያ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
አቶ ቡልቻ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ በርመጂ ወረዳ በ1923 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊምቢ አድቬንቲስት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ አድቬንቲስት ተምረዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እና በሕግ ዲግሪዎች ተመርቀዋል። በወቅቱም በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከተመረቁ 10 ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ወደ አሜሪካ በመሄድ በሲራኪዩዝ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን ለአስር ዓመታት ያህል የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። በ1966 አብዮቱ ሲፈነዳ ተመልሰው ወደ ውጭ አገር መመለሳቸውን ይታወቃል። አንጋፋው ፖለቲከኛና የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በሙያቸው የዓለም ባንክ የአፍሪካ ተወካይ በመሆንም አገልግለዋል። የአዋሽ ባንክ መስራችም ነበሩ። አቶ ቡልቻ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና አዋሽ ባንክ ሽልማት አበርክተውላቸዋል።
በፖለቲካው ዘርፍም የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን በመመስረት በሊቀመንበርነት ያገለገሉ ሲሆን በ1997 በተካሄደ ምርጫ አሸንፈው በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለ5 ዓመታት አገልግለዋል። በምክርቤት አባልነታቸው ሙያዊ እውቀታቸውን በመጠቀም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጠንካራ ሞጋች እንደነበሩ ይታወቃል። አቶ ቡልቻ ባለትዳርና የ6 ልጆች አባት ነበሩ።
በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሕልፈት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞችና ባለስልጣናት ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።
በሱዳን በአየር ድብደባ 10 ሞቱ ከ30 በላይ ቆሰሉ
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ደቡባዊ ክፍል ዛሬ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 10 ሰዎች ሲሞቱ ከ30 በላይ መቁሰላቸውን በአካባቢው የሚገኙ ምግባረሰናይ ድርጅቶች አስታወቁ። የአየር ድብደባው የተፈጸመው በሱዳን ሉአላዊ የሽግግር መንግስት ምክርቤት ጦር ነው ተብሏል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በገበያ ቦታ ላይ ሲሆን እንዲህ አይነት ጥቃት ሲፈጸም በአንድ ወር ውስጥ ይህ ለ3ኛ ጊዜ ነው።
በሱዳን በሁለቱም ጀነራሎች በተቀሰቀሰው ጦርነት በዋና ከተማዋ ካርቱም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከሚያዝያ 2023 እስከ ሰኔ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ 26,000 ሱዳናውያን መገደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሱዳኑ ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕረዚደንት ጀነራል ዓብዱልፋታህ አልቡርሃን ትላንት በቱርክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራውን የልዑካን ቡድን በፖርት ሱዳን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት የቱርክን የሰላም ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸው ነበረ።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓሊ ዩሱፍ ሰይድ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች፤ የቱርኩ ፕረዚደንት የሰላም ጥረት «በሱዳን ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር በር ከፋች ነው» ማለታቸውን ይታወሳል።
የኡጋንዳው ጦር መሪ ማወዛገባቸውን ቀጥለዋል
የኡጋንዳው ፕረዚደንት ዩዌሪ ሙሰቤኒ ልጅና የሐገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ የሐገሪቱ ዋና ተቀናቃኝ ፓርቲ መሪ የሆኑትን አንገት እቀላለሁ ሲሉ ዛቱ። እኒህ በየጊዜው በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን በሚለቋቸው አወዛጋቢ መልዕክቶች የሚታወቁት የጦር አዛዥ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑትን ቦቢ ዋይንን አንገት እንዳይቀሉ የተከላከሉላቸው አባታቸው ዩዌሪ ሙሴቬኒ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኡጋንዳ ጦር አዛዥ የሆኑት ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት «በመካከላችን አባቴ ባይኖር ኑሮ የቦቢ ዋይንን አንገት እቆርጠው ነበር» ብለዋል። ቦቢ በበኩላቸው ዛቻውን በቀላሉ እንደማይመለከቱት ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በርካታ ዛቻዎች እንደደረሱባቸው በማከል። ጀነራሉ ለዚሁ በሰጡት የመልስ መልስ «አንገትህን ከመቁረጤ በፊት የተበደርከንን ገንዘብ መልስ» የሚል እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
እኒሁ ጀነራል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2022 ጦራቸው ኬንያን በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሊቆጣጠራት እንደሚችል ገልጸው ሲያወዛግቡ የነበረ ሲሆን፤ በዚያው አመት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ለጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የላግባሽ ጥያቄ አቅርበው ነበረ፤ 100 ከብቶች በጥሎሽ እንደሚሰጧቸው በማከል።
የሃገሪቱ መንግስት፤ መሰል አስተያየቶች የጀነራሉ የግል እንጂ የመንግስት አቋሞች እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ቢያስተባብልም ለሃገሪቱ ዲፕሎማሲና የገጽታ ግንባታ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ የሃገሪቱ ልሂቃን ይተቻሉ።
በጀርመን የሚኖሩ የሶሪያ ስደተኞች ዕጣፈንታ
የሶሪያ ስደተኞች በጀርመን መቆየት ከፈለጉ ሥራ መስራት እንዳለባቸው የጀርመን ምክትል መራሔ መንግስት አሳሰቡ። ሮበርት ሃቤክ እንዳሉት ሥራ የማይሰሩ ከሆነ ግን በግድ ወደ ሐገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።
የበሽር አልአሳድ መንግስት መውደቅን ተከትሎ በጀርመን የሚገኙ የሶሪያ ስደተኞች ወደ ሐገራቸው ይመለሱ የሚለው ጉዳይ በጀርመን ፖለቲከኞች ዘንድ ከፍተኛ የመከራከሪያ ነጥብ ሆኖ እንደቀጠለ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ቀደም የቀኝ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች «በሶሪያ መንግስት በመቀየሩ በተለይ የማሕበራዊ ዋስትና የሚከፈላቸውና ሥራ የማይሰሩ ሶሪያውያን ሐገራችንን ለቀው ይውጡልን » ሲሉ ተደምጠዋል።
የጀርመን ምክትል መራሔ መንግስት ሮበርት ሃቤክም ይህንኑ ሐሳብ ያጠናከሩ ይመስላል። እሳቸው ዛሬ «ዶችላንድፉንክ» ለተባለ ራድዮ ጣቢያ በሰጡት ቃለምልልስ «አገራቸው ሰላም እስከሆነ ድረስ እዚህ ሥራ የማይሰሩት ተገደውም ቢሆን ወደ ሐገራቸው መመለስ አለባቸው» ሲሉ ተደምጠዋል።
በሶሪያ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2015 የእርስ በእርስ ጦርነት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በጀርመን 975,000 ሶሪያውያን እንደሚኖሩ የጀርመን የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ከነዚህ ከ300,000 በላይ የሚሆኑት የማሕበራዊ ዋስትና ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆናቸውን የዘገበው የጀርመን ዜና አገልግሎት (DPA)ነው።
«ሩስያ ጥፋተኛ ነች» አዘርባጃን
በአለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ የተከሰከሰው የአዘርባጃን አውሮፕላን ተጠያቂዋ ሩስያ ነች ሲሉ የሐገሪቱ ፕረዚደንት አስታወቁ። የፕረዚደንቱ ፅሕፈት ቤት ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ የመጀመሪያ ደረጃ የማጣራት ሂደቱ አውሮፕላኑ በሩስያ አየር መቃወሚያ ተመትቶ መከስከሱን አመላክቷል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ታሕሳስ 25 ቀን 2024 ከአዘርባጃን ባማኮ ከተማ ወደ ሩስያዋ ግሮዥኒ ሲጓዝ የነበረው አውሮፕላን በካዛኪስታኗ የአክታው ከተማ በመከስከሱ ተሳፍረው ከነበሩት 67 ተጓዦች 38ቱ መሞታቸው ይታወሳል።
አውሮፕላኑ በካዛኪስታን ከመከስከሱ በፊት በሩስያ የአየር ክልል እክል እንዳጋጠመው የገለጹት የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ይቅርታ ጠይቀው ነበረ። ይሁንና በሩስያ የአየር መቃወሚያ ተመትቶ ስለመውደቁ ግን ያሉት ነገር አልነበረም።
የአዘርባጃን ፕረዚደንት ኢልሃም አሊዬቭ ለዚህ አደጋ ሩስያ ጥፋተኛ መሆኗን በመግለጽ ይቅርታ እንድትጠይቅና አጥፊዎችን ተጠያቂ እንድታደርግ መጠየቃቸውን የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።
ሩስያ በምስራቅ የዩክሬይን ግዛት የምትገኘውን የኩራኮቭ መንደርን መቆጣጠሯን
ሩስያ በምስራቅ የዩክሬይን ግዛት የምትገኘውን የኩራኮቭ መንደርን መቆጣጠሯን አስታወቀች። መንደሯ የዩክሬይን የስንቅና ትጥቅ ማዕከል እንደነበረችም አስታውቃለች። በሌላ ዜና የዩክሬይኑ ፕሬዚደንት ቭሎደሚር ዘለንስኪ ሐገራቸው ለሰላም ጉጉት እንዳላት ገልጸዋል።
የሩስያ ጦር ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ፤ ኩራኮቭ የተባለችው መንደር የውስጥ ለውስጥ መገናኛ ስርዓት የተዘረጋላትና የምስራቅ ዩክሬይን ግንባር የስንቅና ትጥቅ ማዕከል እንደነበረች አትቷል። የመንደሯ መያዝ ቀሪው የዶኔስክ ግዛትን ለመያዝ እንደ መንደርደሪያ የምታገለግል ቁልፍ ወታደራዊ ጠቀሜታ እንዳላትም አክሏል።
በሌላ ዜና የዩክሬይኑ ፕሬዚደን ቮለደሚር ዘለንስኪ አጋሮቻቸው የሆኑ አገራት ለሐገራቸው ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ ሥርአት እገዛ እንዲያደርጉ ጠየቁ። ፕረዚደንቱ የፊታችን ሐሙስ ጀርመን ባዘጋጀችውና የተለያዩ ሐገራት በሚሳተፉበትና በዩክሬይን ጉዳይ በሚመክረው ስብሰባ ቅድሚያ ሰጥተው የሚጠይቁት ይህንኑ የአየር መቃወሚያ ስርዓት ድጋፍ መሆኑን አስታውቀዋል። ሀገራቸው ለሰላም ከፍተኛ ጉጉት እንዳላት በማከል።
"በየሳምንቱ አዲስ ውጤት ያስፈልገናል ። እርግጥ ነው ፣ በዚህ ዓመት ብዙ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የሚኖር ሲሆን ዩክሬንም ለሰላም ከፍተኛ ጉጉት አላት ። የሚያስፈልገን ዓይነት እውነተኛ ዲፕሎማሲ የተመሠረተው ጠንካራ በሆኑት ነጥቦች ላይ ብቻ ነው ። ዩክሬንን የሚያበረታቱትን ሁሉ አመሰግናለሁ! ክብር ለዩክሬን ይሁን!”
በሌላ ዜና ዩክሬይን ሌሊት ለዛሬ አጥቢያ ሩስያ ለጥቃት ካሰማራቻቸው 128 ድሮኖች 79ኙ መትታ መጣሏን አስታውቃለች። 49 ድሮኖችና 2 ክሩዝ ሚሳይሎችን ደግሞ ዒላማቸውን ከመምታት እንዳከሸፈች በማከል።
በትላንትናው ዕለት ዩክሬይን፤ የሩስያ ግዛት በሆነችው የክርሱክ ግዛት መጠነሰፊ የመልሶ ማጥቃት ማካሄዷን የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበረ። ዩክሬይን በበኩሏ ጥቃቱ መፈጸሟን በማመን «ሩስያ የእጇን አግኝታለች» ማለቷን ይታወሳል።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ