1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 11 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 11 2017

በቶሮንቶ እና በአምስተርዳም የማራቶን ሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውይና አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች ድል ቀንቷቸዋል ። ነገ ስለሚጀምረው የካፍ የአዲስ አበባ ስብሰባ በተመለተከም ቃለመጠይቅ ይኖረናል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እስካሁን ከነበሩ 8 ግጥሚያዎች ሰባቱን በማሸነፍ ዘንድሮ ዋንጫ የማንሳት ግስጋሴውን ቀጥሏል ።

https://p.dw.com/p/4m4Ep
Deutschland | Berliner Marathon 2024
ምስል John Macdougall/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን በወንድም በሴትም በድል ስለታጀቡባቸው የማራቶን ሩጫዎች እንቃኛለን ነገ ስለሚጀምረው የካፍ የአዲስ አበባ ስብሰባ በተመለተከም ቃለመጠይቅ ይኖረናል ከተጨማሪ የስፖርት መረጃዎች ጋር ለዝግጅቱ ማንተጋፍቶት ስለሺ   

በቶሮንቶ እና በአምስተርዳም የማራቶን ሩጫ ፉክክሮች  ኢትዮጵያውያን  አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች ድል ቀንቷቸዋል ። አዲስ አበባ ውስጥ ነገ ስለሚጀምረው የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) 46ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤን በተመለከተ ቃለ መጠይቅ አሰናድተናል ። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ስለ ተከናወኑ የእግር ኳስ ውጤቶች ዳሰሳ አድርገናል ። የመኪና ሽቅድምድ እና ሌሎች ዘገባዎችንም አካተናል ።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቶሮንቶ ማራቶን በወንድም በሴትም አሸነፉ ። ትናንት ካናዳ ውስጥ በተካሄደው የቶሮንቶ  ማራቶን ኢትዮጵያውያት አትሌቶች  አምስተኛ ብቻ ጣልቃ አስገብተው ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ተከታትለው አሸንፈዋል ።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዋጋዬነሽ መካሻ ከምን ጊዜውም በላይ ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን የቦታውን ክብረወሰን አሻሽላ ለድል በቅታለች ። አትሌት ዋጋዬነሽ ርቀቱን 2:20:44 በመሮጥ ነው በአንደኛነት ያጠናቀቀችው ። ዋጋዬነሽን ተከትለውት በሁለተኛነት እና ሦስተኛነት ያጠናቀቁትም የሀገሯ ልጆች አትሌት ሮዛ ደረጀ እና አትሌት አፈራ ጎደፋይ ናቸው ። ሦስቱም ኢትዮጵያዊያት አትሌቶች ባለፈው ዓመት በቦታው ተይዞ የነበረውን የ2:22:16 ክብረወሰን ማሻሻል ችለዋል ። አራተኛ መሠረት ገብሬ እንዲሁም አምስተኛ ረድኤት ዳንኤል በመግባት ሩጫውን የኢትዮጵያውያት ብቻ አስመስለውት ነበር ። በመሃላቸው አምስተኛ ጣልቃ የገባችው ካናዳዊቷ ናታሻ ዎድካ ናት ። ኬንያዊቷ ሯጭ ሊድያ ሲሚዩ የስምንተኛ ደረጃ አግኝታለች ።

ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን ብርታታቸውን ባሳዩበት በወንዶች ተመሳሳይ ርቀትም ኢትዮጵያዊው ሯጭ ሙሉጌታ አሠፋ 2:07:16 በመሮጥ አሸናፊ ሁኗል ። ኬንያውያን ሯጮች ዶሜኒክ ንጌኖ እና ኖሐ ኪምኬምቦይ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።  ኢትዮጵያዊው አትሌት ኃይሉ ዘውዱ አራተኛ ኬንያዊው ብሪያን ኪፕሳንግ አምስተኛ፤ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጊዜአለው አያና ስድስተኛ ደረጃ በማግኘት ተከታትለው ገብተዋል ።

ኢትዮጵያውያን በፓሪስ ማራቶን ወቅት
ኢትዮጵያውያን በፓሪስ ማራቶን ወቅት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Haymanot Tiruneh/DW

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና፦ ኔዘርላንድ ውስጥ ትናንት (ጥቅምት 10 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) በተከናወነው የአምስተርዳም  ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ድል አድርገዋል ። በሴቶች ፉክክር፦ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው 2:16.52 በመሮጥ የቦታውን ክብረወሰን አሻሽላ በአንደኝነት አጠናቅቃለች ። በተመሳሳይ የወንዶች ፉክክር ደግሞ፦ አትሌት ጸጋዬ ጌታቸው በ2:05.38 ቀዳሚ ሆኖ በማጠናቀቅ ለድል መብቃቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘግቧል ።

የአፍሪቃ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) 46ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በነገው ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ ይካሄዳል ። የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ከጉባኤው ዋነኛ አጀንዳዎች መካከል ዋነኞቹ የፕሬዚደንቶች የዕድሜ ጉዳይ ከፍ እንዲል የሚለው ይገኝበታል ብሏል ። ዝርዝሩን ያብራራል ። 

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እስካሁን ከነበሩ 8 ግጥሚያዎች ሰባቱን በማሸነፍ ዘንድሮ ዋንጫ የማንሳት ግስጋሴውን ቀጥሏል ። ከዋነኞቹ ተፎካካሪዎቹ መካከል  በ30ኛው ደቂቃ ላይ ዊሊያም ሳሊባን በቀይ ካርድ ያጣው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት በቦርመስ 2 ለ0 ተሸንፏል ። በ17 ነጥቡም ተወስኗል ። ቦርመስ እስካሁን ካደረጋቸው ግጥሚያዎች አርሰናልን ያሸነፈበት ሦስተኛ ድሉ ነው ። ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ዎልቭስን በገዛ ሜዳው 2 ለ1 ድል አድርጎት ነጥቡን ወደ 20 በማድረስ ሊቨርፑልን እግር በእግር እየተከተ ለው ። ማን ሲቲ ትናንት በጨዋታው መገባደጃ፤ ማለትም መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 5ኛ ደቂቃ ላይ ነው በጆን ስቶን ግብ ነበር ማሸነፍ የቻለው ። የማታ ማታ ከጉድ የወጣው ማንቸስተር ሲቲም እንደ አርሰናል ከሊቨርፑል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ይሰፋ ነበር ።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እየመራ ነው
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እስካሁን ከነበሩ 8 ግጥሚያዎች ሰባቱን በማሸነፍ ዘንድሮ ዋንጫ የማንሳት ግስጋሴውን ቀጥሏል ምስል Michael Regan/Getty Images

ብርቱ ፉክክር በታየበት የትናንቱ ግጥሚያ ሊቨርፑል አንፊልድ ውስጥ ቸልሲን 2 ለ1 ሸኝቶ ነጥቡን 21 አድርሷል ። ማንቸስተር ሲቲን በ1 ነጥብ ይበልጣል ። ቸልሲ የትናንቱን ጨዋታ ቢያሸንፍ ኖሮ ከአርሰናልም ጋር ይስተካከል ምናልባትም በግብ ክፍያ ይበልጥ ነበር ። ለዚያም ይመስላል እስከ ጨዋታው ፍጻሜ ድረስ ብርቱ ፉክክር ያሳየው ። የሊቨርፑል የትናንትና ድል ከእነ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ውጤት አንጻር የፕሬሚየር ሊጉ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው የስፖርት ተንታኞች ገልጠዋል ። የጥቅምት 04 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በሌሎች ግጥሚያዎች፦ ላይስተር ሲቲ ሳውዝሐምፕተንን 3ለ2፤ ኤቨርተን ኢፕስዊች ታውንን 2 ለ0 አሸንፈዋል ።  ከሁለቱም በኩል ቀይ ካርዶች በታዩበት የቅዳሜ ግጥሚያ አስቶን ቪላ ፉልሀምን 3 ለ ለ1 ድል አድርጓል ። ቶትንሀም ዌስትሀምን 4 ለ1 ሸንቷል ።  በእለቱ ኒውካስትል በብራይተን የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ። ማንቸስተር ዩናይትድ ብሬንትፎርድን 2 ለ1 ማሸነፍ ችሏል ።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት ሆፈንሀይም ቦሁምን እንዲሁም ፍራይቡርግ አውግስቡርግን በተመሳሳይ 3 ለ1 አሸንፈዋል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በባዬርን ሌቨርኩሰን የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ። ቬርደር ብሬመን ቮልፍስቡርግን 4 ለ2 ሸኝቷል ። ዑኒዮን ቤርሊን ሆልሽታይን ኪይልን 2 ለ 0 አሸንፏል ።  ባዬርን ሙይንሽን ሽቱትጋርትን 4 ለ0 አደባይቷል ።  ሦስቱ ግቦች የሔሪ ኬን ናቸው ። ቡንደስሊጋውንም እንደ ላይፕትሲሽ በ17ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት ይመራል ። ላይፕትሲሽ ቅዳሜ ዕለት ማይንትስን 2 ለ0 ድል አድርጓል ።

ጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል
ጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል ከጥር ወር ጀምሮ የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ እንደሚሆኑ ታወቀምስል Matthias Schrader/AP/picture alliance

ጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል ከጥር ወር ጀምሮ የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ እንደሚሆኑ ታወቀ ። ቀደም ሲል የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን፤ የእንግሊዙ ቸልሲ እንዲሁም የፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል ።  በባዬርን ሙይንሽን ቡድን ያሰለጥኑት የነበረው እንግሊዛዊ አጥቂ ሔሪ ኬን የቀድሞ አሰልጣኙን አወድሶ ጊዜው እስኪደርስ በብሔራዊ ቡድኑም በእሳቸው ለመሰልጠን እንደጓጓ ገልጧል ። ሔሪ ኬን ይህን ያለው ቅዳሜ ዕለት ሦስት ግብ አስቆጥሮ ሔትሪክ በመሥራት ባዬርን ሙይንሽን በቡንደስ ሊጋው ሽቱትጋርትን 4 ለ0 እንዲያሸንፍ ካስቻለ በኋላ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ነው ።

የመስከረም 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ ቶማስ ቱኹል ከባዬር ሙይንሽን ጋር የገቡት ውል እስከሚቀጥለው የጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ድረስ ነበር ። ሆኖም ውሉ ሳይጠናቀቅ የተቋረጠው ከዐሥርተ ዓመት ወዲህ ባዬርን ሙይንሽን ባለፈው የጨዋታ ዘመን ዋንጫ ማንሳት ስለተሳነው ነበር ። ጀርመናዊው ቶማስ ቱኸል በ2026 የዓለም ዋንጫ ለ60 ዓመታት ዋንጫ ማንሳት የተሳነውን የእንግሊዝ ቡድን ለድል እንዲኢበቁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል ። ሦስቱ አናብስት የዓለም ዋንጫን ማሸነፍ የቻሉት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1966 ብቻ ነው ። የ51 ዓመቱ አሰልጣኝ የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ እንደሚሆኑ ለስካይ ስፖርት ይፋ ያደረጉት ረቡዕ ዕለት ነው ።   የቀድሞው የእንግሊዝ አሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌትን የሚተኩት ቶማስ ቱኹል ከስቬን-ጎራን ኤሪክሰን እና ፋቢዮ ካፔሎ ቀጥሎ ሦስተኛው የውጭ ሃገር አሰልጣኝ ይሆናሉ ። ጀርመናዊ አሰልጣኝ የእንግሊዝ ቡድንን ሲመራም ቶማስ ቱኹል የመጀመሪያው ናቸው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዖምና ታደለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti