1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaእሑድ፣ ጥር 11 2017

https://p.dw.com/p/4pLXx

የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ RSF ኃይሎች በምዕራብ ዳርፉር በከበባ ስር በምትገኘው ኤል ፋሽር ከተማ ባደረሱት ጥቃት በትንሹ 14 ሰዎች መገደላቸውን የሱዳን ማህበራዊ አንቂዎች ቡድን ዛሬ አስታወቀ። 

የፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ ትናንት ቅዳሜ ዑም ካዳዳህ በተባለ ስፍራ ያደረሰው ጥቃት አሰቃቂ እንደነበር የጠቀሰው የማህበራዊ አንቂ ቡድኑ ተጨማሪ ስለደረሰ ጉዳት ግን በዝርዝር አልገለጸም።

አብዛኛውን የዳርፉር ክፍል የተቆጣጠረው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል የመጨረሻ እና እስካሁንም በቁጥጥሩ ስር ያልገባችውን የኤል ፋሽር ከተማ ለመቆጣጠር ካለፈው ዓመት የግንቦት ወር አንስቶ ጥቃት ሲያደርስ ቆይቷል።

የሱዳን ብሔራዊ ጦር በምስራቃዊ እና ሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተወስኖ ሲቆም መዲናዋ ካርቱምን ጨምሮ አጎራባች ትልልቅ ከተሞች አሁንም ድረስ የጦርነት አውድማ ሆነው መቀጠላቸውን ዘገባው አመልክቷል።

በሱዳን ያለው ጦርነት በጎርጎርሳዉያኑ ሚያዝያ 2023 የጀመረ ሲሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት ዳርጎ  ከ12 ሚሊዮን የሚልቁትን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል። መቋጫ ያጣው ጦርነቱ ከ20 ሚሊዮን የሚልቁትን ደግሞ ለረሃብ ሲያጋልጥ ተፋላሚ ወገኖች አንዳቸው ሌላኛውን ከመወንጀል ባለፈ ለጦርነቱ መፍትሄ መሻትን ግን የፈለጉ አልመሰሉም ።

 

በናይጄሪያ ነዳጅ በጫነ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ ፍንዳታ በትንሹ የ86 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

በማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ ነዳጅ ሲያፈስ ነበር ከተባለው ቦቴ ለመቅዳት በርካታ ሰዎች  መሰብሰባቸው አደጋውን የከፋ አድርጎታል ነው የተባለው። ትናንት ቅዳሜ በደረሰው አደጋ ከሞቱ ሰዎች በተጨማሪ 52 ያህል ሰዎች ክፉኛ ቆስለው ወደ ህክምና ተቋማት መወሰዳቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በጎርጎርሳዉያኑ 2023 ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ የሀገሪቱን የነዳጅ ድጎማ ማንሳታቸውን ተከትሎ በናይጄሪያ የምግብ እና የመጓጓዣ ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል።

ፕሬዚዳንቱ በአደጋው ለተጎዱት ሀዘናቸውን ገልጸው በተመሳሳይ ሁኔታ ነዳጅ ለመቅዳት የሚደረግ ሙከራ የሚያስከትለውን አደጋ ሀገር አቀፍ ግንዛቤ የማሳደግ ዘመቻ እንዲጀመር መመሪያ አስተላልፈዋል።

በናይጄሪያ ባለፈው ጥቅምት ወር በደረሰ ተመሳሳይ አደጋ የ170 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።

 

በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል እና ሃማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መደረግ ጀመረ።

የተኩስ አቁሙ ከተያዘለት ጊዜ ሶስት ሰዓታት አርፍዶ ዛሬ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ረፋድ 5 ሰዓት  ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ ጽ/ቤት አስታውቋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለሶስታ ሰዓታት ለመዝገየቱ እስራኤል ሃማስን ተጠያቂ አድርጋለች። ሃማስ በስምምነቱ መሰረት የሶስት ሴት ታጋች  እስራኤላዉያንን ስም ይፋ ሳያደርግ በመቅረቱ እስራኤል የምትሰነዝረውን ጥቃት እንድትቀጥል እንዳስገደዳት አስታውቃለች። ሃማስ በበኩሉ የታጋቾቹን ስም በቶሎ አለማሳወቁ በቴክኒክ ችግር ምክንያት ነው ብሏል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለ18 ወራት የዘለቀውን የጋዛ ጦርነት ሲገታ 96 ያህል  እስራኤላዉያን ታጋቾችን ሲያስለቅቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማዉያን እስረኞችን ከእስራኤል እስር ቤቶች ያስፈታል።

በአሜሪካ ፣ ቃጣር እና ግብጽ አሸማጋይነት ለወራት ሲደረግ የሰነበተው ሁለቱን ተፋላሚዎች የማሸማገል  ጥረት ከቀናት በፊት ሲሰምር የእስራኤል ካቢኔ ይሁንታውን ሰጥቶ ያጸደቀው ግን ትናንት ቅዳሜ ነበር።

ባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ሃማስ እስራኤል ላይ ድንገት በሰነዘረው ጥቃት የተጀመረው ደም አፋሳሹ የጋዛ እልቂት ከ46 ለሚልቁ ፍልስጥኤማዉያን እንዲሁም 1200 እስራኤላዉያን መገደል ምክንያት ሲሆን ከ100 ሺ የሚልቁ ፍልስጥኤማዉያን ቆስለዋል፤ ጋዛንም ወደ ፍርስራሽነት ቀይሯታል።

 

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልዶሚር ዜሌንስኪ አጋር ሃገራት ተጨማሪ  አሜሪካ ሰራሽ ፓትሪዮት የአየር መከላከያ ስረዓት እንዲያበረክቱላቸው ጥሪ አቀረቡ ።

ዜሌንስኪ ጥሪውን ያቀረቡት ሀገራቸው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሺ በላይ የሩስያ የአየር ድብደባ ከተፈጸመባት በኋላ ነው።

ዜሌንስኪ በቴልግራም ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ለዩክሬን "ተጨማሪ ፓትሪዮት ማለት የበለጠ የህይወት ጥበቃ ማለት ነው" ለዚህም "የአጋሮቻችንን ጠንካራ ድጋፍ እንሻለን " ብለዋል። 

ሩስያ ባደረሰችው በዚሁ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት የበርካታ ሰዎች ሲያልፍ በተመሳሳይ በርካቶች ቆስለዋል።

የጥቃቱን መጠን በዝርዝር ያሰፈሩት ፕሬዚዳንቱ ሩስያ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ 660 በምሪት የሚጓዙ ቦምቦች ፣ 550 ድሮኖች እና የ60 ሚሳኤሎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዩክሬን 300 ድሮኖች እና 33 ሚሳኤሎችን ማክሸፍ መቻሏን ነው ፕሬዚዳንቱ የጠቀሱት ።

በሩስያ መጠነ ሰፊ ጥቃት ኪየቭ ፣ ዛፖሪዢያ እና የዶምባስ ግዛት መጠነ ሰፊ ጉዳት ያስተናገዱ መሆናቸውን የጀርመን ዜና ምንጭ ዘግቧል።

 

 

በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት በፊልም ፣ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ድራማዎች የሚታወቀው አንጋፋው አርቲስት እንቁስላሴ ወርቅአገኘሁ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

አርቲስት እንቁስላሴ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ ማለፉን የአርቲስቱ  ቤተሰቦች  መናገራቸውን የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በአዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ ተወልዶ ያደገው አርቲስቱ ከ30 በላይ ፊልሞች እና ትያትሮች ላይ በመተወን አድናቆት ተችሮታል።

ከእነዚህ ውስጥም የእግር እሳት፣ ሥርየት፣ ሰው ለሰው፣ መንጠቆ ቴአትር እና ሌሎች የቴሌቪዥን ድራማዎች እና ፊልሞች ላይ መተወኑን ዘገባዎቹ አመልክተዋል።

አርቲስት እንቁስላሴ ወርቅአገኘሁ የአንድ ወንድ እና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበር፡፡

ታምራት ዲንሳ

ልደት አበበ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።