1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫ ዘመቻ በጀርመን

ኂሩት መለሰ
ማክሰኞ፣ ጥር 13 2017

በምርጫ ዘመቻው ሂደት አማራጭ ለጀርመን ወይም በጀርመንኛ ምህጻሩ AFD ካልርስሩኽ በተባለው የጀርመን ከተማ የበተነው የአውሮፕላን ቲኬት እንዲመስል ተደርጎ የተሰራው በራሪ ወረቀት ሕገ ወጥ ያላቸው ፈልስያን ጀርመንን ለቀው ወደመጡበት እንዲመለሱ ያዛል ። በራሪ ወረቀቱ ጥላቻን የሚቀሰቅስ መሆን አለመሆኑን የጀርመን ፖሊስ እየመረመረ ነው ።

https://p.dw.com/p/4pRWh
Deutschland Berlin 2025 | SPD kürt Scholz erneut zum Kanzlerkandidaten für Bundestagswahl
ምስል JOHN MACDOUGALL/AFP

የምርጫ ዘመቻ በጀርመን

21 ኛው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ በቀደመው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለጎርጎሮሳዊው መስከረም 28 ቀን 2025 ዓም ነበር የታቀደው። ይሁንና የጀርመን ጥምር መንግሥት ባጎርጎሮሳዊው ህዳር 2024 ዓ.ም. በመፍረሱ ምክንያት በጎርጎሮሳዊው የካቲት 23 ቀን 2025 ዓም አዲስ ምርጫ ተጠርቷል። በዚሁ ከአምስት ሳምንት ባነሰ ጊዜ በሚካሄደው ምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አሁን በምርጫ ዘመቻ ተጠምደዋል። ፓርቲዎቹን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎችን ፎቶግራፎችና መልዕክቶች የያዙ ፖስተሮችም ህዝብ በግልጽ ሊያያቸው በሚችል ስፍራዎች ከተሰቀሉ ሳምንታት አልፈዋል። የምርጫው ዝግጅትና የምርጫ ዘመቻው ሂደትም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ትኩረትም ነው። ፓርቲዎቹ የምርጫ ዘመቻቸውን የሚቃኙትም ከነባራዊው ሁኔታ በመነሳት የህዝቡን ቀልብ ለሚስቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ነው። በቅርቡ በተደረገ ጥናት በአሁኑ ምርጫ የህዝቡን ቀልብ የሳቡት ዋነኛዎቹ ጉዳዮች ፍልሰትና የተዳከመው የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ናቸው። ተወዳዳሪዎቹ ፓርቲዎቹም በምርጫ ዘመቻቸው በእነዚህንና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አትኩረው የምርጫ ቅስቀሳቸውን በማካሄድ ላይ እንደሆኑ የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። 

የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ እጩ ፍሪድሪሽ ሜርዝ
የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ እጩ ፍሪድሪሽ ሜርዝምስል Fabian Steffens/Eibner-Pressefoto/picture alliance


በቅርቡ በተካሄዱ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች መሠረት እህትማማቾቹ የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች በጀርመንኛ ምኅፃራቸው CDU እና CSU በህዝብ ድጋፍ የመጀመሪያውን ደረጃ ሲይዙ አማራጭ ለጀርመን በጀርመንኛ ምህጻሩ AFD የተባለው ፓርቲ ደግሞ ሁለተኛው ቦታ ላይ ይገኛል ። የከዚህ በፊቱ ምርጫ አሸናፊ የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ SPD ደግሞ 3ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ሶሻል ዴሞክራቱ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከአንድ ወር በኋላ በሚካሄደው ምርጫ SPDን  ወክለው ለእጩ መራኄ መንግሥትነት ይወዳደራሉ።

ምንም እንኳን ሾልዝ ድጋሚ የመመረጥ እድላቸው አነስተኛ ነው የሚል ግምት ቢኖርም እርሳቸው በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት እንዳሉት ግን ልምድ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ጊዜውም በአሁኑ ምርጫ የማሸነፍ እድላቸው ከፍተኛ ነው የተባሉት የእህትማማቾቹ ፓርቲዎች አይደለም ብለዋል።  
«የሚቀጥሉት አራት ዓመታት ወሳኝ ናቸው። አሁን የሚያስፈልገን ግልጽነት ነው። የሚያስፈልገን መረጋጋት ነው። ሀገራችን ይህን አስቸጋሪ ወቅት እንድትወጣ ልምድ ያስፈልገናል። በሌላ አባባል አሁን ጊዜው ብዙ ንግግር ማድረጊያ አይደለም። ጊዜውም ያረጁ ያፈጁ ሃሳቦች መተግበሪያ አይደለም። ጊዜው ተራው ህዝብን የፖለቲካ መጠቀሚያ  ማድረጊያም አይደለም። በአጭሩ ለማስቀመጥ አሁን በጀርመን ጊዜው የCDU CSU አይደለም። »

የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እጬ ሮበርት ሀቤክ
የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እጬ ሮበርት ሀቤክ ምስል DW

በምርጫ ዘመቻው ሂደት አማራጭ ለጀርመን ወይም በጀርመንኛ ምህጻሩ AFD የተባለው ፓርቲ ባለፈው ሰሞን ካልርስሩኽ በተባለው  የጀርመን ከተማ የበተነው የምርጫ ቅስቀሳ በራሪ ወረቀት ማነጋገሩ ቀጥሏል።  ይኽው የአውሮፕላን ቲኬት እንዲመስል ተደርጎ የተሰራው በራሪ ወረቀት ሕገ ወጥ ያላቸው ፈልስያን ጀርመንን ለቀው ወደመጡበት እንዲመለሱ ያዛል። ቀደም ባሉ ዘገባዎች ማስታወቂያው መሠረታቸው የውጭ የሆኑ ዜጎችን የሚመለከት ተደርጎ ነበር የተገለጸው ። በጀርመን ፓርላማ የፓርቲው ተወካይ ማርክ ቤርንሀርድ ዘገባውን የተዛባ ሲሉ አስተባብለዋል። 
«በበራሪው ወረቀት ላይ የተጻፈው  ሕገ ወጥ ፈላስያን ነው የሚለው። ፍልሰተኞችን በአጠቃላይ የሚመለከት አይደለም ይልቁንም ስለ ሕገ ወጥ ስደተኞች ነው። የምንናገረው በሀገሪቱ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ስለታዘዙ ቁጥራቸው ወደ 300 ሺህ ስለሚደርስ ሰዎች ነው የምንናገረው» 
ያም ሆኖ መጤ ጠል የሚባለው የዚህ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በራሪ ወረቀት ጥላቻን ከመቀስቀስ ጋር መያያዝ አለመያያዙን የጀርመን ፖሊስ እየመረመረ ነው።

ቱጃሩ ኤሎን መስክና የAFD እጩ መራኄ መንግስት አሊስ ቫይድል
ቱጃሩ ኤሎን መስክና የAFD እጩ መራኄ መንግስት አሊስ ቫይድልምስል Patrick Pleul/Sebastian Willnow/dpa/picture alliance

ከዚሁ ፓርቲ ሳንርቅ በአሁኑ ምርጫ የውጭ ጣልቃ-ገብነት መከሰቱ ሲያነጋግር ከርሟል። በዚህ ረገድ አወዛጋቢው አሜሪካዊው ቱጃር ኤሎን ማስክ በተለይ ለጀርመን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ AFD ድጋፋቸውን መግለፃቸው ከፓርቲው እጩ አሊስ ቫይድል ጋር በኤክስ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴም ሃሳብ መለዋወጣቸው የጀርመን ፖለቲከኞችን አስቆጥቷል። መራኄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ፣መስክ በጀርመን የምርጫ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሲሉ ተቃውመዋል። 

ከአንድ ወር በኋላ የሚካሄደው የጀርመን ምርጫ ውጤት  ምን ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ ግምቶች መሰጠታቸው ግምቶች እየተሰጡ ነው። በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች በሚሰጡት ደረጃዎች መሠረት እህትማማቾቹ CDU እና CSU ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አላቸው ።ይህ ማለት ግን ፓርቲዎቹ ምርጫውን በእርግጠኝነት ያሸንፋሉ ማለት እንዳይደለ ዶክተር ለማ ተናግረዋል። ውጤቱን ዶክተር ለማ እንዳሉት አበርን የምናየው ይሆናል።


ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ