በትግራይ የጋዜጠኞች መታገት
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 21 2017የጋዜጠኞች መታገት
በትግራይ ያለው የወርቅ ምዝበራ ለመዘገብ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የመንግስታዊው ትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ባልታወቁ ታጣቂዎች ታፍነው እንደነበረ እና ከሰዓታት በኃላ መለቀቃቸው ጣብያው አስታውቋል።
መንግስታዊው ትግራይ ቴሌቭዥን ትላንት ያሰራጨው ዘገባ እንደሚያመለክተው፥ የተቋሙ ባልደረቦች የሆኑ ጋዜጠኞች በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን ይካሄዳል የተባለው ሕገወጥ ወርቅ የማውጣት ስራ እና እያስከተለው ያለው ችግር ለመዘገብ በተንቀሳቀሱበት ወቅት ባልታወቁ ታጣቂዎች ታግተው ከቆዩ በኃላ መለቀቃቸው አመልክቷል። የሚድያ ተቋሙ ጋዜጠኞች ሲታገቱ በወርቅ ማውጣት ስራው ምክንያት በሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ የተፈጠረውን የአካባቢ መበከል ነዋሪዎች ሲያነጋግሩ እንደነበረ ትግራይ ቴሌቭዥን ገልጿል። ይሁንና ከዚህ በተቃራኒ የሆነ መረጃ ያወጣው የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ በሰሜን ምዕራብ ዞን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሶስቱ የትግራይ ቲቪ ባልደረቦች ሕጋዊ ፍቃድ እንዳላቸው መጠየቃቸው እና ይህ በማረጋገጥ መለቀቃቸው በፅሑፍ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ሕገወጥ የወርቅ ቁፋሮ
ይህ በትግራይ ያለው ሕገወጥ ወርቅ የማውጣት ስራ በትግራይ ትልቁ የውዝግብ አጀንዳ ሲሆን፥ በታሪክ ከፍተኛ ተብሎ የሚገለፅ የወርቅ ማውጣት ስራ በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን መቀጠሉ፣ ይህንኑም አካባቢ በዘላቂነት የሚበክሉ ኬሚካሎች በመጠቀም እንደሚከናወን፣ በዚህ ሕገወጥ ተግባር ደግሞ የመንግሰት ባለስልጣናት እና የሰራዊት መሪዎች እጅ እንዳለ በተደጋጋሚ በተለያዩ አካላት ይገለፃል። ባለፈው ሳምንት ህወሓት ባካሄደችው መድረክ የተናገሩት የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ባለፉት አምስት ወራት ከትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን 41 ኩንታል ወርቅ ወጥቶ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉ፥ ይሁንና «ትግራይ ከዚህ ያገኘችው ገቢ የለም፥ ለምን ብሎ የሚጠይቅ አመራር በግዚያዊ አስተዳደሩ የለም» በማለት ሲተቹ ተደምጠዋል።
ወይዘሮ ፈትለወርቅ "በአምስት ወራት ውስጥ 41 ኩንታል ወርቅ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል። የዚህ ዋጋ ከ60 ቢልየን ብር በላይ ነው። የትግራይ ዓመታዊ በጀት አስራ ምናምን ቢልየን ብር ሊሰጠን በስንት ውጣ ውረድ ነው። ይሁን፥ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ አውጥቶ ነው የገዛው እንበል። ይሁንና የግዚያዊ አስተዳደሩ ሰዎች ተጋሩ ከሆኑ፥ በአምስት ወር ከሄደው 41 ኩንታል ወርቅ ትግራይ ምን አገኘች? ብለው መጠየቅ ነበረባቸው" ብለዋል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሣኤ በበኩላቸው ትላንት በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እና ከሰሜን ምዕራብ ዞን ነዋሪዎች ጋር በመቐለ ባደረጉት ውይይት፥ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር የወርቅ ማውጣት ስራው እንዲቆም ቢወስንም የማስፈፀም አቅም እንዳጣ ጠቁመዋል።
ጀነራል ፃድቃን "ከሳምንት በፊት ተሰብስበን እንደ ትልቅ አጀንዳ ይዘን ይህ አካባቢ እየበከለ ያለ እና ሀብት እየበከለ ያለው ወርቅ የማውጣት ስራ ይቁም ብለን ወስነን ነበር። ይሁንና ከዚህ በፊትም ይቁም ብለን ነበር። በውስጣችን በነበረ ክፍፍል አልተፈፀመም። ዋናው ችግር በአካባቢው መንግስት ወስኖ መፈፀም የሚያስችል አቅም የለውም" ብለዋል።
በትግራይ የሚካሄደው ሕገወጥ ወርቅ የማውጣት ስራ አንዱ ሌላው ለመወንጀል ከሚያደርገው ዘመቻ ባለፈ መንግስት ምንም ዓይነት እርምጃ አልወሰደም በማለት የተለያዩ አካላት ይተቻሉ።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ