ጦርነትና የተፈጥሮ ሃብት
ማክሰኞ፣ ኅዳር 4 2005ጦርነትና የትጥቅ ትግል በሚካሄዱባቸዉ አካባቢዎች የሰዉ ህይወትና ንብረት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሃብት ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚዳረግ በግልፅ ይታያል። የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በየዓመቱ ጥቅምት 27 ቀን በጦርነትና ግጭት የሚወድመዉ የተፈጥሮ አካባቢ እንዲታሰብ ዉሳኔ ካሳለፈ ዓመታት ተቆጥረዋል። በምስራቅ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፑብሊክ አላባራ ያለዉ ግጭት ጦርነት የተፈጥሮ ሃብቱን ክፉኛ እየጎዳ ነዉ።
ጦርነቱ በሰዉ ህይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በእንስሶችና በደኑ ላይም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነዉ, በአካባቢዉ በሚገኘዉ ብሄራዊ ፓርክ ብቻ መኖራቸዉ የሚገለፀዉ የተራራ ላይ ጎሬላዎች ዘራቸዉ ፈፅሞ እንዳይጠፋ ያሰጋል። ደኑም እየተመነጠረ የሚቀርበዉ የከሰል ማገዶ ሌላዉ ችግር ነዉ። እንደአካባቢዉ ፓርክ ዳይሬክተር ገለፃ ከሆነም በየወሩ 80 ኪሎ የሚመዝኑ 120 ሺ ዶንያ ከሰል ይመረታል። ከዚህ ተጠቃሚዉ ደግሞ የሩዋንዳ ነፃ አዉጭ ነን የሚል የሁቱ አማፂ ቡድን ነዉ። በዚህ ግርግር ደግሞ M23 የተባለዉ አማፂ ቡድን የራሱን ስልት ቀይሶ ከቱሪዝም የገንዘብ ምንጭ አድርጎታል። የተመድ በየዓመቱ በጎርጎሮሳዉያኑ የዘመን ቀመር ህዳር ስድስት ቀን በጦርነትና ግጭት ምክንያት የሚወድመዉ የተፈጥሮ አካባቢ እንዲ ታሰብ ከዓመታት በፊት በጠቅላላ ጉባኤዉ አፅድቋል።
ዘንድሮ ድርጅቱ ዕለቱን ሲያስብ ዋና ፀሐፊ ባን ጊሙን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰላምና ፀጥታ ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆናቸዉን ልናስተዉል ይገባል፤ ዘላቂ ሰላምና ከግጭት ማግስት የልማት ተግባራትን ለማከናወን የአካባቢ ተፈጥሮ ክብካቤና የተፈጥሮ ሃብቶች መልካም አስተዳደር ሊኖር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።የዕለቱ ጤናና አካባቢ መሰናዶ ጦርነት በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመረዳት አፍሪቃዊቷን ዴሞክራቲክ ኮንጎ ያስቃኘናል።
ዝግጅቱን ያድምጡ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ