በ100 ዓመታቸው አረፉ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 21 2017
የአሜሪካው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በ 100 አመታቸው በትላንትናው እለት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። አሜሪካንን ለአንድ የፕሬዝዳንት ስልጣን ዘመን የመሯት ፕሬዝዳንት ካርተር በተለይ የግብጽና እስራኤልን የሰላም ስምምነት በማሳካት ይታወሳሉ። «የወተር ጌትን ቅሌትን» ተከትለው ስልጣን የያዙት ጂሚ ካርተር ፈተናዎችና ቀውሶችንም አስተናግደዋል። ከስልጣን ከወረዱ በኋላም በካርተር ማዕከል በኩል በርካታ አለማቀፍ ግብረሰናይ ተግባራትን ሲከውኑ ቆይተዋል። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካና አለም አንድ ታላቅ ሰው አጡ ብለዋል።
ከግብርና ወደ ፖለቲካ
ጄምስ ኧርል ካርተር ጥቅምት 1 ቀን 1924 ዓ/ም እኤአ ነው የተወለዱት ። አባታቸው የእርሻ ቁሳቁሶች አቅራቢ ሲሆኑ እናታቸው ነርስ ነበሩ። ገና በወጣትነታቸው የአሜሪካ የባሕር ኃይል አካዳሚን ተቀላቅለው እንደተመረቁ በ1946 ዓ/ም ሮዛሊን ስሚዝን አግብተዋል ። በባህር ሃይል አባልነታቸው ከጦር መርከቦች እስከ ኑክሌር ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ላይ አገልግለዋል። ይሁን እንጂ አባታቸው በ1953 ዓ/ም ሲሞቱ ከወታደራዊ አገልግሎት ወጥተው ወደ ጆርጂያ ግዛት በመመለስ ለቀጣዮቹ ሁለት አሥርተ ዓመታት የቤተሰባቸውን የኦቾሎኒ እርሻ በማስተዳደር በገበሬነት ኖረዋል። ቀስ በቀስም ከገበሬነት ወደ ፖለቲካው አለም ተቀላቅለው በ1970 ዓ/ም የጆርጅያ ግዛት ገዢ ሆነው ተመርጠዋል።
ከዛም፣ ማንም የማያውቃቸው፣ ገበሬው፣ ወግ አጥባቂ የወንጌላዊ እምነት ተከታዩ ጂሚ ካርተር በ1976 ዓ/ም ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል።
ጂሚ ካርተር «የወተርጌት ቅሌት» ህግ ጥሰትና መሸፋፈን ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ስልጣናቸውን እንዲለቁ ባስገደዳቸው 2 አመት ውስጥ ነው ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት። የእምነት ሰውነታቸው፣ ግልጽነታቸውና ከዋሽንግተን ውጪ የመጡ መሆናቸው በወቅቱ በቅሌት ፖለቲካ የተበረዘውን የዋሽንግተን አየር የሚያጠራ አዲስ እስትንፋስ እንደሆነ ተቆጥሮም ነበር።
እናም አዲስ ተስፋን የሰነቁት፣ ጂሚ ካርተር የአሜሪካ 39ኛው ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡና በ1977ዓ/ም ወደ «ኋይት ሃውስ» ገቡ።
በወቅቱ በዋሽንግተን የሚኖሩ ዘልማዳዊ ፖለቲከኞች ጂሚ ካርተርን ማየታቸው ብዙም አላስደሰታቸውም። ሰበብ አስባብ እየፈለጉም የካርተርን የአስተዳደር ዘዬና ብቃት ይተቹ ገቡ። እሳቸው ግን ይሄንኑ ፈተና ያልፉ ዘንድ ሁሉን ነገር በዝርዝር በማጥናት፣ ራሳቸው ሃገራዊ ጉዳዮችን በቀጥታ በመምራት እና በቂ ግንዛቤን በመያዝ የፖለቲካ መሰናክል ያስቀመጡባቸውን ዋሽንግተናውያን ለመርታት ጥረታቸውን ቀጠሉ።
ይሄው የአመራር ዘያቸው በግብፅና በእስራኤል መካከል ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን ጦርነትና ፍጥጫ ያስቆመውን ፣ «የካምፕ ዴቪዱን » የሰላም ስምምነት እንዲያሳኩ አግዟቸዋል። ይሄው ስኬታቸው እስከ አሁንም አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅላይ ያስመዘገበችው ተጨባጭ ውጤት ተብሎ በታሪክ ተመዝግቧል።
ከገጠሙአቸው ፈተናዎች
የካርተር ፈተና የጀመረው በ1979 ዓ/ም መገባደጃ ላይ ኢራናውያን ታጣቂወች በርካታ አሜሪካውያንን በቴህራን ካገቱ በኋላ ነበር። እነዚሁ ታጋቾች ለ444 ቀናት የታሰሩ ሲሆን በተለይ ስምንት አሜሪካውያን የሞቱበት በፕሬዝዳት ካርተር ትዕዛዝ የተሞከረው ያልተሳካ ታጋቾችን የማስለቀቅ ሙከራ የካርተር የስልጣን ዘመን ታላቁ ጠባሳ ሆኖ አልፏል።
ሌላው የካርተር ፈተና በወቅቱ የነዳጅ ና የቤንዚን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ሁሉም አሜሪካውያን ለኑሮ ውድነት መጋለጣቸው ነበር።
በዚሁ የኢራን ቀውስ እና የኑሮ ውድነት ሃገሪቷን ባስጨነቀ፣ ባስጠበበት፣ በ1980 ዓ/ም ነው ካርተር ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን፣ ከሪፑብሊካኑ ተፎካካሪያቸው ሮናልድ ሬገን ጋር የተፋጠጡት ። ሮናልድ ሬገን በወቅቱ የምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት የጠየቁት አንድ ጥያቄ፣ “ህይወት፣ ኑሮዋችሁ፣ ከአራት አመት በፊተ ከነበረው ተሽሏል ወይ” የሚል ቀላልና ቀጥተኛ ጥያቄ ነበር።
መልሱም ቀላል ነበርና፣ ጂሚ ካርተር ለሁለተኛ የፕሬዝደንትነት ዘመን ለመምራት የሚያስችላቸውን ምርጫ በሮናልድ ሬገን ተሽንፈው አጡት።
ምግባረ ሰናይ
እምነት፣ ተስፋ፣ ጥረታቸው በምርጫ ሽንፈቱ አልቆመም። ከባለቤታቸው ከሮዛሊን ጋር የካርተርን ማዕከልን በማቋቋም በመላው አለም ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት እና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ይሰፍን ዘንድ ሰርተዋል። የተለያዩ ሃገራትን ምርጫዎች ፍትሃዊነትን ታዝበዋል። በአሜሪካውያን ዘንድ ወደ የተገለሉት እንደ ሰሜን ኮሪያ እና ኩባ የመሳሰሉ ሃገራት ተጉዘዋል። የሃማስን መሪዎች ጨምሮ በአሜሪካ አሸባሪ ተብለው ከተሰየሙ ቡድኖችና ግለሰቦችም ጋ ተወያይተዋል።
በ2002 ዓ/ምም ጂሚ ካርተር አለማቀፍ መሪና መልካም ዜጋ በመሆን ላበረከቱት አስደናቂ አስተዋጽኦ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ጂሚ ካርተር በዚህ አላበቁም። የ90ዎቹን የእድሜ እርከን አልፈውም በሁሉም መስክ ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው። 33 መጽሃፍትን ጽፈዋል።ሃቢታት ፎር ሂውማኒቲ በተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት ቤቶችን በመገንባት አስተዋጾኦዋውን ቀጥለዋል። ከሳቸው በኋላ በመጡት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ላይም ያልመሰላቸውን ነገር ለነገ ሳይሉ በመተቸት ይታወቃሉ።
ማህበራዊ ሕይወታቸው
ከባለቤታቸው ሮዛሊን ጋር ለ77 ዓመታት የቆየ ጽኑ ትዳር ነበራቸው። የትዳራቸውን ጽናት ስኬት ሲናገሩ መቼም ቢሆን ተኮራርፈን ወደ መኝታ ላለመሄድ ስምምነት ነበረን፣ እና ሁሉቀን ማታ ማታ መጽሃፍ ቅዱስ እናነብ ነበር ብለዋል።
ባለቤታቸው ሮዛሊን ካርተር ባለፈው አመት ህዳር ወር ላይ በ96 አመታቸው ነበር ያረፉት ። የአራት ልጆች አባት፣ ባጠቃላይ የ22 ልጆች አያትና ቅድመ አያት የሆኑት ጂሚ ካርተርም ትላንት በተወለዱ በ100 አመታቸው፤ ረጅም እድሜ የቆዩ ብቸኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ነው፤ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት።
«አሜሪካና አለም ታላቅ መሪ አጣች»
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካና አለም ታላቅ መሪ አጣች ብለዋል። “ጂሚ ካርተር ማለት ትርጉምና አላማ ያለው፣ እምነት፣ መርህና ትህትን የተላበሰ፣ እንዲሁም ሌሎችን ያስቀደመ ህይወትን መኖር ምን እንደሚመስል ማሳያ ነው” በማለት አክብሮታቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ተመራጩ ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ጂሚ ካርተር ፕሬዝዳንት የነበሩበት ወቅት ፈታኝ ጊዜ እንደነበረ አስታውሰው ለአሜሪካ የሚችሉትን ሁሉ ያደረጉ በመሆናቸው ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ጂሚ ካርተርን “ማህበራዊ እሴቶችን በአግባቡ የኖሩ፣ የክብር፣ የፍትህ እና የበጎ አገልግሎትን ዋጋ ለሁላችንም ያስተማሩ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ጆርጅ ቡሽ በበኩላቸው ጂሚ ካርተር “ለቤተሰባቸው፣ ለማህበረሰባቸውና ለሃገራቸው ታማኝ የነበሩ፣ የፕሬዝዳንትነትን ክብር ከፍ ያረጉ፣ አገልግሎታቸው ከፕሬዝዳንትነታቸው ጋር ያላበቃ” ሲሉ አወድሰዋቸዋል።
ቢል ክሊንተንም ጂሚ ካርተር “በእምነታቸው የተመራ፣ ለሰው ልጆች አገልግሎት በመስጠት ላይ ያተኮረ ረጅምና ጥሩ ህይወትን አሳልፈዋል” ብለዋል።
በጂሚ ካርተር ሞት የሃዘን መግለጫ መለዕክቶች ከሃገር ውስጥም ከውጪም እየጎረፉ ነው። ልዩ ሃገር አቀፍ የቀብር ስነስርዓት የዛሬ አስር ቀን፣ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ሃሙስ፣ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ/ም እንደሚካሄድ ተገልጿል። ይሄው እለት ሃገር አቀፍ የሃዘን ቀን ተብሎ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የታወጀ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ቀብሩ እለት በዋሽንግተን ዲሲ እና በአትላንታ ከተሞች ውስጥ የተለያዩ የመታሰብያ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ታውቋል።
ጂሚ ካርተር በሰብዓዊነት ላይ ያላቸው ተስፋ፣ በእግዚአብሄር ላይ ያላቸው እምነት፣ በዘላለማዊ የስነምግባር እሴቶች ላይ ያላቸው ጽኑ ጥብቅና የማንነት መገለጫቸው እንደነበር የቅርብ ወዳጆቻቸው ይገልጻሉ።
አበበ ፈለቀ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ