1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖለቲከኛ ጀዋር መሀመድ «የምስጋና ጉዞ» በጀርመን

ሰኞ፣ ግንቦት 29 2014

«እዚህ በሁለት ምክንያቶች ነው የመጣሁት ፤ አንደኛው ላመሰግናችሁ፣ ሁለተኛው ደግሞ የወደፊት አቅጣጫ ላመላክታችሁ ነው። እስር ብዙ ነገር ያስተምራል። ለእኛም ሆነ በሀገር ቤት ለሚገኘው ህዝብ ድምጽ ሆናችሁልን በዚያ ቅዝቃዜ ውስጥ ከጎናችን ስለነበራችሁ ፣ ከቤተሰቦቻችን ጎን ስለነበራችሁ በጀርመን የምትገኙ ኦሮሞዎችን እናመሰግናለን ።»

https://p.dw.com/p/4CKfY
[No title]

አቶ ጀዋር መሐመድ ከእስር ከተፈቱ በኋላ አውሮጳ ደርሰዋል

በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የአሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ኦፌኮ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ፖለቲከኛ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ  «የምስጋና ጉዞ» ብለው የሰየሙት በአውሮጳ እና ሰሜን አሜሪካ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ለመገናኘት የሚያደርጉት ይኸው ጉዞ ከፓርቲው ተልዕኮ ውጭ ነገር ግን በፓርቲው ዕውቅና የተሰጠው መሆኑን የፓርቲው ጽ/ቤት አስታውቋል። 
ፖለቲከኞቹን ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ሲገናኙ የመጀመሪያ በሆነው በዚሁ ጉዞ አቶ ጀዋር መሐመድ ባሳለፍናቸው ቅዳሜ እና እሁድ በጀርመን እና ፈረንሳይ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ማህበረሰብ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ባለፈው ቅዳሜ በጀርመኗ ደቡባዊ ከተማ ኑርንበርግ ፉርት ከደጋፊዎቻቸው የተገናኙት አቶ ጀዋር መሀመድ የጉዟቸው አላማ ሁለት መሆናቸውን ተናግረዋል።  
«እዚህ በሁለት ምክንያቶች ነው የመጣሁት ፤  አንደኛው ላመሰግናችሁ፣ ሁለተኛው ደግሞ የወደፊት አቅጣጫ ላመላክታችሁ ነው። እስር ብዙ ነገር ያስተምራል። ለእኛም ሆነ በሀገር ቤት ለሚገኘው ህዝብ ድምጽ ሆናችሁልን በዚያ ቅዝቃዜ ውስጥ ከጎናችን ስለነበራችሁ  ፣ ከቤተሰቦቻችን ጎን ስለነበራችሁ ፣ የተሰው ወገኖቻንን ስለደገፋችሁ ፣ ባላችሁት ነገር የቆሰለውን ስለደጎማችሁ በጀርመን የምትገኙ ኦሮሞዎችን እናመሰግናለን ።»
በሀገሪቱ የሶማሌ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ ጦርነት እና ግጭቶች እየተካሄደ ነው ያሉት አቶ ጀዋር ፤ ጦርነቱ እና ግጭቶች በሀገሪቱ ሌሎች ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶችን አስከትለው ሀገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ስሟ በቀውስ እንዲጠራ አድርጓል ብለዋል። ሂደቱ ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ማስከተሉን ገልጸው ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ የተጠበቀው ለውጥ መስመሩን መሳቱ ነው ይላሉ።
«የዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ምክንያቱ ምንድነው ? ብለን የጠየቅን እንደሆነ ሽግግሩ መስመሩን መልቀቁ ፤ ከኢህአዴግ በኋላላ ሌላ አምባገነን ስርዓት ለመፍጠር መፈለግ፣ ቅያሜዎች እና ጥርጣሬዎች መበራከት በፊት ለነበሩ ችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ የአንድን ቡድን ፍላጎት እና የበላይነት ለማረጋገጥ መሯሯጥ መኖሩ ወደዚህ ጦርነት አስገብቶናል።
አቶ ጀዋር በንግግራቸው ቀደም ሲል ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ሁሉም የፖለቲካ ተዋንያን ሊደማመጡ ይገባ ነበር ፣ ያ ባለመሆኑ ደግሞ ሀገሪቱ አሁን በቀላሉ ልትወጣ ከማትችለው ችግር ውስጥ አስገብቷቷል ብለዋል።  ዘላቂ እና ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት መደረግ አለበት ያሉትን አመላክተዋል። 
ያለው መፍትሔ እውነተኛ ሰላም ነው። በኃይል የሚመጣ ሰላም ሳይሆን በእውነት የሚመጣ ሰላም፤  በጉልበት የሚመጣ ሰላም ሳይሆን በጥበብ የሚመጣ ሰላም ፤ በማፈን እና በማስጨነቅ የሚመጣ ሳይሆን በመነጋገር ፣በመደማመጥ  እና በመቻቻል የሚመጣ ሰላም ያስፈልገናል። »
ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት ፤ ለችግሮች መንስኤ «የዝሆን ያህል» ድርሻ ነበረው ያለው መንግስትም ለመፍትሄውከፊት መቅደም ይገባዋልም ብለዋል። 
በመድረኩ አግኝተን ካነጋጋርናቸው ውይይቱ ተካፋዮች መካከል የበርሊን ከተማ ነዋሪው  አቶ ተስፋዬ አብዲሳ አንዱ ናቸው። እንደ እርሳቸው በሀገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ዘላቂ እና ሰላማዊ መፍትሄ ይሻል ባይ ናቸው ። ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ውይይቶች በአፋጣኝ መደረግ እንደሚኖርባቸው ነው። 
«በዚያች ሀገር ፖለቲካ ያገባናል የሚሉ አካላት ሁሉ መጥተው በጠረጴዛ ዙሪያ ምንድነው ችግሩ ብለው ከመጀመሪያው ጀምረው መምከር አለባቸው። በችግሮቹ ላይ ግልጽ ውይይት መደረግ አለበት ። ዛሬም ነገም ወደ እነዚያ ችግሮች መመላለስ አይኖርብንም።የጋራ የሆነ ብሄራዊ መግባባት ለመድረስ መጣር ነው።» 
ሌላዋ የበርሊን ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ቢፍቱ ጣሃ እና የሙኒክ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ፈቲያ አወልም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ ። ነገር ግን ከመንግስት እና የፖለቲከኞች ሚና ባሻገር ህዝቡ በመደማመጥ የመፍትሄ አካል እንዲሆን ራሱን ማዘጋጀት አለበት ባይ ናቸው። 
« ያቺን ሀገር የሚያዋርድ የዚያችን ሀገር ህዝብ የሚያዋርድ ነገር ነው የተፈጠረው ፤ የክፋትን ጥግ አይተናል። እኔ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አንዲት ኢትዮጵያዊት  የምለው ወደ ማስተዋል ተመልሰን አገራችን እና ህዝባችን ተረጋግቶ ህዝባችን መደማመጥ አለበት፤ ራሱን ማዳመጥ አለበት። ሆይ ሆይ የሚለውን የግፋ በለው ፖለቲካ ልናቆም ይገባል።,,,ህዝቡ ተግቶ መስራት ነው ያለበት ። ኑሮውን ለመለወጥ ፤ ሁሉም ፖለቲከኛ አይደለም ይሄን ፕሮፖጋንዳ ትቶ ፤ ጥላቻ ትቶ ለሰዎች እልቂት ማጨብጨም ትተን ሰላም ነው የሚያዋጣን ብለን መቆም አለብን » 
 » 
አቶ ጀዋር መሐመድ ባለፈው ቅዳሜ በጀርመን በጀመሩት እና ትናንት በፈረንሳይ ፓሪስ ያስቀጠሉት ጉዞ ቀጥሎም በቤልጅየም ኔዘርላንድ እና እንግሊዝ ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸው ጋር ከተጋናኙ በኋላ ወደ ሰሜና አሜሪካ እንደሚያቀኑ ለመረዳት ችለናል።   

[No title]

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ