የጃራ መጠለያ ጣቢያ ተፈናቃዮች እንግልት
ረቡዕ፣ ነሐሴ 25 2014በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን “ጃራ” በተባለ መጠለያ ጣቢያ ይኖሩ የነበሩ ከ30ሺህ በላይ ተፈናቃዮች “በአካባቢው ያለውን ጦርነት ሰግተን ትናንት በሙሉ መጠለያ ጣቢያውን ለቅቀን ወደ አፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ ብንደርስም አትገቡም በመባላችን ከብዙ ዉጣ ውረድ በኋላ እንደገና ዛሬ ወደ ቀድሞ መጠለያ ጣቢያችን እየተመለስን ነው” አሉ፣ በመጠለያ ጣቢያው የነበሩ ንብረቶች በመዘረፋቸውም ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፣ የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላክልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ተፈናቃዮች ግቢውን ለቅቀው ሄደው ነበር የሚለውን በሙሉ ባይቀበልም፣ እርዳታ ግን ከዛሬ ጀምሮ ይደርሳቸዋል ብሏል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከአላማጣ ከተማ፣ ከራያ፣ ከራያ ባላ፣ ከኮረም፣ ከኦፍላ፣ ከራያ ቆቦና አጎራባች ወረዳዎች የተፈናቀሉ ከ31 ሺህ በላይ ሰዎች በሰሜን ወሎ ዞን ከወልዲያ ከተማ በ57 ኪሎሚትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጃራ መጠለያ ጣቢያ ይኖራሉ፡፡
ተፈናቃዮቹ ሰሞኑን በሰሜን ወሎ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን ጦርነት በመስጋት ትናንት በመጠለያ ጣቢያው ያሉ ተፈናቃዮች በሙሉ ግቢውን ለቅቀው ወደ አፋር ክልል ማምራታቸውን አንድ ተፈናቃይ አስረድተዋል፡፡ሌላው አስተያየት ሰጪም በጉዞ ላይ በተፈናቃዩ ላይ በርካታ ችግሮችና እንግልቶች ከደረሱበት በኋላ ጭፍራ ቢደረስም “ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ” ባሉት ምክንት ወደ አፋር ክልል መግባት እንዳልተቻለ ነው የገለፁት አፋር ጭፍራ ወረዳ ከደረሱ በኋላ ግን በተለያዩ ምክንያቶች መግባት እንደተከለከሉና በረሀ ላይ አድረው እንደገና ወደ ጃራ ዛሬ እየተመለሱ እንደሆኑ አንድ ተፈናቃይ ተናግረዋል፡፡በጎዞ ላይ ብዙ እንግልቶች እንደደረሰባቸው፣ ወደ መጠለያ ጣቢያው ተመልሰው ቢመጡም ግቢው ተዘርፎ እንዳገኙት ተፈናቃዮቹ አመልክተዋል፣ የምግብ የውሀና የመኝታ ችግሮች በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሉባቸው አመልክተዋል፡፡ በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር ግን ካምፑን ጥለው የሄዱት ጥቂቶች እንደሆኑ አመልክተው እርዳታ ግን ከዛሬ ጀምሮ እንደሚጓጓዝላቸው አረጋግጠዋል፡፡የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን “ስለጉዳዩ ከቦታው መረጃ ስላልደረሰኝ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ” ብለዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ