ሐዋሳ-ደቡብ ኢትዮጵያ መስተዳድር ነዳ በቁነና እንዲሸጥ ወሰነ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በክልሉ «እየተባባሰ መጥቷል» ያለዉን የቤንዚን እጥረት ለመቃለል በክልሉ ቤንዚን በኩፖንና በቁነና እንዲሸጥ መወሰኑን አስታወቀ።የኢትዮጵያ መንግሥት በነዳጅ ዘይት ላይ በተደጋጋሚ ያደረገዉ የዋጋ ጭማሪ በሐገሩ ሕዝብ ኑሮና እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነዉ።የዳጅ ዋጋ ንረትና ለገበያ የሚቀርበዉ መጠን ማነስ ሁለት የደቡብ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች እንዳሉት «በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላ» አቃርጧቸዋል።የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ እንዳለዉ ክልሉ ቤንዚን በቁነና እንዲሸጥ የወሰነዉ ገበያ ላይ ያለዉን ዉስን ቤንዚን በተገቢዉ መንገድ ለማሰራጨት ነዉ።የቢሮዉ ኃላፊ ገለቦ ጎልቶ እንዳሉት ቢሯቸዉ አዲስ ባወጣዉ የቁነና ደንብ መሰረት አሽከርካሪዎች የሚቀዱት ነዳጅ መጠን፣ የሚቀዱበት ነዳጅ ማደያና ነዳጁን የተጠቀሙበት ርቀት ቁጥጥር ይደረግበታል።
«እነዚሕ ባጃጆች እዚሕም ይቀዳል።እዚያም ሔዶ ይቀዳል።ይኸ ፈር የሚይዘዉ አንድ ማሕበር የትማደያ ላይ ነዉ የቀዳዉ----»
በየአካባቢዉ የሚኖሩ አሽከርካሪዎች እንደሚሉት በተደጋጋሚዉ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ጭማሪና እጥረት ምክንያት ነዳጅ ለማግኘት ሥራ ፈትተዉ በየነዳጅ ማደያዎቹ ለረጅም ጊዜ መሰለፍ እየተገደዱ ነዉ።
ሰነዓ-20 ኢትዮጵያዉን ስደተኞች ሞቱ
ኢትዮጵያዉን ስደተኞችን አሳፍራ የአደን ባሕርን በመቅዘፍ ላይ የነበረች አነስተኛ ጀልባ ባሕር ላይ በመገልበጧ አሳፍራቸዉ ከነበሩ ስደተኞቹ 20ዎቹ ሞቱ።የዓለም የፍልስተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) እንዳስታወቀዉ ጀልባይቱ ባለፈዉ ቅዳሜ 35 ኢትዮጵያዉን ስደተኞችን አሳፍራ ከጅቡቲ ጠረፍ ተነስታ ታኢዝ ወደተባለዉ የየመን ግዛት በመቅዘፍ ላይ ነበረች።ታኢዝ ባሕር ጠረፍ ስትደርስ በተነሳ ከባድ ነፋስ ተገፍታ በመግልበጧ ከመንገደኞቹ 20ዎቹ ሲሞቱ፣ የተቀሩት 15ቱ ተርፈዋል።ከሟቾቹ 9ኙ ሴቶች፣ ሌሎቹ ወንዶች ናቸዉ።በርካታ ኢትዮጵያዉን ስደተኞች ከጅቡቲና ሶማሊያ ተነስተዉ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር ሲሞክሩ አንድም ሰምጠዉ አለያም በረሐ ዉስጥ ይሞታሉ።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ መሠረት ባለፉት 10 ዓመታት ዉስጥ ወደየሚን ለመግባት የሞከሩ 3 ሺሕ 435 ስደተኞች ሞተዋል፣ ወይም ያሉበት አይታወቀም።ከነዚሕ ዉስጥ 1 ሺሕ 416ቱ ባሕር ዉስጥ ሰምጠዉ ሞተዋል።አብዛኞቹ ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ።
ኒሚይ-የሳሕል አካባቢ ሐገራት በአዋሳኝ ድንበሮቻቸዉ ጦር ሊያሰፍሩ ነዉ
የኒዤር፣ የቡርኪና ፋሶና የማሊ መንግሥታት በአዋሳኝ ድንበሮቻቸዉ የሸመቁ አማፂያንን የሚወጋ የጋራ ጦር ኃይል ሊያሠፍሩ ነዉ።እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2020 እስከ 2023 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት የሶስቱ ሐገራት ወታደራዊ ሁንታዎች ከየሐገራቱ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይና ከሌሎች ምዕራባዉያን መንግስታት ጋር የነበራቸዉን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር አቋርጠዋል።በምትኩ የአካባቢዉን ፀጥታ በጋራ ለማስከበርና ጠላቶቻቸዉን ተባብረዉ ለመዉጋት የሳሕል መንግስታት ትብብር (AES) ያሉትን ማሕበር መሥርተዋል።የኒዤር መከላከያ ሚንስትር ሳሊፉ ሞዲ ዛሬ እንዳሉት በሳምንት ዉስጥ የሚሠፍረዉ ጦር በአየር ኃይል፣በከባድ መሳሪያና በቃኚና ሰላይ ኃይል የተጠናከረ 5000 ወታደሮች ይኖሩታል።ጦሩ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አላቸዉ የሚባሉና ሌሎች አማፂያንን ይወጋል።የሳሕል አካባቢ መንግስታት፣ የምዕራባዉያን ጦር ከአማፂያን ጋር ሲዋጉ በርካታ ዓመታት አስቆጥረዋል።በተከታታዩ ዉጊያ በሺሕ የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተ,ፈናቅሏል።
ብራስልስ/ፓሪስ-የትራምፕ ማስጠንቀቂያና የአዉሮጳዉያን ሥጋት
ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አዲስ ያወጁት የዉጪ ጉዳይ መርሕ የአሜሪካን የረጅም ጊዜ ወዳጅ አዉሮጳዉያንን አስደንግጦ ለመፍትሔ እያጣደፈ ነዉ።ትራምፕ መስተዳድራቸዉ ከዉጪ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦችና ኩባንዮች ላይ ቀረጥ እንደሚጨምር አሳዉቀዋል።በትራምፕ ዉሳኔ መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪስ የተፈጥሮ ጥበቃ ስምምነትና ፣ከዓለም የጤና ድርጅት አባልነት ትወጣለች። የሰሜን አትላቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል መንግስታት ለድርጅቱ ተጨማሪ ገንዘብ ካላዋጡ አሜሪካ ድጋፏን ትቀንሳለችም።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ካያ ካላ ዛሬ እንዳሉት አዉሮጳ ትራምፕ ያሉትን ማድረግ አለባት።
«ትራምፕ በቂ ገንዘብ አታዋጡም ማለታቸዉ እዉነት ነዉ።ተጨማሪ ገንዘብ የምናዋጣበት ጊዜ አሁን ነዉ።ከአባል ሐገራት፣ከግሉ መስክና ከአዉሮጳ የጋራ በጀትም ልናዋጣ ይገባል።ሥለ ሩሲያ እዉነታዉን መቀበል አለብን።ሩሲያ ዛሬም፣ነገም፣ለመከላከያ በቂ ገንዘብ እስካላወጣን ድረስ ለሕልዉናችን አስጊ ነች።»
የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮና የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በበኩላቸዉ ዛሬ ፓሪስ ዉስጥ ባደረጉት ስብሰባ የትራምፕን መርሕ ለመቋቋም አዉሮጳ ጠንካራ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለበት ተስማምተዋል።ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ዉይይት ከመከላከያዉ ጉዳይ ይልቅ አዉሮጳ ከአሜሪካ ጋር ለሚኖራት የንግድ ግንኙነት ልዩ ትኩረት መስጠታቸዉ ተዘግቧል። የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የትራምፕ መርሕ ለአዉሮጳ ፈታኝ እንደሚሆን አሳዉቀዋልም።ጀርመንን ጨምሮ አብዛኞቹ የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግሥት ሕብረቱ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር አዲስ የንግድ ስምምነት እንዲዋዋል ይፈልጋሉ።ፈረንሳይ ግን አዲስ ስምምነት ከመፈራረም ይልቅ የትራምፕ መስተዳድር በአዉሮጳ ሸቀጦችና ኩባንዮች ላይ አዲስ ታሪፍ ከጣለ፣ አዉሮጳም በአሜሪካ ሸቀጦችና ኩባንዮች ላይ ተመሳሳይ ርምጃ መዉሰድ አለባት ባይ ናት።
ዳቮስ-ጉቴሬሽ ለጋዛዉ ተኩስ አቁም ትራምፕን አመሰገኑ
የጋዛ ሕዝብን ከተጨማሪ እልቂት ያደነዉና የታገቱ እስራኤላዉያንን እንዲለቀቁ የረዳዉ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ከፍተኛ ግፊት ማድረጋቸዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አስታወቁ።ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ቱቴሬሽ ዳቮስ-ስዊትዘርላንድ ለተሰየመዉ የዓለም የምጣኔ ሐብት ጉባኤ እንደነገሩት የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲደረግ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቀጠር፣ ቱርክና ሌሌችም ሐገራት ለወራት ጥረዋል።ይሁንናበተለይ እስራኤል ስምምነቱን ላለመቀበል ለረጅም ጊዜ ማቅማማቷን ድንገት ያቆመችዉ በትራምፕ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ነዉ ብለዉ ጉተሬሽ ያምናሉ።
«ይሁንና ድርድሩ ሲጓተት፣ሲጓተት፣ ሲጓተት ነበር።ድንገት ግን ሆነ።እንደሚመስለኝ በዚያ ሰዓት የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዝደንት ከነበሩት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ አስተዋፅኦ ተደርጎ ነበር።እስራኤል ተኩስ ከመቆሙ ከሁለት ቀናት በፊት የነበራትን አቋም ባንዴ ለዉጣ ተኩስ አቁሙን ተቀብላለች።ይሕ እንደሚመስለኝ የጠንካራ ዲፕሎማሲና አብነት አሳይቶቶናል።ለዚሕ እዉቅና ልንሰጠዉ ይገባል።»
ጉቴሬሽ በዚሑ በዳቮሱ ጉባኤ ላይ አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የተፈጥሮ ሐብትን ለማስጠበቅ የተረገዉን ዓለም አቀፍ ስምምነት ማፍረሳቸዉን ተችተዋል።
ሰነዓ-ሁቴዎች ይዘዋቸዉ የነበሩ የመርከብ ሠራተኞችን ለቀቁ
አብዛኛ የመንን የሚገዙት የሁቲ አማፂያን አምና ሕዳር ይዘዋቸዉ የነበሩ የአንድ መርከብ ሠራተኞችን ዛሬ ለቀቁ።የየመኑ ሳባ ዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ የሁቲ ላዕላይ ምክር ቤት በወሰነዉ መሠረት ጋላክሲ ሊደር የተባለችዉ መርከብ ሠራተኞች ተለቀዉ ወደ ኦማን ሔደዋል።የሁቲ ታጣቂዎች እስራኤል የጋዛ ሕዝብን መገድልና ማሰቃየቷን በመቃወም በአደን ባሕረ ሰላጤና በቀይ ባሕር በኩል ከእና ወደ እስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን ሲያጠቁ ነበር።ሁቴዎች ጋላክሲ ሊደር የተባለችዉን መርከብ አጥቅተዉ 25 ሠራተኞችን የያዙት አምና ሕዳር ጥቃቱን እንደጀመሩ ነበር።አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበዉ መርከቢቱ በበሐማ ስም የተመዘገበች፣ የጃፓን ኩባንያ የሚያንቀሳቅሳት፣አብረሐም ራሚ ኡንጋር ከተባሉ የእስራኤል ነጋዴ ጋር ግግኙነት ያላት የብሪታያ ንብረት ናት።የሁቲ ባለሥልጣናት እንዳሉት 25ቱንስ እስረኞች የለቀቁት የጋዛዉን ተኩስ አቁም በመደገፍ፣ ከሐማስ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነዉ።
አሻፈንቡርግ-ሁለት ሰዎች በጩቤ ተገደሉ
ደቡብ ጀርመን አሻፈንቡርግ ከተማ ዉስጥ ማንነቱ በግልፅ ያልተነገረ አንድ ግለሰብ ሁለት ሰዎችን በጩቤ ወግቶ ገደለ።ሌሎች ሁለት ሰዎችን አቆሰለ።ፖሊስ አንዳስታወቀቁ ከሟቾቹ አንዱ የ41 ዓመት ጎልማሳ፣ ሁለተኛዉ የሁለት ዓመት ሕፃን ነዉ።ፖሊስ አንድ የ28 ዓመት ወጣት አፍቃኒስታናዊ ተጠርጣሪን መያዙን አስታዉቋል።ፖሊስ አክሎ እንዳለዉ የጥቃቱን ዓላማና የአጥቂዉን ትክክለኛ ማንነት ለመለየት ገና በምርመራ ላይ ነዉ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ